ኢራናዊቷ የመብት ተሟጋች ናርገስ ሞሐመዲ

7 ህዳር 2023

እስር ላይ የምትገኘው ኢራናዊቷ ሎሬት ናርገስ ሞሐመዲ የኖቤል ሽልማት ከተሸለመች ከአንድ ወር በኋላ የረሃብ አድማ መምታቷን ቤተሰቦቿ ገለጡ።

የ51 ዓመቷ የመብት ተሟጋች አድማ የመታችው የኢራን መንግሥት ለሷና ለሌሎች ታራሚዎች የሕክምና አገልግሎት ነፍጓል፤ እንዲሁም ሂጃብ መልበስ ግዴታ አድርጓል በሚል እንደሆነ በመግለጫ ጠቁማለች።

መግለጫው አክሎ ናርገስ የልብና የሳንባ ሕክምና ቢያስፈልጋትም አቃቤ ሕግ ግን ወደ ሆስፒታል እንዳትሄድ ከልክሏታል ይላል።

ባለፈው ሳምንት ቤተሰቦቿ ወደ ሆስፒታል እንዳትሄድ የታገደችው ፀጉሯን ለመሸፈን ፈቃደኛ ባለመሆኗ ነው ብለው ነበር።

የኖርዌጂያን ኖቤል ኮሚቲ ሊቀ-መንበር ሁኔታው እጅግ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

ሊቀ-መንበሯ ለናርገስ ሽልማቱን በሰጡ ወቅት “የኢራን መንግሥት ሴቶች ላይ የሚያደርሰውን በደል በመታገል” ለሠራችው ሥራ እንደሆነ ገልጠው ነበር።

ቤሪት ሬይስ-አንደርሰን፤ “ሴት ታራሚዎች ሕክምና ለማግኘት የግድ ሂጃብ መልበስ አለባቸው የሚለው ሕግ ኢ-ሰብዓዊ እና የሞራል ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከኢራን አቃቤ ሕግም ሆነ ከማረሚያ ቤት አስተዳዳሪዎች እስካሁን ምንም ዓይነት አስተያየት አልተሰማም።

የናርገስ ቤተሰብ በለቀቀው መግለጫ ኢቭን ከተሰኘው የኢራኑ አስፈሪ ማረሚያ ቤት በደረሳቸው መልዕክት መሠረት ናርገስ ከሰኞ ጥዋት ጀምሮ የረሃብ አድማ መትታለች።

አክቲቪስቷ ሁለት ነገሮችን ስትቃወም ነበር።

አንደኛው “እስላማዊው ሪፐብሊክ ለሕመምተኛ ታራሚዎች ሕክምና መንፈጉ፤ ይህም ታራሚዎችን ለበለጠ ሕመምና ሞት እየዳረገ መሆኑ” ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ “ኢራናዊያን ሴቶች “ሂጃብ ካልለበሱ ሞት ይጠብቃቸዋል” የሚለው ፖሊሲ ነው።

መግለጫው እንደሚለው አቃቤ ሕግ፤ ናርገስ ወደ ሆስፒታል ሄዳ ሕክምና እንዳታገኝ በተጋጋሚ ከልክሏል፤ አቤቱታም ሊቀበል አልቻለም።

“ከታማኝ የሆስፒታሉ ዶክተር በደረሰን መረጃ መሠረት ምርመራ እና ኢኮካርዲዮግራም ተደርጎላት ለአስቸኳይ የልብና ሳንባ ሕክምና ወደ ሆስፒታል እንድትሄድ ተመክሮ ነበር።”

ባለፈው ረቡዕ የአክቲቪስቷ ቤተሰብ እንደገለጠው ሌሎች የኢቭን ሴት ታራሚዎች ናርገስ ወደ ሆስፒታል ሄዳ እንድትታከም ጫና ለማሳደር ለሁለት ቀናትና ምሽቶች ተቃውሞ አድርው ነበር።

ነገር ግን “የማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ከላይ በተሰጠ ትዕዛዝ መሠረት ጭንቅላቷን ሳትሽፍን ወደ ሆስፒታል መሄድ አትችልም ብለውናል” የሚል መልስ እንደሰጧቸው የናርገስ ቤተሰብ ተናግሯል።

የኢራን ሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ማዕከል ምክትል ፕሬዝደንት የሆነችው ናርገስ የ10 ዓመት እስር ተፈርዶባታል።

በጠቅላላው 13 ጊዜ ለእስር የተዳረገችው የኖቤል ተሸላሚዋ አምስት ጊዜ ጥፋተኛ ስትባል በጠቅላላው የ31 ዓመታት እስር ተፈርዶበታል።

አልፎም 154 ጊዜ እንድትገረፍ ቢፈረድባትም ፍርድ ተግባር ላይ ስለመዋሉ የተሰማ ነገር የለም።

በሸሪዐ በሚመራው በኢራን ሕግ መሠረት ሴቶች ፀጉራቸውን በሻርፕ እንዲሸፍኑና ሰውነታቸውን የሚከልል ረዥምና ለቀቅ ያለ ልብስ እንዲለብሱ ይገደዳሉ።

በአውሮፓውያኑ መስከረም 2022 ማሻ አሚኒ “ያልተገባ” ሂጃብ ለብሳለች በሚል በኢራን ግብረ ገብ ፖሊስ እጅ ሳለች መሞቷን ተከትሎ በመላው ኢራን ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር።

በወቅቱ ኢራናዊያን ሴቶች ሻርፓቸውን በማቃጠል እና በማውለብለብ ተቃውሟቸውን የገለጡ ሲሆን በርካቶች በአደባባይ ፊታቸውን መሸፈን አቁመው ነበር።

ናርገስ ባለፈው ማክሰኞ በኖርዌጂያን የኖቤል ኮሚቲ ገፅ ላይ በለጠፈችው ደብዳቤ ሂጃብ የመልበስ ግዴታን “የኢራንን ፈላጭ ቆራጭ ኃይማኖታዊ አገዛዝ ለማስቀጠል ሕብረተሰቡ ላይ የተጫነ የአፈና እና ቁጥጥር መሣሪያ ነው” ስትል ገልጣው ነበር።