
ከ 6 ሰአት በፊት
ካሊድ ኢል ኢስታል አየርላንድ ቤልፋስት ውስጥ ነው የተወለደው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም እዚያ ነው የተማረው።
ባለቤቱ እና ሌሎች ቤተቦቹ በጋዛ መገደላቸውን ተከትሎ አሁን ወደ አየርላንድ ተምልሷል።
ካሊድ 30 ዓመቱ ነው። ቤተሰቦቹ ጋዛ ሳሉ እሱ በሥራ አጋጣሚ በሳዑዲ አረቢያ ነበር።
ድንገት በጋዛ ሁሉ ነገር ተቀየረ። እስራኤል ጋዛን በቦምብ ቀን ተሌት መደብደብ ጀመረች። ካሊድም ሕይወቴ የሚላትን ባለቤቱን አጣ።
ካሊድ “አሁን ሁሉን ነገሬን አጥቻለሁ” ይላል። ቀሪ ሕይወቱን አሁን ለጊዜው የተረፉለትን ሁለት ልጆቹን ወደ አየርላንድ ዋና ከተማ ደብሊን በሰላም በማምጣት ማኖር ይሻል።
ሁለቱ ልጆቹ ግን በሕይወት ከጋዛ ይወጣሉ ወይ የሚለው ካሊድን ያስጨንቀዋል። የእናታቸው ዕጣ እንዳይደርስባቸው ይፈራል።
“ከጋዛ እንዲወጡ እሻለሁ፤ መንግሥት አንድ ነገር ሊያደርግ ይገባል። ሁለቱም ልጆቼ አየርላንድ ዜጎች ናቸው” ይላል።
አሁን ጋዛ የቀሩት አንድ ዓመት እና 4 ዓመት የሆናቸው ልጆቹ ናቸው። እዚያ ከአያቶቻቸው ጋ ነው ያሉት።
የአየርላንድ ባለሥልጣናት አስቸኳይ ድጋፍ ካላደረጉለት ልጆቹ በሕይወት ከጋዛ ይወጣሉ ብሎ እንደማያምን ካሊድ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።
- የአረብ አገራት በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሲጠይቁ አሜሪካ ተቃወመቸ5 ህዳር 2023
- አሜሪካ በጋዛ ሰማይ ድሮን ለቅኝት መላኳን አመነች5 ህዳር 2023
- ዜሌንስኪ፡ ‘’የጋዛ ጦርነት የዓለም ትኩረት ከዩክሬን እንዲነሳ አድርጓል’’5 ህዳር 2023

“እሷ ማለት ሕይወቴ ነበረች”
ካሊድ በሰሜን አየርላንድ፣ ቤልፋስ ከተማ ተወልዶ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱንም በዚያ ነው ያጠናቀቀው። አባቱ በኩዊንስ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው።
ስምንት ዓመት ሲሆነው ቤተሰቡ መኖሪያውን ጋዛ አደረገ። ካሊድም አብሮ ሄደ።
ዩኒቨርስቲ ሲገባ የወደፊት ባለቤቱን በዚያው በጋዛ ተዋወቀ። አሽዋቅ ጀንዲያ ትባላለች።
“እሷ ማለት ሕይወቴ ነበረች” ይላል ካሊድ ደጋግሞ።
ከሳምንታት በፊት እሰራኤል በጋዛ ላይ ጥቃት ስትጀምር ካሊድ ባለቤቱን ወደ ደቡባዊ ጋዛ በፍጥነት እንድትሄድ እና ከእርሱ ዘመዶቹ ዘንድ እንድትቆይ አሳሰባት።
እሱ እስከዚያ የአይሪሽ ባለሥልጣናትን መጎትጎት ጀመረ። በሰላም ከጋዛ ሊወጡ የሚችሉበትን ሁኔታ ባለሥልጣናቱ እንዲያመቻቹለት ነው የጠየቀው።
ባለቤቱ ምክሩን ተቀብላ ወደ ደቡባዊ ጋዛ ተጓዘች። ልክ ወደእርሱ ቤተሰቦች ዘንድ ስትደርስ አሳዛኝ ሁኔታ ተከሰተ።
“እሷ እዚያ በደረሰች ቅጽበት እስራኤል አካባቢውን በቦምብ መደብደብ ጀመረች።”
የቦምቡ ጥቃቱ እናቱን እና ወንድሙን ወዲያው ገደላቸው።
ቀጥሎ በሌላ ጥቃት አጎቱ እና የአጎቱ ሁለት ልጆች ተገደሉ። ሁለቱም ሐኪሞች ነበሩ።
ሁለቱ የካሊድ ልጆች ከፍርስራሽ ውስጥ ተገኙ።
ባለቤቱ አሽዋቅ ወዲያው ወደ ሆስፒታል ተወሰደች። 60 ከመቶ ሰውነቷ ተቃጥሎ ስለነበረ ወዲያው ሕይወቷ አለፈ።
“ሐዘኑ እየገደለኝ ነው፤ እኔ እንዲያውም የተሻልኩ ሳልሆን አልቀርም። በጋዛ ሁሉም ከእኔ በባሰ ቤተሰቡን አጥቷል” ይላል ካሊድ።
አሁን የተረፉለትን ሁለቱን ልጆቹን ስለ እናታቸው ምን እንደሚላቸው ግራ ገብቶታል። ምን ብሎ እንዴትስ አድርጎ ያስረዳቸዋል?
እሰራኤል ጋዛን መደብደብ የጀመረችው ሐማስ በመብረቃዊ ጥቃት 1400 ዜጎቿን ገድሎ፣ ከ240 በላይ የሚሆኑትን ካገተ በኋላ ነው።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው እስከ አሁን ከ9ሺህ በላይ ሰዎች ጋዛ ውስጥ በተፈጸሙ የእስራኤል ጥቃቶች ተገድለዋል።
የአየርላንድ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንደሚለው ከ8ሺህ የሚበልጡ ጥምር ዜግነት ያላቸው ሰዎች አሁን በጋዛ ይገኛሉ።
ይሁንና እነዚህን ሁሉ ከጋዛ ለማስወጣት ረዘም ያለ ጊዜ ይፈልጋል።
“ጊዜ? ጊዜ ይፈልጋል አሉ? ጊዜ ከፈለገማ ሞቱ ማለት ነው። ባለቤቴ የሞተችው እኮ በ5 ደቂቃ ውስጥ ነው።” ይላል ካሊድ።