በአየር ጥቃቱ የተገደሉ ጋዛውያን

5 ህዳር 2023, 07:59 EAT

ጋዛ በእስራኤል የማያባራ የአየር ጥቃት ወደ ፍርስራሽነት ተቀይራለች።

ለአንድ ወር ያህል እየተካሄደ ባለው የአየር ጥቃት ትምህርት ቤቶች፣ መጠለያ ጣቢያዎች፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጂዶች እና ሌሎችም ወድመዋል።

እስራኤል ሐማስን ካላጠፋሁ አላንቀላፋም ብላለች።

ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 400 ሰዎች ተገድለዋል።

እስራኤል ከአየር ጥቃት በተጨማሪ የእግረኛ ጦሯን በጋዛ ሰርጥ ውስጥ አስገብታለች።

በአየር እና በመሬት ጥቃቶች እንዲሁም ከባሕር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን በማቀናጀት ጋዛን እያጠቃች እንደሆነ ጦሯ አስታውቋል።

በእነዚህም ጥቃቶች ከ9 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ ሕጻናት ናቸው ብሏል በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር።

ቢቢሲ በእነዚህ ጥቃቶች የሚወዷቸውን ሰዎች ያጡ ቤተሰቦችን እና የዐይን እማኞችን አናግሯል።

ዩሱፍ አቡ ሙሳ

ዩሱፍ አቡ ሙሳ
የምስሉ መግለጫ,ዩሱፍ አቡ ሙሳ

እስራኤል ጋዛን በሙሉ ከበባ ውስጥ አስገብታ ነዳጅ፣ ኤሌክትሪክ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን አቋርጣለች።

ጋዛም ከፍተኛ የኃይል እጥረት ገጥሟታል።

የኻን ዩኒሱ ታዳጊው የሰባት ዓመቱ ዩሱፍ አቡ ሙሳ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን ዕድለኛ ነበር።

ዩሱፍም ሆነ ታላላቆቹ የዘጠኝ ዓመቱ ሃመድ እና እህቱ ጁሪ የካርቱን ፊልሞቻቸው አልተቋረጠባቸውም ነበር።

ምስጋና ይግባውና በናስር ሆስፒታል ራዲዮግራፈር (የራጅ ባለሙያ የሆነው) አባታቸው መሐመድ አቡ ሙሳ ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫ [ሶላር] በቤቱ በመግጠሙ መብራት ነበራቸው። አባታቸው ታዳጊዎቹ የሚወዷቸው ፊልሞች እንዳይቋረጥ አድርጎ ነበር።

እንደተለመደውም ጥቅምት 4/2016 ዓ.ም. ታዳጊዎቹ ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ሳለ ቤታቸው በእስራኤል የአየር ጥቃት ተመታ።

ጁሪና ሃመድ ተረፉ። የቤቱ ጣሪያ ሲደረመስ የሰባት ዓመቱ ታዳጊ ዩሱፍ ተገደለ።

በወቅቱም መሐመድ በሆስፒታሉ ውስጥ የ24 ሰዓት ፈረቃ ላይ ነበር። ባለቤቱ ዩሱፍን ፍለጋ ወደ ሆስፒታሉ እየጮኸች ገባች።

ሃመድን ወዲያው ማግኘት ቻለች።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ጁሪን ከፍርስራሹ ውስጥ አውጥተዋት ሕይወቷ ተርፏል።

ጭንቅላቷ ላይ ጉዳት ቢደርስባትም ወላጆቿ እያገገመች እንደሆነም ይናገራሉ።

ራዋን “ፍሪዝ ፀጉር ያለውን ቆንጆ ልጅ” በሆስፒታሉ ውስጥ አለ ወይ? እያለች ከወዲያ ወዲህ ስታማትር የሚያሳይ ቪዲዮንም በርካቶች ተመልክተውታል።

መሐመድ የልጁን አስከሬን በሆስፒታል የሬሳ ክፍል ውስጥ አገኘው።

“ለመጨረሻ ጊዜ ዩሱፍን በሕይወት ያየሁት ወደ ሥራ ከመሄዴ በፊት እየሮጠ መጥቶ በር ላይ እቅፍ ሲያደርገኝ ነው” ይላል መሐመድ በሐዘን።

“ብስኩት እና ሙዝ ከሰጠሁት በኋላ ሳመኝ እና ቻው አለኝ። ሁልጊዜም ወደ ሆስፒታል ስለምሄድ ይሆናል ዶክተር የመሆን ህልም ነበረው” ሲል አባቱ ስለተነጠቀው ልጁ ተናግሯል።

ዶክተር ሚድሃት ሳይዳም

ዶክተር ሚድሃት ሳይዳም
የምስሉ መግለጫ,ዶክተር ሚድሃት ሳይዳም

ዩሱፍ በተገደለበት በዚያ ምሽት ዶክተር ሳይዳም እረፍት አስፈልጓቸው ቤታቸው ነበሩ።

የ47 ዓመቱ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ በጋዛ ከተማ በሚገኘው በአልሺፋ ሆስፒታል ለሳምንት ያህል ሳይወጡ ሌት ተቀን ሲሰሩ ነበር። በዚያች ምሽት የሥራ ባልደረቦቻቸውን ተሰናብተው ወደ ቤት ሄዱ።

ነገር ግን ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ተገደሉ።

“የዚያ የተረጋጋ፣ ተጫዋች እና ደግ ዶክተር አስከሬን በማግሥቱ ጥዋት ይሠራበት ወደነበረው ሆስፒታላችን አመጡት” ሲሉ የሥራ ባልደረባቸው ዶክተር አድናን አልቡርሽ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶክተር አልቡርሽ በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደሉትን ዶክተር ሳይዳምን ለ20 ዓመታት ያውቋቸዋል።

ለሙያቸው እና ለሥራቸው በነበራቸው ትጋትም በሥራ ባልደረቦቻቸው ዘንድ “እረፍት አልባው ዶክተር” የሚል ቅጽል ስም እንዳስገኘላቸውም ይናገራሉ።

በሆስፒታሉ በቀዶ ሕክምና ሐኪምነት ፈር ቀዳጅ የነበሩት ዶክተር ሳይዳም ወጣት ዶክተሮችንም መንገድ በማሳየት እና በማማከርም ትልቅ ስም አትርፈዋል።

“ዶክተሮች ችግር ቢያጋጥማቸው ዶክተር ሳይዳም ጋር መፍትሄ እንዳለ ያውቁ ነበር” ሲሉ በአልሺፋ ሆስፒታል የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አህመድ ኤል ሞካላቲ ተናግረዋል።

“የእሱ መቀጠፍ ለዚህ ሆስፒል ብቻ ሳይሆን ለሕክምና ባለሙያዎችም ትልቅ ኪሳራ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ኑር ዩሱፍ አል ካርማ

ኑር ዩሱፍ አል ካርማ
የምስሉ መግለጫ,ኑር ዩሱፍ አል ካርማ

ኑር የ17 ዓመት ተማሪ ነበረች።

በደቡባዊ ጋዛ 14 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዴር አል ባላ ከተማ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት መገደሏን አጎቷ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአየር ጥቃቱ ሌት ተቀን ሲፈጸምም የእህታቸው ልጅ ሕይወቷን ለማትረፍ ከዘመዶቿ ጋር መቆየት አስባ ነበር ይላሉ መሐመድ አል ካርማ።

“አባቷ ሌላ ቦታ እንዳትሄድ እና እዚያው እንድትቆይ ነገሯት። በነገታውም ቤታቸው በአየር ድብደባ ተመታ። ዕጣ ፈንታዋ ነበር ማለት ነው” ይላሉ።

ኑር የተገደለችው ከወንድሟ ልጅ ከያዛን ጋር ነው። ሁለቱም ሳሎን ውስጥ እየተጫወቱ ነበር። ታላላቅ እህቶቿ ኦላ እና ሁዳ ከእናታቸው ጀማልታት ጋር ቁርስ እያዘጋጁ ነበር። እንደ ዕድል ሆኖ እነሱ በሕይወት ተረፉ።

ኑር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የምታጠናቅቅበት የመጨረሻው ዓመት ላይ ነበረች። ዶክተርም የመሆን ህልም ነበራት። የትምህርት ቤት ቦርሳዋም በአየር ጥቃት ከወደመው ፍርስራሹ ስር ተገኝቷል።

በቦርሳዋ ውስጥም መጽሐፎች እና ማስታወሻ ደብተር ተገኝተዋል። በአንዱ ገጽ ላይም “ቤተሰቦቼ እንዲኮሩብኝ እፈልጋለሁ። በአላህ ፈቃድ ከፍተኛ ውጤት አገኛለሁ” የሚል ጽሁፍ አስፍራለች።

ሉሪን አዛም አቡሃሊማ

ሉሪን አዛም አቡሃሊማ
የምስሉ መግለጫ,ሉሪን አዛም አቡሃሊማ

ሉሪን ለመጨረሻ ጊዜ ለእጮኛዋ ካሌድ አል ማስሪ በላከችው መልዕክት “ከማያባራው የአየር ጥቃት ለማምለጥ ከስፍራ ወደ ስፍራ መንቀሳቀስ ደክሞኛል” ብላው ነበር።

የ30 ዓመቷ ሉሪን ከአክስቷ ጋር ለመቆየት በሚል በጋዛ ሰርጥ መሃል ወደ ሚገኘው ኑሴራት የስደተኞች መጠለያ ሄዳለች። ሉሪን በጋዛ ከተማ የወላጆቿን መኖሪያ ቤት ያወደመውን የአየር ጥቃትን ጨምሮ ከሁለት የአየር ጥቃቶች ተርፋ ነበር።

“ገላዬን ልታጠብ፣ ልጸልይ እና ልረፍ” አለችኝ ይላል በቆጵሮስ ነዋሪ የሆነው እጮኛዋ ካሊድ።

የነበረችበት ቤት በአየር ጥቃት ሲመታም እየጸለየች በነበረችበት ወቅት ነው።

“የተገደለችው በጸሎት ላይ እያለች ነው” ብሏል እጮኛዋም።

ሉሪን እና ካሊድ በጋዛ ባለው ያልተረጋጋ ሁኔታ ምክንያት ሠርጋቸውን ለሁለት ጊዜ አራዝመዋል።

በመጨረሻም ታኅሣሥ ወር ላይ ለመጋባት ቀን ቆርጠው ነበር። ኑሯቸውንም ወደ ቆጵሮስ ሊያደርጉም ዕቅድ ነበራቸው።

“አሁን ለዘላለም አርፋለች። ነጭ ቀሚስ ትለብስ ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ግን ነጭ መጎናጸፊያ ለብሳ ላትመለስ ሄዳለች” ሲል ልቡ በሐዘን የተሰበረው እጮኛዋ ተናግሯል።

ፈቅሪያ ሐሰን አብዱል አል

ፈቅሪያ ሀሰን አብዱል አል
የምስሉ መግለጫ,ፈቅሪያ ሐሰን አብዱል አል

በጋዛ ከተማዋ ራድዋን ሰፈር በዓል፣ ሠርግ፣ እንዲያው የትኛውም ዝግጅት ካለ በርካቶች ወደ ፈቅሪያ ያቀናሉ።

ታዋቂ ልብስ ሰፊ ነበረች፣ ብዙዎችን ያስጌጠች።

“ቤታችን በሙሽሮች፣ በሚዜዎች፣ በአበባ ያዦች ሁሌም እንደተሞላ ነበር። በልብስ ስፌት ለየት ያለ ችሎታ ነበራት” ትላለች የፈቅሪያ ልጅ ኔቪን።

ተጠልለውበት የነበረ ቤት በእስራኤል የአየር ጥቃት በመመታቱ የ65 ዓመቷ ልብስ ሰፊ ፈቅሪያ ተገድላለች። አብረዋትም ሁለት ወንድሞቿ፣ ሁለት ልጆቿ እና ሁለት የልጅ ልጆቿ ተገድለዋል።

በጓደኛዋ ቤት ተጠልላ የነበረችው ኔቪን እናቷ ቤተሰቧን በጣም የምታፈቅር፣ ትልልቅ የቤተሰብ ድግሶችን ማዘጋጀት የምትወድ እንደነበረች ትናገራለች። ግጭቱ በተባባሰበት ወቅት የእናቷ ስሜት ክፉኛ ተጎድቶ ነበርም ብላለች።

“ይህ መጨረሻ የሌለው ጦርነት አድክሞኛል” ስትል ነበር ከልጇ ጋር በነበራት የስልክ ጥሪ የተናገረችው።

ማዘን እና አህመድ አቡ አሲ

ማዘን  አቡ አሲ
የምስሉ መግለጫ,ማዘን አቡ አሲ

ሁለቱ ወንድማማቾች የ17 ዓመቱ ማዘን እና የ13 አህመድ የተገደሉት በአል አህሊ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንዳታ ነው።

የፍልስጥኤም ባለሥልጣናት ፍንዳታው የተከሰተው በእስራኤል አየር ጥቃት እንደሆነ አስታውቀዋል። እስራኤል በበኩሏ ይህንን ያስተባበለች ሲሆን፣ ፍንዳታው የተከሰተው በፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ የከሸፈ ሮኬት ምክንያት ነው ብላለች።

ሁለቱ ወንድማማቾች በጣም ቢቀራረቡም ባህርያቸው የተለያየ ነበር ይላሉ አባትየው አረፋት አቡ ማሲ።

አረፋት እና ባለቤታቸው የጥርስ ሐኪም ለመሆን ህልም የነበረውን ማዘንን ለመውለድ ለፍተዋል። ለስምንት ዓመታትም ያህል ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን የሚባለውንም ሕክምና ከተከታተሉ በኋላ ነበር ማዘን ሊጸነስ የቻለው።

“ከሁሉም ልጆቼ በበለጠ ብሩህ አዕምሮ ነበረው” ይላሉ አባቱ ስለ ማዘን ሲናገሩ።

 አህመድ አቡ አሲ
የምስሉ መግለጫ,አህመድ አቡ አሲ

የ13 ዓመቱን አህመድን ደግሞ “በጣም ጠንካራ፣ ደፋር እና ሥራ ፈጣሪ ነው” ይሉታል አባቱ።

“በቤታችን አቅራቢያ ባለች ትንሽ ዳስ ውስጥ አሻንጉሊቶችን እና የትምህርት ቤት ቁሳቁሶችን ይሸጥ ነበር” ይላሉ አባት አረፋት።

በሕይወት የቀራቸው ልጅ የሦስት ዓመቱ ፋራጅ ብቻ ነው። እሱም ወንድሞቹ የት ናቸው እያለ ሥራው ቀን ተሌት ማልቀስ ሆኗል።

“አምላክ በሰማይ እንዲኖሩ መርጧቸዋል ብዬ ነገርኩት። ለሁለቱ ጎበዝ ልጆቼ የተሻለ ቦታ ነው” ብለዋል ልጆቻቸውን የተነጠቁት አረፋት።

የ26 ዓመቷ ፋርማሲስት ሳፋ ኔዛር ሃሱና
የምስሉ መግለጫ,የ26 ዓመቷ ፋርማሲስት ሳፋ ኔዛር ሃሱና

የ26 ዓመቷ ፋርማሲስት ሳፋ ኔዛር ሃሱና በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ውስጥ በተፈጸመው የአየር ጥቃት ነው የተገደለችው።

በወቅቱ ከሦስት ወር ጨቅላዋ ኤልያና እና ከባለቤቷ ጋር ተኝታ የነበረ ሲሆን፣ ሁሉም በአየር ጥቃቱ ተገድለዋል።

የ32 ዓመቷ ጋዜጠኛ ሳሌም ማማ፣ ከባለቤቷ፣ የሁለት ዓመት እድሜ ካላት ሴት ልጇ እንዲሁም ከሰባት ዓመት ወንድ ልጇ ጋር በእስራኤል አየር ጥቃት ተገድላለች። የአምስት ዓመት ልጇ ብቻውን ተርፏል።

ባለፉት ሦስት ሳምንታት 33 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 28ቱ ፍልስጤማውያን መሆናቸውን የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ አስታውቋል።

በተለይም የጋዛ ጋዜጠኞች ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ዋጋ እየከፈሉ ነው ብሏል።

የ32 ዓመቷ ጋዜጠኛ ሳሌም ማማ
የምስሉ መግለጫ,የ32 ዓመቷ ጋዜጠኛ ሳሌም ማማ