
7 ህዳር 2023
በሶማሌ ክልል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ከ20 ሰዎች በላይ ሲሞቱ፣ ከ20 ሺህ በላይ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተገለጸ።
ባለፈው ሳምንት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ ጎርፍ በሰው፣ በእንሰሳት እና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ባለሥልጣንት አሳውቀዋል።
በጎርፍ አደጋው ምክንያት አስካሁን ቢያንስ የ24 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ወደ 23 ሺህ የሚጠጉ አባወራዎች ለመፈናቀል ተዳርገዋል።
በሶማሌ ክልል የአደጋ መከላከል ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አስተባባሪ የሆኑት አቶ በሽር አረብ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የጎርፍ አደጋው በአጠቃላይ 10 ሺህ ሄክታር የሰብል መሬት ያወደመ ሲሆን፣ 3600 የቁም እንስሳትም ሞተዋል።
በክልሉ የተከሰተው ጎርፍ ጉዳት ያስከተለው በአብዛኛው በወንዝ ዳርቻ አካባቢ ባሉ ወረዳዎች እንደሆነም ተናግረዋል።
“ሸለሌ ዞን፣ አፍዴሪ እና ሊበን ዞኖች በዋነኛነት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። እስካሁን በ27 ወረዳዎች፣ በ82 ቀበሌዎች እና በሦስት ትልልቅ ከተሞች ነው ጎርፉ የተሰተው። እነሱም በአፍዴር የሚገኙት ጨረቲ፣ ሽንሌ ዞን በሚገኘው ቀላፎ እና በሊበን ዞን ዶሎአዶ ናቸው” ብለዋል።
በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ በአጠቃላይ 42 ሺህ 301 አባወራዎች የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ወደ 23 ሺህ አባወራዎች መፈናቀላቸውን ባለሥልጣኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አክለውም “ዝናቡ ከመስከረም ሦስተኛው ሳምንት አንስቶ መዝነብ ከጀመረ ወዲህ በጎርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ምክንያቶች የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል” ብለዋል።
በውሃ ማጠራቀሚያ አካባቢ በከፍተኛ ዝናብ ምክንት በሞላ ውሃ ውስጥ ከብት የሚጠብቁ ልጆች ለመዋኘት ገብተው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ እነዚህ ጨምሮ እስካሁን ቢያንስ 24 ሰዎች መሞታቸውን አመልክተዋል።
- የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት እና የባሕር በር ለማግኘት ያሏት አማራጮች6 ህዳር 2023
- አዲሱ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ዕቅዴ የጨዋታ ስልት በመቀየር ውጤት ማምጣት ነው አሉ4 ህዳር 2023
- ከ4 ሳምንታት የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት በኋላ በግልጽ የሚታዩ 5 እውነታዎች5 ህዳር 2023

በጎርፉ ምክንያት “በመንገዶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በአርሶ አደር ማሠልጠኛ ጣቢዎች እና በሌሎችም መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ደርሷል” ሲሉም አክለዋል።
ከባድ ዝናብ መጣል የጀመረው መስከረም አጋማሽ ላይ እንደሆነ እና እየተባባሰ የመጣው ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ ወዲህ ባሉት ቀናት ውስጥ መሆኑ ተነግሯል።
አቶ በሽር አረብ እንዳሉት በሶማሌ ክልል የወንዞች መገናኛ በሆኑ አካባቢዎች የውሃው መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን፣ እንዲሁም ወንዝ አቅራቢያ ካሉ አካባቢዎች ተሻግሮም ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
“አገልግሎት መስጫ ተቋማት እና የተለያዩ መሠረተ ልማት ያሉባቸው አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ በውሃ ተውጠው ነው ያሉት።”
በጎርፍ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች በሌሎች ውሃ በማይደርስባቸው አካባቢዎች ሰፍረው እንደሚገኙ እና ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ደግሞ ተፈናቃዮች በትምህርት ቤቶች እንደተጠለሉ አቶ በሽር ተናግረዋል።
“እስካሁን 6ሺህ 300 አባወራዎች የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች ተሰጥቷቸዋል” ያሉ ሲሆን፣ ለሌሎችም ተፈናቃዮች ተመሳሳይ ድጋፍ ለማቅረብ በመንገድ አለመመቻቸት ምክንያት ቢዘገይም ለእነሱም እንደያሚደርሱ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።
በጎርፉ ተሸፍነው መኪና ለማሳለፍ አስቸጋሪ ሁኔታ ባለባቸው አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አማካይነት እርዳታ ለማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል።
አቶ በሽር ለጎርፉ ተጎጂዎች “እርዳታ ለማድረስ እንዲቻል መንገድ ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ነው” ያሉ ሲሆን፣ ተጨማሪ እርዳታ ለማግኘት ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ መቅረቡንም ተናግረዋል።
የአየር ሁኔታ ትንበያ ዝናቡ አሁንም እንደሚቀጥል እንደሚያመለክተው የጠቆሙት ኃላፊው ይህ ደግሞ ተጨማሪ ሰዎች ለተመሳሳይ ችግር እንደሚዳርግ በመግለጽ፣ የተጎጂዎች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ ትንበያዎችን በመከተል በተለያዩ ዞኖች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች ተሰጥቶ እንደነበረ፣ ለአደጋ ጊዜ የሚያስፈልጉ ጀልባዎች እና ዝግጅቶች እንደተደረገም አቶ በሽር አክለዋል።
ከባድ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ክስተት ያጋጣመው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጎራባቾች ሶማሊያ እና ኬንያ ጭምር ነው።
በዚህም ሳቢያ በአገራቱ ውስጥ የጎርፍ መጥለቅለቅ በሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ሰሞኑን የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።