ማኅበራዊ ከወጣቶች 80 በመቶው ሥራአጥ በሆኑባት ከተማ የተጀመረው የሥራ ላይ ልምምድ

አበበ ፍቅር

ቀን: November 5, 2023

የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ በየዓመቱ አዳዲስ መመርያዎች ቢዘጋጁም፣ እዚህ ግባ የሚባል መፍትሔ አልተገኘለትም፡፡ ይልቁንስ በየወቅቱ እያሻቀበ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ ይነገራል፡፡

ከችግሩ ስፋትና አሳሳቢነት የተነሳም መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና አምራች ኢንዱስትሪዎች ችግሩን ለማቃለል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡

ይሁን እንጂ በየወቅቱ የሚፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ከሚወጡት ተማሪዎችና ሥራ አጥተው በቤታቸው ከሚውሉት ወጣቶች ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ አይደለም፡፡

ወጣቶች በተለይ ትምህርታቸውን ጨርሰው የልፋታቸውን ውጤት ሳያገኙና ህልማቸው ዕውን ሳይሆን ሲቀር ለከፋ ድባቴና ለተለያዩ ሱሶች ከመጋለጣቸው ባሻገር፣ ለተለያዩ ዝርፊያና ለውንብድና ተግባር ተጋላጭ መሆናቸው አይቀርም፡፡

ብዙ ወጣቶችም ራሳቸውን ለማጥፋት ከሚያነሳሳቸው ጉዳይ መካከል አንዱ ሥራ አጥ መሆን እንደሆነም ይወራል፡፡ በሌላ በኩል ወጣቶች ሥራ ባጡ ቁጥር ወደ ጦርነት የመግባት ዕድላቸውም ሰፊ ነው፡፡

በሥራ አጥነት ዙሪያ ያለውን ክፍተት ይሞላል፣ ወጣቶንም በሠለጠኑበት የሥራ ዘርፍ ለመቀጠር፣ ቀጣሪ ድርጅቶችም ብቁ የሆነ የሰው ኃይል የሚያገኙበትን ዕድል ለማመቻቸት ያስችላል የተባለውና ከ2014 ዓ.ም. የቀጠለ የሥራ ላይ ልምምድ ሊሰጥ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

ለስድስት ወራት የሚቆየው ሥልጠና ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 25 የሆኑና የትምህርት ደረጃቸው 12ኛ ክፍልና ከዚያ በታች የሆኑ የሚሳተፉበት ነው፡፡ በዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑትም በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ያቋረጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሲሆኑ፣ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ገብተው ለስድስት ወራት የሥራ ላይ ልምምድ የሚያደርጉና በቂ የሥራ ክህሎት የሚቀስሙበትም ይሆናል፡፡

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ከ49 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ እንደሚያደርጉ፣ ቢሮው ከአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር በመሆን ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ‹‹ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ የልምምድ ፕሮግራም›› በሚል መሪ ቃል ባደረገው የምክክር መድረክ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የቢሮው ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ እንዳሉት፣ በመዲናዋ ከሚገኙት ወጣቶች 80 በመቶ የሚሆኑት ሥራ አጥ ናቸው።

ይህንን ክፍተት ያቃልላል የተባለው ፕሮጀክት በ2014 ዓ.ም. ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወሱት አቶ ጃንጥራር፣ በተለይ በ2015 ዓ.ም. ከ10 ሺሕ በላይ ወጣቶች በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሥራ ላይ ልምምድ እንዳደረጉና ብቃታቸው ታይቶ እንደ ተቋማቱ ይሁንታ በቋሚነት ተቀጥረው እንዲሠሩ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

7,300 ወጣቶች በሥራ ላይ ልምምድ መቆየታቸውንና ከቆዩት ውስጥ አምስት ሺሕ ገደማ በአሁኑ ወቅትም በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሥራ ላይ ልምምድ እያደረጉ እንደሚገኙም አክለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በ2016 ዓ.ም. ከ15 ሺሕ የሚልቁ ወጣቶች በከተማዋ በሚገኘ በሆቴል፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽንና በአምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ለተከታታይ ስድስት ወራት የሥራ ላይ ልምምድ እንደሚያደርጉ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

ወጣቶቹ የተግባር ላይ ልምምዱን ለማድረግ ሲሄዱ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች የልጆቹን ጉልበት እንደሚበዘብዙ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሥራውን ጠጋ ብለው እንዳይሠሩ በማድረግ በሙያው ላይ ዕውቀቱ ሳይኖራቸው ሠልጥነዋል ብለው የምስክር ወረቀት እንደሚሰጡ አንስተዋል።

ሆኖም ወጣቶቹ በሚኖሩበት ወረዳ ተመዝግበው በአቅራቢያቸው በሚገኝ ድርጅት በሚፈልጉት የሙያ ዘርፍ በቀን ለ8፡00 ሰዓት፣ በሳምንት ለአምስት ቀናትና በወር ደግሞ ለ22 ቀናት ከባለሙያዎች ጎን በመሆን ዕውቀትን እንደሚቀስሙ ታሳቢ ተደርጎ ነው ፕሮግራሙ የተጀመረው።

ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር ሌላ ነገር መሸፈን ባይችልም፣ ለትራንስፖርት የሚሆን በየቀኑ 110 ብር፣ በወር 2,420 ብር በጠቅላላው በስድስት ወራት 14,520 ብር እንደሚሰጣቸው አቶ ጃንጥራር አስታውቀዋል።

ወደ ሥልጠና ከሚገቡት መካከልም 60 በመቶው ሴቶች እንደሆኑና ከእነዚህ መካከልም ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ያሏቸው 945 ብር ተጨማሪ ክፍያ ይሰጣቸዋል፡፡ የስድስት ወራቱን የሥራ ላይ ልምምድ ላጠናቀቁ ወጣቶች ደግሞ የሥራ ማፈላለጊያ 7,260 ብር ይሰጣቸዋል ተብሏል። ለዚህና አጠቃላይ ላለው የመጀመሪያ ዙር የሥልጠና ወጪ አንድ ቢሊዮን ብር መመደቡም ተገልጿል።

ወጣቾቹ በሚኖሩበት ወረዳ ሥራ አጥ መሆናቸው ተመስክሮ ከተመለመሉ በኃላ፣ ቀጥታ ወደሚፈልጉት ድርጅት ከመሄዳቸው በፊት የተለያዩ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና እንደሚሰጣቸው የተናገሩት ደግሞ የቢሮው የሥራ ሥምሪትና ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሡልጣን ናቸው።

የሕይወት ክህሎት ሥልጠና የወሰዱ ወጣቶችንና የአምራች ድርጅት ባለቤቶችን በማገናኘት ከአራት ሰዎች ጀምሮ እንደ ድርጅቱ የሰው ኃይል ፍላጎት እስከ መቶ ሃምሳና ከዚያ በላይ ተለማማጅ ወጣቶችን መውሰድ ይችላሉ ብለዋል፡፡

‹‹ወጣቶቹ ለድርጅቶቹ ፀጋዎች ናቸው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ድርጅቶች ወጣቶቹን ተቀብለው ኃላፊነት በመውሰድ በሙያው ላይ በቂ ዕውቀትን እንዲያስጨብጧቸው ከሥልጠና በኃላም በቋሚነት ቀጥረው እንዲያሠሯቸው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

‹‹ሠልጥነው በተሰማሩበት የሥራ መስክ በቂ ሙያን ይዘው ለሚወጡ ወጣቶች፣ መንግሥት ሥራ አፈላልጎ የማስቀጠር ግዴታ አለበት፤›› ሲሉ ዳይሬክተሩ አክለዋል።

በውይይቱ በሥራ ፈላጊዎችና በድርጅቶች በኩል ያሉ ክፍተቶችን ብቻ እንጂ በመንግሥት በኩል ያሉ ችግሮች አልተነሱም የሚል ቅሬታ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች በኩል የተነሳ ሲሆን፣ በመንግሥት በኩልም ትልቅ ክፍተት በመኖሩ በደንብ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል።

የመሥሪያ ቦታ በማጣታቸውና ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥረው የሚሠሩበት ቦታ አግባብነት በጎደለው መንገድ ተቀምተው ለሌላ እየተላለፈ መሆኑን በመጠቆም፣ ‹‹የሥራ ዕድልን የምንፈጥረው እንዴት ነው?›› ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ያላግባብ ከባድ ኪሳራ እየደረሰበት ነው በሚል ለሚመለከተው አካል አቤት ቢሉም፣ ሰሚ አለማግኘታቸውን ተናግረው፣ ምቹ የመሥሪያ ቦታ ባለማግኘታቸው ቀጥረው ማሠራት ቀርቶ እንደ ድርጅት በገበያ ላይ ለመቆየት አዳጋች እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ ችግሮቹን አግባብ ባለው መንገድ ከተፈቱ ወጣቶችን ተቀብለው በማሠልጠን ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከመሥሪያ ቦታ እጥረት፣ የወጣቶች የሥራ ፍላጎት አለመኖርና ተያያዥ ጥያቄዎች በመድረኩ የቀረቡ ሲሆን፣ የቢሮው ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ጃንጥራር እንደሚሉትም፣ በማንኛውም መሥፈርት ቢሆን ለእያንዳንዱ ሥራ ፈጣሪ መሬት ማቅረብ ፈፅሞ የማይቻል ነው ብለዋል፡፡

‹‹በመንግሥት በተሰጠው ሼድ ውስጥ የምትሠሩ ሰዎች በሥራ ዕድል ልምምድ ሰበብ ዋስትና እየፈለጋችሁ ከሆነ ይህ ፈፅሞ ሊሆን አይችልም፤›› ያሉት አቶ ጃንጥራር፣ ሼድ ወስደው አምስት ዓመት የሞላቸው ኢንተርፕራይዞች ላይ በተደረገ ምልከታ በተሰጣቸው ዓላማ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ እንዳሉ ሁሉ፣ መሥራት ባለመቻላቸው ያከራዩ ወጣቶች መኖራቸውን አውስተዋል።

ከዚህ ወጪ ላልተፈለገ ዓላማ ሲያውሉ የነበሩ ሰዎች መገኘታቸውን አብራርተዋል። ወጣቶች ሼዱን ከወሰዱ ከአምስት ዓመታት በኋላ ቀጣይ ለሚመጣው ትውልድ ማሸጋገር ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡  

በከተማዋ ካለው ጠቅላላ 7 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ 22.8 በመቶው ወይም 1.56 ሚሊዮኑ ወጣት ሥራ ይፈልጋል ያሉት አቶ ጃንጥራር፣ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኢንተርፕራይዞች በተሰጣቸው ሼድ አምስት ዓመታት ከሞላቸው ለቀጣዩ ሊያስረክቡ ይገባል ብለዋል።