ዘለንስኪ አሁንም ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ያሻናል ይላሉ
የምስሉ መግለጫ,ዘለንስኪ አሁንም ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ያሻናል ይላሉ

5 ህዳር 2023, 08:57 EAT

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የጋዛና እሰራኤል ጦርነት በዩክሬን ላይ የነበረውን ትኩረት ሰርቋል ሲሉ ተናገሩ።

ዜሌንስኪ እንዳሉት የዓለም ትኩረት ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲዞር ደግሞ ‘የሩሲያ ፍላጎት’ ነበር።

በዩክሬን የጦርነት አሁናዊ ሁኔታ ዙርያ የተጠየቁት ዜሌንስኪ ጦርነቱ በዩክሬን በኩል ፈቀቅ እያለ አይደለም የሚለውን ሪፖርት አስተባብለዋል።

በቅርብ ጊዜ ከፍተኛ የዩክሬን የጦር መኮንኖች ዩክሬን በጦርነቱ የረባ ድል ልታስመዘግብ እንዳልቻለችና በሁለቱም በኩል ፍጥጫ ሆኖ እንዳለ አምነው ነበር።

በደቡብ በኩል የተደረገው የዩክሬን መልሶ ማጥቃት ብዙ ተብሎለት ብዙ ድል ተጠብቆ የነበረ ሲሆን በውጤቱ ግን እምብዛምም ፈቀቅ ሊል አልቻለም።

ይህ ዜሌንስኪ በጦርነቱ የረባ ድል አለማስመዝገባቸው ምዕራባዊያን ለዩክሬን የሚሰጡትን እርዳታ ቆም ብለው እንዲያስቡበት ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ፍርሃት አለ።

በዩክሬን ደጋፊ አገራት በኩል ከወዲሁ የመታከት ሁኔታ መታየት ጀምሯል። አንዳንድ አገራት ከፍተኛ ገንዘብና ጦር መሣሪያ ለዩክሬን የምንሰጠው ‘እስከመቼ ነው?’ የሚል ጥያቄም እያነሱ ነው።

ባልተያያዘ ዜና ቅዳሜ የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ረስተም ኡሜሮቭ የ128ኛው ብርጌድ አባል የሆኑ የዩክሬን ወታደሮች የተገደሉበት ሁኔታ እንዲጣራ አዘዋል።

በዚህ ጥቃት ምን ያህል ወታደሮች እንደተገደሉ አሐዝ ባይሰጡም ዐርብ ዕለት የሩሲያ ሚሳኤል በደቡባዊ ዛፖሮዢያ በርካታ የዩክሬን ወታደሮችን ሳይገድል አልቀረም።

የዩክሬን ሚዲያዎች ከ20 በላይ የዩክሬን ወታደሮች በዚህ ጥቃት ተገድለዋል ብለዋል።

የዩክሬን ወታደራዊ ጽሕፈት ቤት ቅዳሜ ዕለት እንደገለጸው በክሪሚያ ሩሲያ መርከብ ለመገንባት የምትገለገልበትን አንድ ተቋም ማጥቃቱን ይፋ አድርጓል።

የዩክሬን ደቡባዊ ባሕረ ሰላጤ ክሪሚያ በ2014 ነበር በሩሲያ በኃይል የተያዘው።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር በበኩሉ ከተተኮሱት 15 ሚሳኤሎች 13ን ማምከኑን እና ሆኖም ግን የሩሲያ አንድ መርከብ ላይ ጉዳት መድረሱን አምኗል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ባለፈው ቅዳሜ ኪየቭን በጎበኙበት ወቅት ዘለንስኪ እንዳሉት ይህ የጋዛ ጦርነት ለዩክሬን የሚሰጠውን ትኩረት ወስዶታል።

ጨምረውም፣ ሩሲያ ይህ በዩክሬን ላይ የነበረው የዓለም ትኩረት እንዲዳከም ወይም ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄድ ትፈልግ ነበር ብለዋል።

ዘለንስኪ ሩሲያ በጦርነቱ የአየር ቁጥጥር የበላይነት እንደያዘች ያመኑ ሲሆን አገራቸው ይህን ለመቋቋም በአስቸኴይ አሜሪካ ሠራሽ ኤፍ-16 ልትታጠቅ ይገባል ብለዋል።

ዜሌንስኪ በምዕራባዊያን ዘንድ ከፑቲን ጋር እንዲደራደሩ ግፊት አይሎባቸዋል የሚለውን የአንዳንድ ሚዲያዎች አስተያየት አስተባብለዋል።

“በዚህ ወቅት ከአውሮፓ ኅብረትም ሆነ ከአሜሪካ መሪዎች አንዳቸውም ከሩሲያ ጋር እንድንደራደር ግፊት አላደረጉብኝም” ብለዋል።

”ከሩሲያ ጋር መደራደሩ በጭራሽ የማይታሰብ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ፑቲን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ዩክሬን የሞከረችው የመልሶ ማጥቃት መክሸፉን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሚኒስትራቸው ሰርጌይ ሾይጎ በበኩላቸው ኪየቭ ምንም እንኳ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ እርዳታ በገፍ እየቀረበላት ቢሆነም በጦርነቱ ግን ጭራሽ ሊሳካላት አልቻለም ብለዋል።