“ለማኅበራዊ ሚዲያ ማድመቂያ በማኅሌቱ የሚታየው የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ሊቆም ይገባል ” ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምትታወቅባቸው እና ከምትገለገልባቸው የማይዳሰሱ ሀብቶቿ መካከል አንዱ እና ዋነኛው ሥርዓተ ማኅሌት ነው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው በገለጻቸው ቤተክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮዋን በማኅሌት ታቀርባለች ፤ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይዘቱን በለቀቀ መልኩ አቀራረቡ ተለይቶ ማኅሌት በማይመስል መልኩ ባልተገባ ሁኔታ ሥርዓቱን ባልጠበቀ አቀራረብ ሲቀርብ እየተመለከትን ነው ብለዋል።
በዚህ ሁኔታ በአሁን ወቅት በተለያዩ የሶሻል ሚዲያዎች የቤተ ክርስቲያኗን ስልት እና ሥርዓት በትክክል በሚገልጽ መልኩ ሲገለገሉ አይታይም ይህን ነገር እግዚአብሔር አይቀበለውምና ሊቀር ይገባል ብለዋል ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ።
አሁን ያለው ሥርዓት ከእግዚአብሔር ጋር አያገናኘንም ቤተክርስቲያንንም አይገልጻትም የጥንት አባቶቻችን ሥርዓት በልክ ተሰርቶ ተቀምጦ ያለው ከሚፈልገው መንገድ ወጥቷልና የሚመለከታቸው አካላት ሊቃውንትን ጨምሮ ይህን እንቅስቃሴ በጊዜ ሊያስቆሙ ይገባል ነው ያሉት።
©eotc tv