
5 ህዳር 2023, 09:23 EAT
አሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ወደ ጋዛ ሰማይ በመላክ ቅኝት እንዲያደርግ ማድረጓን ለመጀመርያ ጊዜ አመነች።
የፔንታገን ቃል አቀባይ ብሪግ ፓት ራይደር ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ‘አጋቾችን በተመለከተ መረጃ ለመሰብሰብ’ የተላኩ ነበሩ ብለዋል።
“ይህ የቅኝት በረራ የተደረገው ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ነው።”
አሜሪካ የድሮን ቅኝት ማድረጓን ያመነችው በረራዎችን እየተከታተሉ የሚዘግቡ ድረ ገጾች ይህንኑ ክስተት ማጋለጣቸውን ተከትሎ ነው።
ፔንታገን ዐርብ ባወጣው መግለጫ፣ “አሜሪካ ሰው አልባ ድሮኖችን በጋዛ ቅኝት እንዲያደርጉ፣ ለአጋር አገር እስራኤል ድጋፍ እንዲሰጡ፣ በተለይም ደግሞ የታገቱ ሰዎች ያሉበትን መረጃ ለማግኘት ተልከዋል” ይላል።
እነዚህ ድሮኖች ከዚህ ቀደም በአፍጋኒስታን አገልግሎት ላይ ውለዋል። በዋናነት የቅኝት ሥራ የሚሠሩ ሲሆን ከ20 ሰዓታት በላይ አየር ላይ ያለምንም ችግር መቆየት የሚያስችል አቅም አላቸው።
ስማቸውን መግለጽ ያልወደዱ ምንጮት ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በሰጡት ጥቆማ እነዚህ ድሮኖች ለእስራኤል ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት ሳይሆን ታጋቾቹ ያሉበትን ለማፈተሽ ነው አገልግሎት ላይ የዋሉት፤ ታጋቾቹን በተመለከተም ድሮኖቹ የቃረሙት መረጃ ለእሰራኤል ተላልፎ ተሰጥቷል።
ይሁንና እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ብቻ አይደሉም በአካባቢው ሥራ ላይ የዋሉት።
ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ ባሕር ኃይል በአረቢያን ባሕር ሰው አልባ በሆነ ፈጣን ጀልባ የታገዘ ጥቃት መሰንዘሩን ገልጧል።
ባሕር ኃይሉ እንዳለው ሰው አልባ በሆነ መሣሪያ ጥቃት በዚህ መሣሪያ ሲፈጸም በመካከለኛው ምሥራቅ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።
ይህ ክስተት አሜሪካ በአካባቢው ያላትን ወታደራዊ አቅም ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው ተብሏል።
- ዶክተር፣ ልብስ ሰፊ፣ ጨቅላ ሕጻን…- በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደሉት መካከል የጥቂቶቹ አሳዛኝ ታሪክ5 ህዳር 2023
- ከ4 ሳምንታት የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት በኋላ በግልጽ የሚታዩ 5 እውነታዎች5 ህዳር 2023
- ብሊንከን የጋዛ የተኩስ አቁም ጥሪን ውድቅ አደረጉ5 ህዳር 2023
ባለፈው ወር የአሜሪካ ባሕር ኃይል ከየመን አቅጣጫ ወደ እስራኤል የተተኮሱ በርካታ የድሮንና የሮኬት ጥቃቶችን ማምከኑ ተነግሯል።
አሜሪካ ሁለት የጦር ጄት ተሸካሚ ከፍተኛ ወታደራዊ መርከቦችን ወደ ምሥራቅ ሜዲትራኒያን ባሕር ማስጠጋቷ አይዘነጋም።
ይህን ያደረገችው በሐማስና በእስራኤል የሚደረገው ጦርነት ተከትሎ ሌሎች የአካባቢው አገሮች እጃቸውን እንዲሰበስቡ ለማድረግ ነው።
ከትናንት በስቲያ ዐርብ ስሜት በተቀላቀለበት ሁኔታ ንግግር ያደረጉት የሒዝቦላህ መሪ ሐሰን ነስረላህ የአሜሪካ የጦር ጄት ተሸካሚ ወታደራዊ መርከቦች አንዳችም ዓይነት ጥቃት ለመሰንዘር እንዳይሞክሩ አሳስበው ነበር።
“የናንተ ወታደራዊ መርከቦች አላስፈሩንም፤ ወደፊትም አንፈራቸውም” ብለው ነበር ሐሰን ነስረላህ፤ ዐርብ ዕለት በርካቶች በተከታተሉት ንግግራቸው።