
Byአንባቢ
November 5, 2023
በተመስገን ታረቀኝ ካሳ
ማንም ሰው እስከ እዚህ ዘመን ድረስ ሲወለድ አገር አለው። ይህ አገሬ የሚለው ትርጓሜ እንደ አገሮች የሚለያይ ሲሆን፣ በአብዛኛው ወደ እዚህች ዓለም የመጡበት ቦታ በአባቶች ብሒል ‹‹እትብቱ የተቀበረበት›› አገሩ እንደሆነ ይታሰባል። ሆኖም ግን መውለድም ይሁን መወለድ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከቦታ ወደ ቦታ በሚደረጉ ዝውውሮች እንዲሁም፣ ጉዞዎች የሚከሰቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ በስደት ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በመሸጋገር ለተሻለ ኢኮኖሚ በትምህርትም ይሁን በቅጥር ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር በመዘዋወር፣ አገሮች ለዜጎቻቸው በውጭ አገሮች በሚሰጡት ኃላፊነት፣ በፖለቲካ ጥገኝነት ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በመሻገር፣ በቱሪስት ጉዞ ላይ በሚፈጠር ክስተት፣ አገሮች የሌላ አገር ሕዝቦች ገብተው እንዲኖሩ በሚሰጡት ፈቃድና በተዋጊነት በሚገጥም ሁኔታ የሚፈጠር ይሆናል። በዚያም ይሁን በዚህ ሥረ መሠረቱ አገሬ ብሎ በሚያምንበትና በተሰጠው ዕውቅና አገር የሚለው ትርጉም የሚደመደም ይሆናል። ነገር ግን አገር የሚለው ዕሳቤ መንግሥት፣ ወይም ቤተሰብ፣ ወይም ማኅበረሰብ፣ በሰጠው ምስክርነት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም። እያንዳንዱ ሰው በራሱ ሥነ ልቦናም የሚቀርፀውም ጭምር ነው።
ስለአገር ይህን ያህል ካልን ማንም ሰው እንደ ግል ወይም እንደ ቡድን ወይም እንደ ሕዝብ አገሬ ብሎ ለሚያምንበት ይቆረቆራል። ለመቆርቆሩ መነሻ መሠረት የሚሆነው ስለአገሩ የማኅበረሰብ ክብር፣ ስለአገሩ ሉዓላዊነት፣ ስለአገሩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ሀብት፣ ስለሕዝቡ ሰብዕና፣ ስለአገሩ ዕድገትና የጥበብ ደረጃ፣ አገሩ ከሌሎች አገሮች ጋር ስላለው መስተጋብር፣ ስለአገሩ ፖለቲካ፣ ስለአገሩ ባህል፣ ስለአገሩ ፍትሕ፣ ስለአገሩ ሥነ መንግሥት፣ ስለአገሩ የሀብት ክፍፍል፣ በአገሩ ስላለው እኩልነትና ነፃነት፣ ስለአገሩ መሠረተ ልማት፣ ስለአገሩ ሕዝብ እምነት፣ ወዘተ. መቆርቆር ይኖራል። በዚህ ሁኔታም ቢሆን አገርን ሽፋን አድርገው ለግል ጥቅማቸውና በድብቅ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የሸፍጥ ምግባር የሚያራምዱ እንዳሉ ልንገነዘብ ይገባል። እነዚህ የሸፍጥ ተልዕኮ አራማጆች ሳያውቁ ወይም ሳይረዱ ወይም ለጥቅምና ለሥልጣን ናፋቂ በመሆን የሚፈጽሙት ተግባር ነው።
የሸር ተልዕኮ አስፈጻሚዎች አገራቸውን አሳልፈው ለክፉ ምግባር የሚሰጡ ይሆናሉ። ለአገር ተቆርቋሪነት ሕይወትን አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርስ ነው። አገር አርግዛ የወለደች እናትም ተደርጋ ትቆጠራለች። አገር ሁሉን አዘጋጅታ እንደምትመግብ ወላጅም ትቆጠራለች። አገር ምግብ አዘጋጅታ እንደምታጎርስም እናት ትቆጠራለች። ስለአገር በሚኖር የተለያዩ ሁኔታዎች ስናነሳ በፆታ ወክለን እንናገራለን። የአገር ፆታን በሚመለከት ከአገር ወደ አገር ይለያያል። አንዳንድ አገሮች አገራቸውን በወንድ ፆታ ይመስላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሴት ፆታ ይመስላሉ። ምክንያቱም እንደ አገሮች ይለያያል። የኢትዮጵያን ብናይ በጽሑፍ የተቀመጠ ምክንያት ያለ ባይሆንም፣ በተዛምዶ የተወሰኑ ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ በሴት ስትመሰል ሴቶች ልጆች በማኅፀናቸው የሚፈጠሩባቸው ሲሆን፣ ለአቅመ መወለድ እስኪደርሱም ከደማቸው ልጆችን መግበው የሚያቆዩ በመሆናቸው ሲሆን፣ ልጆች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ምግብ መመገብ እስከሚጀምሩ ጡታቸውን አጥብተው እንዲሁም፣ ለልጆች በሚያስፈልገው ዓይነትና ልክ እንክብካቤ ስለሚያደርጉ ከዚህ አፈጣጠርና ቁርኝት ጋር በማዛመድ አገራችንን በእናትና በሴት ፆታ እንመስላለን። እናት ለልጇ ማድረግ ያለባትን ሁሉ እንደምታደርገው አገርም እንዲሁ ታደርጋለች የሚል ተምሳሌት ለመግለጽ ነው። እናት ልጇን አትበድልም፣ አገርም እንዲሁ አትበድልም ለማለት ነው በሴት ፆታ የተመሰለችው።
ሌላው ኢትዮጵያ በሴት ፆታ የተመሰለችው እናት አምጣ (እንደዚህ ዘመን ሳይሆን) ልጅ ትወልዳለች። ከእነ ብሒሉም ‹‹ምጡን እርሽው፣ ልጁን አንሺው›› እንደሚባለው የምጡን ሥቃይና ፈተና በጊዜው እጅግ የከፋ ቢሆንም አልፏልና መልካሙን ብቻ እናስብ የሚል መልዕክት ያለው ብሒል ነው። ኢትዮጵያም የሰው ዘር ተፈጥሮባታል። ብዙ መከራና ሥቃይንም ዓይታ ይህንን የሰው ዘር ከዘመን ዘመን አሻግራ ለዚህ ዘመን አድርሳለች ለማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሴት ብልህ ነች። እናም የኢትዮጵያ ልጆች ብልኃት ያላቸው ናቸው ለማለት ነው። ሴት አገርን መምራት ትችላለች። ለዚህም ንግሥት ሳባና ዮዲትን እንደ ምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም ለሴቶች የመሪነት ብቃት መኖርን ለማመላከት ሲባል ነው ኢትዮጵያ በሴት ፆታ የተመሰለችው። ኢትዮጵያን በሴት ፆታ ለመሰየም ምክንያቶች እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። ከተለያዩ አተያዮችና ዕሳቤዎች ሌሎችንም ማለት ይቻላል።
ሰው ለአገሩ ቀናይ መሆን አለበት። በዚህ መነሻነትም የጆን ኤፍ ኬኔዲን አባባል መጥቀስ ይቻላል። ‹‹እኔ ለአገሬ ምን አደረኩኝ? እንጂ አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ? ማለት የለብንም፤›› ብሏል። ከዚህ አባባል መነሻነት አገሩ ምንም ያላደረገችለት ሰው እንዳለ መልዕክቱ የሚያስረዳው አለ። አገሩ ምንም ያላደረገችለት ሰው ሊኖር አይችልም። አገሬ ምንም አላደረገችልኝም የሚል ሰው ካለ እናቴ ለእኔ ምንም አላደረገችልኝም ብሎ እንደመናገር ይቆጠራል። እጅግ ቢያንስ እናት በሕይወት እስከምንወለድ ድረስ ደሟን አጋርታ መግባ የጭንቅ ምጧን አምጣ ወልዳናለች። ይህ ባይሆን ኖሮ ሰው ሆነን በሕይወት ወደ እዚህች ምድር ባልመጣን ነበር። በመሆኑም ምንም ያላደረገች እናት እንደሌለች ሁሉ ምንም ያላደረገች አገርም አትኖርም። እናት በእርግዝናዋ ወቅት ከአገሪቱ ያገኘችውን ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ሰጥታና ተሸክማ አኑራለች። ሳትበላ፣ ሳትጠጣ፣ ሳትተነፍስ፣ ሳትለብስና በመሬት ላይ እንደ ሁኔታዎች ጎጆ ሳይኖራት አርግዛ የምትወልድ እናት የለችም። የሚበላውን፣ የሚጠጣውን፣ የሚተነፈሰውን፣ የሚለበሰውንና የሚኖርበትን ያቀረበች አገር ናት። ስንወለድም እጇን ዘርግታ የተቀበለችውና የተረከበችው አገር ናት። ይህ የአገር ስጦታ እጅግ በትንሹ ስንጠቃቅሰው ነው እንጂ የአገር ስጦታ ከዚህም ያለፈ ነው።
ውቅያኖስን በማንኪያ ከመጨለፍ ከሚቆጠር የአገር አበርክቶ ባለፈ ብዙ ብዙ ነገሮችን አገር ለልጆቿ አድርጋለች፣ ታደርጋለችም። ይህም በመሆኑ አገር ያላደረገችው ምንም ነገር የለም። ሰዎች አገራቸውን ለመክዳት ሰበብ አስባብ ለመደርደር ካልሆነ በስተቀር አገር ብዙ አድርጋለች። እናት ልጇን ለአቅመ ሥራና ራስን ለመደገፍ ከሚችልበት አቅም እስከሚደርስ እናት ከራሷ አስቀድማ ለልጇ ዋጋ ትከፍላለች። ለአቅመ ሥራና ራስን በምንችልበት ጊዜ እናታችንን በመክዳት ምንም አላደረግሽልኝምና ምንም ላደርግልሽ አልችልም ማለት የክህደት ጥግ ነው። ይህ ዓይነቱ ክህደት በእጅጉ የሚያዋርድ ራስ ወዳድነት ይሆናል። አገርን ምን አድርጋልኝ እኔ ምን ላደርግላት ትጠብቃለች? የምንል ከሆነ እንዲሁ ክህደት ነው የሚሆነው። ይሉንታ ቢስ ነው የምንሆነው። እናትን መርዳት ልጅ ከሚያገኘው የሚተርፍ ነገር ሲኖረው ከሆነ ይህም ስግብግብነት ነው። ለአገርም ሲሆን እንዲሁ ለእናታችን ካገኘነው በማካፈል የምንረዳ ከሆነ ለአገርም እንዲሁ ሊሆን ይገባል።
ለአገር ሳይተርፈን የምንሰጥ፣ እየደከመንና እየታከተንም የምንሠራ፣ ቢጎልብንም አገር እንዲሞላላት የምንተጋ፣ ቢያስፈልገንም ከእኔ ይቅር ብለን ለአገር የምናሳልፍ፣ እንዲሁም ብትደፈር ለሕይወታችን ሳንሳሳ መስዋዕት የምንሆን የአገር ልጆች ልንሆን ይገባል። ለአገር የምንሠራው ለልጅና የልጅ ልጆቻችን ከዚህም ባለፈ ስለሚሆን ሳንለግም፣ ጥቅም ሳይገዛን፣ ሥልጣን ዓይናችንን ሳይጋርደንና በዕውቅና ትዕቢት ሳንመረዝ ዝቅ ብለን በመሥራት ከፍ ብለን ትውልድን ማላቅ አለብን። አገር ከትውልድ የምንረከባት ምድራችን ከአባቶች በአደራ የተላለፈችልን የህሊናና የሞራል ተገዥነታችንን የምናስመሰክርበት ሰው የመሆናችን መገለጫ ነው። ሰው የመሆን ስንል ሰብዕና ያለውን ሰው ማለት እንጂ ሰብዕናን አሽቀንጥሮ በመጣል ከእንስሳም በወረደ አስተሳሰብና ድርጊት የተጠመደ ማለት አይደለም። ሰብዕና ስንልም ስግብግብነት ያልረታው እኔ ሳይሆን እኛ የሚለውን የሚያስቀድም መብላትን ብቻ ያለመ ሳይሆን ማብላትንና ግብረ ገባዊነትን የተካነ ማለት ነው። ሰብዕና ጭንቅላቱ በአሉታዊ ሳይሆን በአዎንታዊ የሞላው፣ በጎነትን የተላበሰ፣ እንዲሁም ሌሎችን በመርዳት የሚረካ ማለት ነው። ፈሪኃ ፈጣሪ ያለውና ነገን አሻግሮ በማማተር ገና ለሚመጣው ትውልድ መሸጋገሪያ ድልድይ የሚሠራ ነው።
ሰብዕናና መልካምነት የተዋሃደው የበጎ ሥራዎች መገለጫ ነው። ሰብዕና ለሰዎች ፍቅር አለኝታ መሆን ነው። ሰብዕና ለፍትሕና እኩልነት ዋስ ጠበቃ መሆን ማለት ነው። አገርም በሰብዕና የተቃኙ ሰዎች የሚኖሩባት መሆን አለባት። አገርንም ሰብዕና በተሞላበት መንገድ ልንጠብቅ እንዲሁም ልንገነባ ያስፈልገናል። አገር የግል አይደለችም የጋራ እንጂ። በጋራ ስለአገር ብለን ስንሠራም ይሁን አገርን ስንጠብቅ የሚያግባባን እንጂ የሚለያየን አይኖርም። ምክንያቱ የጋራ ኃላፊነታችንን ለጋራ ተጠቃሚነት የምናውለው ከሆነ ለምን እንለያያለን? በጋራ መልካም ነገር ለማግኘት ምን ያጣላናል? ምንስ ይለያየናል? መልካም የሚባለው ምንድነው? የሚለው አተያይና አረዳድ ላይ ልዩነት ካለን የልዩነታችን መንስዔ የሚሆነው አዎንታዊና አሉታዊ ዕሳቤዎች ሲናኙብን የምንሰጠው ትርጓሜና ምግባር ነው። የአዎንታዊ ሐሳቦቻችንና ድርጊቶቻችን ከማስተዋል፣ ከህሊና ተገዥነትና ከፈሪኃ ፈጣሪ የሚመነጩ ሲሆን፣ የአሉታዊ ምግባራችን መገለጫዎች ደግሞ እንደ አብነት እንጥቀስ ካልን ማር ይመራል፣ ወተት ለምንም አይጠቅምም፣ ማካፈል ኃጢያት ነው፣ ሌብነት ጀግንነት ነው፣ ማታለል ብልኃት ነው፣ ዋልጌነት ብልጠት ነው፣ መመቅኘት የትጋት ማነቃቂያ መንገድ ነው፣ ዘረፋ የሀብት ማፍሪያ አቋራጭ መንገድ ነው፣ ወዘተ. እያልን አሉታዊ ዕሳቤዎቻችንን በምናስተናግድበት ሁኔታ የሚፈጠር ዕሳቤና ተከትሎም የሚመጣ ድርጊት ነው።
የአሉታዊ አስተሳሰብ ውጤቶች ለብቻዬ ልኑር፣ ለብቻዬ ልደግ፣ ለብቻዬ ከፍ ከፍ ልበል፣ ወዘተ. የብቸኝነትና የእኔ ብቻ ይሁን የሚል የዛር መንፈስና የመስገብገብ በሽታ ሲጠናወተን ነው የምናልመውም የምንተገብረውም። በጋራ መኖር ተፈጥሯዊ አስገዳጅ ሁኔታ ሆኖ ግለኞችና ስግብግቦች የጠባብ ተጠቃሚነትንና አጥር አጥሮ ለብቻ መኖርን የሚሹ ይሆናሉ። አጥሩ ያረፈበትን እንኳን የጋራ መሆኑን አይቀበሉም። ትረካቸውም ይሁን ትርክታቸው መነጠልን ማዕከል ያደረገ ነው። መነጠል ደግሞ አይደለም በሕይወት እያለን ስንሞትም ተግባራዊ አይሆንም። ተነጥሎ የተወለደ የለም። ተነጥሎ የሚሞትም የለም። ሁለመናችን የጋራና የወል ነው። ከአፈጣጠራችን እስከ አሟሟታችን የጋራና የወል የሆነውን ተፈጥሯችንን ለመለያየት ስንጥር ተፈጥሮን የካድን መሆኑን እንኳን ማስተዋል ይሳነናል። እኔን በእኛ መተካት ካቃተን ለግላችንም ይሁን ለኅብረታችን ፈውስ የሌለው በሽታ እንሆናለን፣ እኔነትንም እንጎዳለን። ለእኛነትም መሰናክሎች እንሆናለን። በአገር ደረጃም መለያየቱ የሚመጣው ከዚህ መነሻነት ነው። በግል እንታወራለን፣ በጋራ ጉዳይ እንቅፋቶች እንሆናለን። እኔ ብቻ ካልበላሁ ይውደም ዓይነት የተበላሸ የአስተሳሰብ በሽታ ‹‹ካልበላሁት ጭሬ እደፋለሁ›› አለች ዶሮ እንደሚባለው የአስተሳሰብ ስንኩሎች እንሆናለን። በጋራ ለምንጠቀምበት በጋራ ተግተን ከሠራን ስለምን በልዩነት ጎራ እንሠለፋለን? የልዩነት ጎራ ሌላው መገለጫው ያልኩት ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ የሚል ዕሳቤ ነው።
አንዳንድ ሰዎች የአስተሳሰብ እስረኛ የሚሆኑ አሉ። አስተሳሰብ ሐሳብ እንጂ የድርጊት ውጤት አይደለም። ገና ወደ ድርጊት ሳይገባ በሐሳብ ብቻ ራሳቸውን ጠፍንገው የሚያሠሩ አሉ። አንድ የዚህ ዓይነት ምሳሌ እናንሳ፡፡ ባልና ሚስት ገና ልጅ አልወለዱም ሁለቱም ለመውለድ ይጓጓሉ። መውለድ መቻላቸውን እርግጠኛ አይደሉም። አባት ሴት ልጅ ቢወልድ ምኞቱ ነበር። እናት ደግሞ ወንድ ልጅ ብትወልድ ምኞቷ ነበር። ሁለቱም ግን የሐሳብ እስረኞች ነበሩ። በአልጋ ላይም አይስማሙም። የፈጣሪ ፈቃድ ሆነና ሴት ልጅ ተወለደችላቸው። ሰውን ከሰው ለመለየት ስም ያስፈልጋልና ስም መውጣት ነበረበት። እኔ ስም ማውጣት አለብኝ እኔ ማውጣት አለብኝ በሚል መግባባት ላይ መድረስ አልቻሉም። ሁለቱም ስም የማውጣት ድርሻቸውን በምክንያት ለማስረዳት ታተሩ። እናት የተመኘኸው ሴት ልጅ ስለነበር ሴት ልጅ አግኝተናል፣ እኔ ወንድ የፈለግኩኝ ቢሆንም ሴት ስለሆነች ቢያንስ ቢያንስ ስም የማውጣት ድርሻ ለእኔ ይገባል አለች። አባት ደግሞ እርግጥ ነው ሴት ልጅ እንዳገኝ እመኝም እጓጓም ነበር አግኝቻለሁ።
በአገራችን ባህል ስም የማውጣት የወንድ ድርሻ ስለሆነ ስምም የማወጣት መብት የእኔ መሆን አለበት አለ።
እናትም ሁሉን ጠቅልለህ ለምን ለራስህ ብቻ ማድረግ ትፈልጋለህ? ባህል ሌላ መሆን ሌላ ነውና የአገራችን ባህል የሚባለውን ተወውና ቢያንስ ቢያንስ በእርግዝና የተሰቃየሁትን ቦታ ሰጥተኸው ስም እንዳወጣ እንኳን የእኔ ድርሻ ይሁን ትላለች። ባል የአገሬንማ ባህል አልተውም፣ እኔነቴን አስተካክሎ ሳልጎብጥ አርቆ ያሳደገኝ ባህሌ ነውና አልተወውም ይላል። ሚስትም ባህል እኮ ጎጂም አለና ጎጂ ባህልንም ይዘህ መኖር አለብህ ማለት ነው ትለዋለች። ባል ይኼኛው ባህሌ ጎጂ ስላልሆነ አይደለም እኔ ለልጄም አወርሳለሁ ይላል። የሴቶችን መብት ዕውቅና ባለመስጠቱ ይኼ ባህልማ ጎጂ ነው ትላለች። የሴቶችን መብት እምኑ ጋ ነው የጎዳው? እኔ የጎዳ መሆኑ አልታየኝም ይላል ባል። ሚስት በተራዋ ሴት ስም አታወጣም በማለቱ የሴቶችን መብት የጨፈለቀ ነው ትላለች። ምንም ስህተት የለበትም አለ ባል። ምክንያቱም አለ ባል ልጅህ ናት ስላልሽኝ አምኜ ተቀበልኩሽ እንጂ የሌላ ብትሆንስ ምን ማረጋገጫ አለኝ። አባትነት እምነት እናትነት ግን እውነት ነው ይላል። የቀደምት ቅድመ አያቶቻችን ብሒል ስለሆነም እኔ ሳምንሽ አንቺ ደግሞ ስም እንዳወጣ መፍቀድ ይኖርብሻል አላት። እንዴ አታምነኝም ማለት ነው? እንዴት አታምነኝም? ሳታምነኝ ነበር ይህንን ያህል ጊዜ ባልና ሚስት ሆነን የኖርነው? ሚስት ያዙኝ ልቀቁኝ አለች። ባልም እንደ እጮኛ ሳውቅሽ እኮ ድንግል ሆነሽ አላገኘሁሽም። በልጅነትሽ ለራስሽ ያልታመንሽ እንዴት እኔ ልመንሽ ይላታል። ያኔማ በስህተት የተፈጸመ ነበር ትለዋለች። ባልም ሰው መቼ ነው ሳይሳሳት ፍፁም ሆኖ የሚኖረው ይላታል። አሁን ዕድሜ ላይ እኮ ማመዛዘን የምንችልበት ዕድሜ ላይ ደርሰናል ትለዋለች። የቱ አመዛዛኝ ሰው ነው ከስህተት ንፁህ በመሆን ፍፁም የሆነው ይላል ባል። አንተ እንደሆንክ ሙዝዝ ጥምዝዝ ማለት ትወዳለህ ትላለች ሚስት። በምነግርህ ብቻ እመነኝ ማለትሽ ምንም አማራጭ የለኝም አምኜሽ እየኖርን ነው። ከዚህ ባለፈ ግን ቃልሽን ፍፁም አድርጎ ማሰብ ሰው ሁሉ ከኃጢያት ነፃ ነው ብሎ ማሰብ ይሆናል ይላል ባል። ይህም ሐሳብ ምንም በልቧ ጠብ አላለም ሚስት። ባልም ነገርን ነገር ይቆሰቁሰዋልና ልቡ የሻከረበት ወንድ ነበርና እከሌን እጠረጥረዋለሁ ሲል ነገሩ እየከረረ መጣ። ወደ ጠብና ድብድብ ሲቀየር ባል ሚስትን ሊደበድብ ሲሰነዝር በልጁ አይጨክንም ብላ በሕፃን ልጇ ስትከለል ለሚስት የተሰነዘረው ለሕፃኗ ሆኖ በዚህ ሁኔታ የሕፃኗ ሕይወት ያልፋል። ሁለቱም በጉጉት ያገኟትን ልጅ አጡ።
ከዚህ የምንረዳው ለጋራ ጥቅማችን የየግል ሐሳባችንን አገንትረን የሚጠቅመንን ሁሉ በተራ ጉዳዮች መልሰን የማናገኘውንም ጭምር እንድናጣ ያደርገናል። በየኔ ይሁን የእኔ ይሁን አጉል ግትርነትና እልኸኝነት የሰበሰብነውንም እንበትናለን። የሚያስፈልገንንም እንዳናገኘው በሩን እንከረችማለን። ግልጽ መሆንም ከባድ ሸክም ይሆንብናል። መተማመን ለመፍጠርም የምናደርገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ግልጸኛ አለመሆናችንና መተማመን ለመፍጠር ጥረት ባለማድረጋችን ብዙ ዋጋ እንድንከፍል ያደርገናል። የጋራ ተጠቃሚነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በየግላችን የምናስበውና የምንተገብረው በምንጓዝበት መንገድ የተቃርኖ እያደረግነው የጥረታችንን የድምር ውጤት/ሪዛልታንት ፎርስ አልቦ እናደርገዋለን። ምክንያታዊነትና አመክኖ እንፈራለን። ሐሳባችንን የሚያመክኑብን ይመስለናል። በንግግር ብቃት ያለመኖር እንደምክንያት እያሳበብን አሳማኝ ጭብጥ ስናጣ ሐሳባችንን በኃይል ብቻ መጫንን እንፈልጋለን። ይህ ባይሆን እንኳን ምክንያታዊና አመክኗዊ ሐሳቦችን የብልጣ ብልጦችና አፈጮሌዎች በማለት እናጣጥለዋለን።
የአገር ጉዳይ የጋራ ጉዳይ እስከሆነ ዘንዳ ተቆርቋሪነታችን እጅግ የተራራቀ ልዩነት ሊኖረው አይገባም። የሐሳባችን ባዘቶ ይገንና ለታዋቂነትና ዕውቅና ወይም ለስግብግብ ጥቅመኝነት እጅ ስንሰጥ ለአገር መቆርቆር መሆኑ ቀርቶ ሽፋኑን በመጠቀም የምንሸቅጥበት ይሆናል። ለአገር መቆርቆርና ለግል መስገብገብ የማይጣጣሙና የማይገናኙ ተፃራሪ ሐሳቦች ናቸው። መቆርቆር ከሆነ ግን ልጆች ለእናታቸው ምን እናልብሳት በሚል የሐሳብ ልዩነት ቢፈጠር የአቅምና የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በሚያስፈልገው ልብስ የተለያየ አተያይ ቢኖርም እንኳን ማልበስ በሚለው ግን ልዩነት ሊኖር አይገባም። የታረዘች እናትን ልብስ አያስፈልጋትም የሚል ልጅ ካለ ለእናቱ የማይሆን መሆኑን ያረጋገጠ ከኃዲ ነው ማለት ይቻላል። በማልበስ ከስምምነት ላይ ተደርሶ የልብስ ዓይነት፣ ቀለም፣ ብዛት፣ ዋጋው፣ ጊዜው፣ ወዘተ. መለያየቶች አይኖሩም ማለት አይደለም፣ እንደሚኖሩም ይጠበቃል። ቁምነገሩ ለታረዘችው እናት ቀድሞ የደረሰው የሚመሠገን ሆኖ ሌሎችም እንደ ልጆች አቅምና ፍላጎት በተለያዩ ጊዜያት ለእናት ቢበረከቱ ክፋት የሚኖረው አይሆንም። እናትም ከአንድ ወደ ብዙ አማራጮች አልባሳት ይኖራታል።
በአገር ጉዳይም ልናደርግ የሚገባንን በማከናወናችን በየትኛውም ባለአገር በክፉና በክፋት ሊወሰድ አይገባም። የተለያየ ነገር በተለያየ መንገድ ለአገራችን ብናደርግ የመልካምነት እንጂ በጎጂነት ሊታሰብ አይገባም። ነገር ግን ለታረዘች እናታችን ያለበስናት ልብስ ለበሽታና ተውሳክ አጋላጭ ከሆነ ለመጥቀም ያደረግነው ጎጂ ይሆናል። ለአገርም እንዲሁ። በመሆኑም ስለምናደርገው ነገር ሁሉ ጥንቁቅ፣ አስተዋይና አመዛዛኝ ልንሆን ይገባናል።
አገራችንንና ሕዝባችንን ሰላም ያድርግልን!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው temesgen1959@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
