በአድዋ 00 ሙዚየም የሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ ስራ ሂደት ላይ ቅሬታ እንዳለው የኢትዮጵያ የሠዓሊያን እና ቀራፂያን ማህበር ገለፀ።

የሙዚየሙ የሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ ስራ ሂደት በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ሊሰራ ሲገባ ግልፅ ባለሆነ ምክንያት ለቻይናዊያን ባለሙያዎች ስራው ተላልፎ መሰጠቱን አግባብ አይደለም ያለው የኢትዮጵያ የሠዓሊያን እና ቀራፂያን ማህበር ነው፡፡
መንግስት የኪነ-ህንፃ ግንባታውን ከስነ ጥበብ ፕሮጀክቱ ለይቶ ስነ ጥበቡን በሀገር ጥበበኞችና አዋቂዎች አስመክሮ፣ ንድፍ አስቀርቦና አስገምግሞ ማሰራት ይገባው ነበር ሲሉ የኢትዮጵያ ሠዓሊያን እና ቀራፂያን ማህበር ዋና ፀሐፊ አርቲስት ወንድወሰን ከበደ ለጣቢያችን ገልፀዋል::

ኢትዮጵያ በስነ-ጥበብ የምትታይበት መድረክ መሆን የሚችል ሙዚየምን ጨረታ እንኳን ባልወጣበት ሁኔታ የሀገሪቱ የስዕል እና ቅርፃ ቅርፅ ሊቆች አሻራቸውን እንዳያስቀምጡ መደረጉን ባለሙያዎች አብራርተዋል::
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ጉምቱ የስነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ሃሳብ ያላካተተ የስነ-ጥበብ ፕሮጀክት አግባብነት የለውም ያሉት ዋና ፀሐፊው ኃላፊነቱ የተሰጣቸው ቻይናውያን ተደራድረው 19 የሀውልት ስራን ለአንድ ግለሰብ ሠጥተዋል ሲሉም አክለዋል::
አርቲስት ወንድወሰን ከበደ እንዳሉት በሙዝየሙ የስነጥበብ ስራ ላይ ውይይት ሊደረግበት እና ለሕዝብ ግልፅ ሊሆን ስለሚገባ መንግስት ውሳኔውን ከልሶ በድጋሜ ማጤን አለበት በማለት አፅዕኖት ሰጥተዋል::
በጉዳዩ ዙርያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት ምላሽን ለማካተት ተደጋጋሚ የሆነ ሙከራ ብናደርግም ሳይሳካ ቀርቷል:: ሆኖም የከተማ አስተዳደሩን ምላሽ ባገኘን ጊዜ የምናቀርብ ይሆናል::
ምንጭ፦ አራዳ FM