
ከ 1 ሰአት በፊት
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ለሦስት ቀናት የተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ አገራትን ረግጠዋል። ዓላማቸው ደግሞ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ያለው ግጭት ወደ ሌሎች አገራት እንዳይዛመት ለማድረግ ነው።
አርብ እስራኤል። ቅዳሜ ዮርዳኖስ። እሑድ ዌስት ባንክ፣ ኢራቅ እና ቱርክ።
በየደረሱበት ሁሉ ተግዳሮት ነበር። ተስፋ የለም ተብሎ እንዲታሰብም ምክንያት የሚሆን ጭምር ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ትልቅ ፈተና የነበረው ለማንም ሳይወግኑ መካከል ላይ ያለ አቋም ይዘው መታየት ነበር።
አርብ ዕለት ብሊንከን ቴል አቪቭ ተገኝተው ጦርነቱ በጊዜያዊነት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ። ምክንያት ያሉት ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ እና ታጋቾች እንዲለቀቀቁ ለማበረታታት ነበር። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጥሪውን ውድቅ ለማድረግ አፍታም አልቆዩ።
በማግስቱ የእስራኤል አረብ ተወካዮችን አነጋገሩ። ሁሉም አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቁ። እስራኤል የጦር ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲሉ የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አይማን ሳፋዲ ተናገሩ።
በተመሳሳይ ሰዓት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ለማድረግ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ለመድረስ የሚደረገው ለውጥ እንዴት ነው ሲባሉ አውራ ጣታቸውን ቀስረው “ጥሩ እየሄደ ነው” ሲሉ መልሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ ተስፋ እና በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ስሜት ለየቅል ነበር።
ብሊንክን እሑድ ያደረጓቸው ጉዞዎች በሚስጥር መያዛቸው በቀጠናው ያለውን ውጥረት የሚያሳይ ነው።
ከፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጋር ለነበራቸው ውይይት ወደ ራማላህ ያቀኑት ጥይት በማይበሳው መኪና ነው። በቤተመንግስት ጠባቂዎች መንገዱ ከእንቅስቃሴ ነጻ ተደርጎ በታጠቁ መኪናዎች ታጅበው ነው በፍጥነት ሲጓዙ የነበሩት።
- የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት እና የባሕር በር ለማግኘት ያሏት አማራጮችከ 6 ሰአት በፊት
- ጋዛ፡ “ባለቤቴ በ5 ደቂቃ ውስጥ ሞተች፤ እሷ ለእኔ ሕይወቴ ነበረች”ከ 6 ሰአት በፊት
- በፊሊፒንስ አንድ ዲጄ በቀጥታ ሥርጭት ላይ ሳለ ተገደለከ 5 ሰአት በፊት
ኢራቅ የደረሱት ጨለማን ተገን አድርገው ነው። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ እና ባልደረቦቻቸው ከባግዳድ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ለመጓዝ ከመኪና ሄሊኮፕተርን ተጠቅመዋል። ለጥቂት ደቂቃ ባደረጉት በረራ የጥይት መከላከያ ኮፍያ እና እና ልብስ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ሞሐመድ ሺዓ አል ሱዳኒን ለማግኘት ሲጓዙ ደግሞ ወታደራዊ እጀባው ከፍተኛ ነበር።
ሰኞ የቱርክ ባለስልጣናትን ለማግኘት ቀጠሮ ይዘዋል። የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶጋን መቀመጫቸውን በእስራኤል ያደረጉትን አምባሳደራቸውን መልሰው፤ ከኔታንያሁ ጋር መገናኘት አልፈልግም ብለዋል። አክለውም “ሰርዘነው ወደ ውጭ ጥለነዋል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ። በዚህ ሁሉ ማግስት ነው እንግዲህ ብሊንከን አንካራ የሚደርሱት።
ብሊንከን ይኼኛውን እሳት አጠፋው ሲሉ ሌላ እሳት እያጋጠማቸው ይመስላል።

ባግዳድ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ፕሬዝዳንት ባይደን ያነሱት ጊዘያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረሳል ወይ?አረብ አገራትስ ይቀበሉታል ወይ? የሚል ጥያቄ ተሰንዝሮላቸው ነበር።
ለሁለቱም ጥያቄ አዎ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አሜሪካኖች ሰብአዊ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም መተግበር የሚቻልበትን “ዝርዝሮች እና አተገባበራዊ” ስጋቶቹን ለመፍታት ከእስራኤላውያን ጋር መስራታቸውን ቀጥለዋል።
አረቦችን በተመለከተ በተኩስ አቁም ላይ የሃሳብ ልዩነት እንዳለ ተናግረዋል። ሆኖም ሁሉም ያነጋገሯቸው አካላት ሰብዓዊ ተኩስ አቁም መደረሱ ታጋቾችን ለመፍታት እንደሚረዳ፣በጋዛ የዕርዳታ ስርጭትን ለማሳደግ እና የውጭ ዜጎችን ከጋዛ ለማስውጣት እንደሚረዳ ያምናሉ።
“ባለፉት ቀናት በአካባቢው አስፈላጊ መሻሻል አይተናል። ነገር ግን አሁንም አብረው የሚመጡ ችግሮችም አሉ” ብለዋል።
ለጊዜው ግን ብሊንከን ያነሱትን ሃሳብ የሚቀበል ማንም አይመስልም። ምክንያቱ ደግሞ እስራኤልም ሆነች የአረብ አገራቱ ከዜጎቻቸው የሚደርስባቸው ጫና ሁለቱን ወገኖች እያራራቁ ነው።

ብሊንከን ከእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ጋር በማዕከላዊ ቴል አቪቭ መግለጫ ለመስጠት አርብ ዕለት ካሜራዎች ፊት በቆሙበት ሰዓት እስራኤላዊያን መስከረም 26 በሐማስ የተወሰዱትን ታጋቾች ለመታደግ መንግስት የበለጠ እንዲጥር በዝማሬ እና በጩኸት ሲጠይቁ ይሰማ ነበር።
ሄርዞግ “የእኛም ልብ ከእነርሱ ጋር ነው” ብለዋል።
በአውሮፓ እና በአሜሪካ በሚገኙ አገራት የፍልስጤም ደጋፊ የሆኑ ተቃዋሚዎች በገፍ ወደ ጎዳና ወጥተዋል። ሰልፈኞቹ ዋሽንግተን የሚገኘው የዋይት ሃውስ አጥር ላይ ሲወጡ ታይተዋል። የፓሪስ፣ የለንደን እና የበርሊን ጎዳናዎችን ሞልተው በተቃውሞ ንጠውታል።
የኢስታንቡል ተቃዋሚዎች ብሊንከን “የእልቂቱ ተባባሪ” የሚል መፈክር ይዘው ታይተዋል።

ከእስካሁኑ የብሊንከን ጉዞ አዎንታዊ ነገር ማየት ከተቻለ፤ ከሁሉም ወገኖች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑና ለጊዜው ግጭቱ አለመስፋፋቱ ነው።
ጆ ባይደን በጥቅምት ወር በዮርዳኖስ ከአረብ መሪዎች ጋር ሊያደርጉት የነበረው ስብሰባ በጋዛ ሆስፒታል በደረሰ ፍንዳታ በድንገት መሰረዙን ተከትሎ፤ ብሊንከን ስብሰባውን ቅዳሜ ማከናወናቸው የተወሰነ መሻሻል መኖሩን አመላካች ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአረብ አቻዎቻቸው ስለ ፍልስጤማውያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እና በአካባቢው “ዘላቂ” ሠላምን ለማረጋገጥ በሚያስችለው መንገድ ላይ እንዲያስቡ ለማበረታታት ያደረጉት ሙከራ ብዙም የተሳካ አልነበረም።
“ይህ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ ምን አይነት ጋዛ እንደሚኖር ሳናውቅ ስለጋዛ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዴት እናስባለን? ስለወደመ ምድር ልናወራ ነው? ሙሉው ህዝብ ወደ ስደተኛነት ስለተቀየረባት አገር ልንነጋር ነው?” ሲሉ የዮርዳኖሱ ውጭ ጉዳይ ሚስተር ሳፋዲ ጠየቀዋል።
በዋይት ሃውስ ከአይሁድ ማህበረሰብ መሪዎች ጋር የተወያዩት ፕሬዝዳንት ባይደን፤ በእስራኤል እና በጋዛ የደረሰው አሰቃቂ እና ደም መፋሰስ መጨረሻው የመካከለኛው ምስራቅ አገራትን ወደ ተሻለ ስፍራ ይቀየራል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ግን ይህን መሰሉ ተስፋ ብዙም አይታይም።