
5 ህዳር 2023, 08:39 EAT
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እስራኤል በጋዛ ላይ እያደረገችው ያለውን የተቀናጀ ጥቃት እንድታቆምና የተኩስ አቁም እንዲደረግ እየተደረገ ያለውን ጥሪ ውድቅ አደረጉ።
አንቶኒ ብሊንከን የተኩስ አቁሙ ሐማስ እንደገና እንዲደራጅ እና ተጨማሪ ጥቃቶች እንዲፈጽም ያስችላል ብለዋል።
ነገር ግን እስራኤል በጋዛ ቀጠና ውስጥ በሰለማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ሁሉንም እርምጃዎች መውሰድ እንዳለበትም ተናግረዋል።
ብሊንከን ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እየጠየቁ ካሉ የአረብ መሪዎች ጋር በዮርዳኖስ ቅዳሜ ዕለት ከተነጋገሩም በኋላ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።
አንቶኒ ብሊንክን ከሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ ግብጽ እና ዮርዳኖስ አመራሮች ጋር ተነጋግረዋል።
የአረብ አገራት መሪዎች እስራኤል የጦር ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲሉም ከሰዋል።
“እስራኤል እያደረገችው ያለው ራስ የመከላከል ነው ብለን አናምንም” ሲሉም የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ ከብሊንከን ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ያለችው የተቀናጀ ጥቃት ራሷን ከሐማስ የመከላከል መብት ነው ስትል አሜሪካ ድጋፏን ቀጥላለች።
“ እየተፋፈመ ያለው ጦርነት ንጹሐን ዜጎችን እየገደለ ነው፣ ቤታቸውን፣ ሆስፒታላቸውን፣ ትምህርት ቤቶቻቸውን፣ መስጂዶቻቸውን እና ቤተ ክርስቲያኖቻቸውን እያወደመ ይገኛል” ሲሉም ነው የዮርዳኖሱ መሪ የተናገሩት።
“እየሆነ ያለው በምንም መንገድ ምክንያትም ሆነ ሰበብ ሊፈለግለት አይገባም። ለእስራኤልም ሆነ ለቀጠናው ሰላም አያመጣም” ሲሉም አክለዋል።
- ዶክተር፣ ልብስ ሰፊ፣ ጨቅላ ሕጻን…- በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደሉት መካከል የጥቂቶቹ አሳዛኝ ታሪክ5 ህዳር 2023
- “አንዳንድ ጊዜ ከካሜራ ጀርባ ቆሜ አለቅሳለሁ” የጋዛው ጋዜጠኛ4 ህዳር 2023
- ከ4 ሳምንታት የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት በኋላ በግልጽ የሚታዩ 5 እውነታዎች5 ህዳር 2023
በጋዛ ያለው ጦርነት ሌሎች የቀጣናው መሪዎችን እና ኃይሎችን በመሳብ መካከለኛውን ምስራቅ ወደ አለመረጋጋት ሊመራ ይችላል የሚል ስጋት ደቅኗል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የተኩስ አቁሙን ባይደግፉም ጦርነቱ ለሰብዓዊ እርዳታ ሲባል በጊዜያዊነት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ከአረብ አገራት መሪዎች ጋር ከመወያየታቸው በፊት ወደ እስራኤል አቅንተውም ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ተወያይተው ነበር። አሜሪካ ጦርነቱ በጊዜያዊነት እንዲቆም ያቀረበችው ሐሳብ በእስራኤል ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።
እስራኤል ሐማስን ካላጠፋሁ አላንቀላፋም ብላለች።ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 400 ሰዎች ተገድለዋል።
እስራኤል ከአየር ጥቃት በተጨማሪ የእግረኛ ጦሯን በጋዛ ሰርጥ ውስጥ አስገብታለች።
በአየር እና በመሬት ጥቃቶች እንዲሁም ከባሕር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን በማቀናጀት ጋዛን እያጠቃች እንደሆነ ጦሯ አስታውቋል።
በእነዚህም ጥቃቶች ከ9 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ ሕጻናት ናቸው ብሏል በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር።