
ከ 5 ሰአት በፊት
ፍልስጤማዊ ካናዳዊው ማንሱር ሾማን ከጋዛ ቤተሰቦቹን ይዞ እንዲወጣ ቢፈቀድለትም ጋዛ እንደሚቆይ ገለጸ።
የአምስት ልጆች አባት የሆነው ማንሱር ጋዛ ሆኖ ጦርነቱን መሰነድ እንደሚፈልግ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ከቤተሰቦቹ ተነጥሎ ጋዛ ቀርቶ በጦርነቱ እየሆነ ያለውን መመዝገብ ኃላፊነቱ እንደሆነ ያምናል።
ባለቤቱና አምስት ልጆቹ ከጋዛ እንዲወጡ ከተፈቀደላቸው የመጀመሪያዎቹ ካናዳውያን ቤተሰቦች መካከል ናቸው።
አሁን በሰላም ግብፅ ደርሰዋል።
ከጋዛ እንዲወጡ ፈቃድ ከተሰጣቸው 80 ካናዳውያን 59 ያህሉ መውጣት ችለዋል።
በራፋ ድንበር በኩል ለመውጣት የሚጠባበቁ ከ400 በላይ ካናዳውያን እንዳሉ ተገልጿል።
ማንሱር የአስተዳደር አማካሪ ነው። ጋዛ መቅረት ግዴታዬ ነው ይላል።
“2.3 ሚሊዮን ሰዎች እየተሰቃዩ እስከሆነ ድረስ ታሪካቸውን መንገር ሃይማኖታዊም ሰብአዊም ግዴታዬ ነው” ይላል።
በኦንታሪዮ የሚገኘው ኪንግስተን ዩኒቨርስቲና አልበርታ ያለው የካልጋሪ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ ነው።
በአልበርታ ለዓመታት የነዳጅና ጋዝ ዘርፍ ላይ ሠርቷል።
- እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የትኞቹ አገራት ተቃወሙ? የትኞቹስ ደገፉ?ከ 6 ሰአት በፊት
- ግብፅ ከጋዛ ወደ ግዛቷ በሚያሻግረው የራፋህ በር ላይ ቁጥጥሯን ያጠነከረችባቸው ምክንያቶችከ 6 ሰአት በፊት
- ሐማስ በእስራኤሉ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎችን አልገደልኩም አለ7 ህዳር 2023
የተወለደው ኢየሩሳሌም ቢሆንም የባለቤቱ ትውልድ ከተማ ወደሆነው ጋዛ ተሻግረው ለመኖር ወስነዋል። ይህም ልጆቻቸው በቅድመ አያቶቻቸው መሬት እንዲያድጉ በማለት ነው።
በጋዛ ሰርጥ ጦርነት በየጊዜው ቢነሳም ሕይወታቸው መልካም ነበር።
“ልጆቻችን ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ይማሩ ነበር። እኔም ባለቤቴም ሥራ ነበረን። ጓደኞች ነበሩን። በቅርባችን ድንቅ መስጊድ ነበር” ይላል።
አሁን መኖሪያውን ካሀን ዩኒስ ሆስፒታል አድርጓል። የሚተኛው የወሊድ ክፍል ወለል ላይ ነው።
“ልጅ ሲወለድ በጎ ዜና እሰማለሁ” ይላል።
እስራኤልና ግብፅ በራፋ ድንበር በኩል የሚወጡ የውጭ አገር ዜጎች ዝርዝር ላይ ከተስማሙ በኋላ የሰዎቹ አገር እንዲቀበል መረጃ ይተላለፋል። የውጭ አገራት ዜጎችም በራፋ ድንበር በኩል መውጣት ጀምረዋል።
ማንሱር እና ቤተሰቡ እዚህ ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ነበር። የካናዳ ቆንጽላ ሠራተኛ በግብፅ ድንበር በኩል እንደሚጠብቃቸው ተነግሯቸዋል።
ለ72 ሰዓት በግብፅ ቆይተው ወደ ካናዳ ያቀናሉ።
አባትና ባል ሆኖ ቤተሰቡን ትቶ ወደኋላ መቅረት ቀላል ውሳኔ እንዳልነበረ ይናገራል።
ግን በሚችለው መንገድ ለመርዳት ጋዛ መቅረት መርጧል።
“የፈራረሰ ድንጋይ በማንሳትም ይሁን ዜና በመሥራት አግዛለሁ” ይላል።

በርካታ ካናዳውያን ከጋዛ ለመውጣት እየተጠባበቁ ነው።
የሳማህ አል-ሳባጋ የ73 ዓመት አባቷ ቤተሰቦች ለመጠየቅ ነበር መስከረም ላይ ጋዛ የሄዱት።
እስካሁን በራፋ ድንበር በኩል የሚወጡ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ባለመኖሩ አዝናለች።
“በየቀኑ ሳዋራው ድምጹ ውስጥ ሐዘን እሰማለሁ። ጋዛ ውስጥ አንድም ቀን በሕይወት መቆየት መታደል ነው ይላል” ትላለች።
እስራኤል ባለፉት ቀናት ጋዛ ላይ ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመች ነው። እግረኛ ጦርም አስገብታለች። ጋዛ ሙሉ ከበባ ውስጥም ትገኛለች።
የሳማህ አል-ሳጋባ አባት ከጦርነቱ ሽሽት አራት ጊዜ ነው መኖሪያ ቦታ የቀያየሩት።
በጋዛ እስካሁን ከ10,300 በላይ ሰዎች እንደተገደሉና ከእነዚህ መካከል ከ4,000 የሚበልጡት ሕጻናት እንደሆኑ ተገልጿል።