

በ25ኛው የጤና ጉባዔ የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል
ማኅበራዊ በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዕጥፍ በላይ ጨመረ
ቀን: November 5, 2023
- ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ ተይዘዋል
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3.3 ሚሊዮን የወባ በሽተኞች መለየታቸውን፣ ይህም በ2014 በጀት ዓመት ተመዝግቦ ከነበረው 1.6 ሚሊዮን ከዕጥፍ በላይ መጨመሩን የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
‹‹ጠንካራ የጤና ፋይናንስ ለዘላቂ የጤና ልማት›› በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀናት የተካሄደው 25ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በተከፈተበት ሥነ ሥርዓት ሚኒስትሯ እንዳመለከቱት፣ ወባ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ መቀነስ ቢያሳይም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ፣ ከዚህ በፊት ከተለመዱት በሽታ አስተላላፊ ትንኞች በተጨማሪ አዲስ ዓይነት ትንኝ መስፋፋትና የትንኞች ዘረ መል ባህሪ መለዋወጥ እንዲሁም የመከላከልና የሕክምና ሥራዎች በተለያየ ምክንያት በየወቅቱ አለመከናወናቸው፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም የነበሩ የፀጥታ ችግሮችና የማኅረበሰቡ የመከላከል ሥራዎች መቀዛቀዝ ለበሽታው መስፋፋት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም በ2014 ዓ.ም. እና 2015 ዓ.ም. ከ17 ሚሊዮን በላይ አጎበሮች ለየወረዳዎች መሠራጨታቸውን፣ 1.2 ሚሊዮን ቤቶች በፀረ ወባ ኬሚካል መረጨታቸውን፣ በሰባት ክልሎች በሚገኙ 565 ወረዳዎች የወባ በሽታን ለማስወገድ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አክለዋል፡፡
እንደ ሊያ (ዶ/ር)፣ የ2015 በጀት ዓመት የጤናውን ዘርፍ ዕቅድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊ እንቅስቃሴ ቢደረግም፣ በየአካባቢው የግጭቶች መከሰትና መቀጠል፣ ሌሎችም ተፈጥሯዊ የሆኑት እንደ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ፣ የተለያዩ ወርርሽኞች መከሰት ፈተና ሆነዋል፡፡
ዕድሜያቸው ከ37 እስከ 49 ዓመት ለሆናቸው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሴቶች የቅድመ የማኅፀን በር ካንሰር ምርመራ በመስጠት ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት መገኘቱን፣ ይህም ሊሆን የቻለው የካንሰር ሕክምና የሚሰጡ ተቋማትን ወደ 1,030 ከፍ እንዲል በመደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዕምሮ ጤና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋት በተሠራው ሥራ በአሁኑ ሰዓት ከ70 በመቶ በላይ በሚሆኑ ሆስፒታሎች የአዕምሮ ጤና፣ በ13 የመንግሥት ጤና ተቋማት ደግሞ የሱስ ሕክምና አገልግሎቶች እየተሰጡ እንደሚገኙም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ‹‹መንግሥት ጤናማ ዜጋ ለማኅበረሰብ መሠረት መሆኑን በመገንዘብ በሁሉም ለሁሉም ተደራሽ፣ ተመጣጣኝና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት የሚሰጥ የጤና ሥርዓት መገንባት ቀዳሚ ዓላማው ነው፤›› ብለዋል፡፡
በዚህም የተነሳ የጤና መሠረተ ልማትንና የጤና መድን ሽፋንን ለማስፋፋት፣ የአቅርቦት ሰንሰለትን ለማሻሻል፣ የጤና ባለሙያዎችን ለማሠልጠንና የማኅበረሰቡን የጤና መርሐ ግብሮች ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ወደ ተግባር ከተገባ ብዙ ጊዜ እንደሆነው ተናግረዋል፡፡
ለዚህም እንደ ማሳያ ሕፃናት ጤናማ ዕድገት እንዲኖራቸውና ምርታማና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ለማድረግ የቀዳማይ ልጅነት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ እየተተገበረ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ይህንን የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ከትምህርት፣ ከጤናና ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን ገልጸው፣ በከተማና ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ለመርሐ ግብሩ ትግበራ፣ ለንድፈ ሐሳብ፣ ለጥናትና ለምርምርና አቅም ግንባታ ዘርፉ ጠቃሚ ሚና መጫወት የሚችል የልህቀት ማዕከልን ወደ ማደራጀት ተግባር ለመግባት እየታሰበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ስምንት ጤና ጣቢያዎች፣ ሁለት አዳዲስ ጠቅላላ ሆስፒታሎች ተገንብተዋል፣ ሁለት ሆስፒታሎችን የማስፋፋትና መልሶ የማልማት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛሉ ያሉት ከንቲባዋ፣ በአምስት ሆስፒታሎችና በሁለት ጤና ጣቢያዎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ ዕውን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን ከመፍጠር ባሻገር በ19 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መጀመሩን የገለጹት ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙሉጌታ እንዳለ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
እንደ ሙሉጌታ (ዶ/ር) የጤና አገልግሎትን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ባለፉት ዓመታት የሦስት ጤና ጣቢያዎችን የሰው ኃይልና ግብዓት የማሟላት እንዲሁም የ28 ጤና ጣቢያዎችን የማስፋፋትና የግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
በተለይ በዳግማዊ ምኒልክ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚገኘው የዓይን ባንክን በአዲስ መልክ በመገንባት በዘመናዊ መንገድ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በዚሁ ሆስፒታል 35 የኩላሊት እጥበት ማሽኖችን የመያዝ አቅም ያለው ማዕከል ተገንብቶ ኅበረተሰቡ የአገልግሎቱን ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
የነፍሰ ጡር እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል፣ የወሊድና የድኅረ ወሊድ አገልግሎትና የሕፃናት ክትባት ተደራሽነት፣ የሕክምና ዕድገትና ክትትል በመሻሻላቸው፣ የእናቶችና የሕፃናት ሞት ምጣኔ በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተናግረዋል፡፡፡
በአሁኑ ጊዜ 221,338 አባወራዎችና እማዎራዎች ወይም ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የማኅበራዊ ጤና መድን ወይም አባላት እንዲሆኑ፣ ከእነዚም መካከል ከ73,000 በላይ የሚሆኑና የጤና መድን ሽፋን መክፈል የማይችሉ የከተማው አስተዳደር እየከፈለላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን፣ ለከፋይ አባላትም 50 ከመቶ ያህሉን ክፍያ እንደሸፈነላቸው ገልጸዋል፡፡
በኃይሌ ግራንድ ሆቴል በተከናወነውና መድረክ፣ በጤናው ዘርፍ በሕይወት ዘመን አገልግሎት የላቀ የሙያ አገልግሎት፣ በጤና ሙያ መስክ ልዩ አስተዋጽኦ እንዲሁም በሥራ አመራር ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ 14 የጤና ባለሙያዎች የዕውቅና ምስክር ወረቀትና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
