የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ
የምስሉ መግለጫ,የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ

ከ 6 ሰአት በፊት

በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀረበው የተኩስ አቁም ሐሳብ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያገኝ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት ድምጻቸውን አቅበዋል፣ የተወሰኑ አገራት ደግሞ ተቃውመውታል።

አንድ ወር ባለፈው እስራኤል በጋዛ ላይ በምታካሂደው ጥቃት ምክንያት የሟቾች ቁጥር እየጨመረ እና ሁኔታዎችም እየተባባሱ ከመምጣታቸው ጋር በተያያ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስተያየትን ከፋፍሏል።

ከሐማስ ጥቃት በኋላ ብዙ አገራት እስራኤልን ይደግፉ ነበር። እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው የአየር ጥቃት እና ሐማስን ለማጥፋት በሚል እየፈጸመች ያለው የእግረኛ ጦር ወረራ ትችት እያስከተለ መጥቷል።

አንዳንድ አገራት በጦርነቱ ላይ ይዘውት የነበረውን አቋም እየለወጡ ይመስላል።

አሁን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መነጋገሪያ የተኩስ አቁም ጉዳይ ነው።

እአአ ጥቅምት 27 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በእስራኤል እና ሐማስ መካከል “አፋጣኝ እና ዘላቂነት ያለው ሰብአዊ ተኩስ አቁም” እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፏል።

በዮርዳኖስ የቀረበው እና አስገዳጅ ያልሆነው የውሳኔ ሐሳብ 120 ደጋፊዎች፣ 14 ተቃዋሚዎች ነበሩት። 45 አገራት ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን የተባበሩት መንግሥታትን የውሳኔ ሐሳብ “አሳፋሪ” ብለውታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም የተኩስ አቁም ጥሪውን እንደማይቀበሉ ገልጸዋል።

አሁን ተኩስ ማቆም ለሐማስ “እጅ መስጠት ነው” ብለዋል።

ይህንን ተከትሎ አገራት እስራኤልን እየተቹ፣ ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እያቋረጡ፣ ወደ እስራኤል የላኳቸውን አምባሳደሮችንም እየጠሩ ይገኛሉ።

የተኩስ አቁም ሐሳብን የተቃወመችው አሜሪካ ሳትቀር ውጊያው “እንዲቆም” ጠይቃለች።https://flo.uri.sh/visualisation/15647652/embed?auto=1

ምዕራቡ ዓለም

በርካታ የምዕራቡ ዓለም አገራት እስራኤልን ከጦርነቱ መነሻ ጀምሮ በይፋ ሲደግፉ ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከእስራኤል ጎን እንደሚቆሙ “እስራኤል ዜጎቿ የሚፈልጉትን ለማቅረብ እንድትችል እናደርጋለን” በማለት ገልጸዋል።

ሆኖም ግን ከሰሞኑ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ቴል አቪቭ በማቅናት ሰብአዊ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና በጋዛ ንጹሃን የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመቀነስ ጉልህ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

ዋይት ሐውስ የተኩስ አቁሙ ጊዜያዊ እንደሚሆን ገልጾ፣ የአረብ አገራት ዘላቂ የተኩስ አቁም መጠየቃቸውን ነቅፏል።

የካናዳ እና የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትሮች እስራኤል “ራሷን መከላከል ትችላለች” ሲሉ ነበር በጦርነቱ መጀመሪያ ድጋፍ የሰጡት።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የውሳኔ ሐሳብ ሲቀርብ ግን ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።

በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የፍልስጥኤም ደጋፊዎች በለንደን ሰልፍ ወጥተው ጦርነቱ እንዲቆም ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ኅብረት “የሐማስን ጥቃት አጥብቀን እናወግዛለን” ብሎ የነበረ ሲሆን፣ በተመድ ጀርመን እና ጣልያን ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።

ስፔን እና ፈረንሳይ የተኩስ አቁሙን ደግፈዋል።

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኡል ማክሮን፣ ፈረንሳይ ከእስራኤል ጎን እንደሆነች በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ቢገልጹም የንጹሃን መገደል ሲጨምር የአቋም ለውጥ በተወሰነ ደረጃ አሳይተዋል።

“በጋዛ በሐማስ እና በንጹሃን መካከል ልዩነት መኖር አለበት። ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ለመጠበቅ እና አሸባሪዎች ላይ ለማነጣጠር ሰብአዊ ተኩስ አቁም ያስፈልጋል” ብለው በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ጽፈዋል።

ለፍልስጤማውያን ድጋፍ ለንደን ውስጥ የተደረገ ሰልፍ
የምስሉ መግለጫ,ለፍልስጤማውያን ድጋፍ ለንደን ውስጥ የተደረገ ሰልፍ

የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት

አብዛኛው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የተመድን ረቂቅ ውሳኔ ደግፈው ድምጽ ሰጥተዋል።

የእስራኤልን ወታደራዊ ዘመቻን አብዛኞቹ ይኮንናሉ።

ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና ባሕሬን ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን ያደሱ አገራት ሲሆኑ፣ መጀመሪያ ላይ የሐማስን ጥቃት አውግዘዋል።

አሁን ግን ባሕሬን አምባሳደሯን ከእስራኤል ስታስወጣ፣ እስራኤልም አምባሳደሯን ከባሕሬን ጠርታለች።

ዮርዳኖስም ከእስራኤል አምባሳደሯን ጠርታለች። “ያልተጠበቀ ሰብአዊ ቀውስ” በመፍጠርም እስራኤልን ከሳለች።

ሳዑዲ አረቢያ ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን ለማደስ ለወራት ንግግር ላይ ብትቆይም ግጭቱ በአፋጣኝ እንዲቆም ጠይቃለች፤ ሐማስንም አላወገዘችም።

ጥቅምት 26 የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ ዮርዳኖስ፣ ባሕሬን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ኩዌት፣ ግብፅ እና ሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች “በጋዛ ንጹሃን ዒላማ መደረጋቸውን እና ዓለም አቀፍ መርኅ መጣሱን” ተቃውመዋል።

ራስን የመከላከል መብት የፍልስጤማውያንን መብት የሚገፍ መሆን እንደሌለበት በጥምረት ባወጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት የኢራን መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ፣ ሙስሊም አገራት ከእስራኤል ጋር የምጣኔ ሀብት ግንኙነት በማቋረጥ ነዳጅ እና ምግብ ከእስራኤል ማስገባት እንዲያቆሙ አሳስበዋል።

የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሒም ራይሲ፣ ሐማስ እስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈው ተዋጊዎቹን “ጀግና፣ ደፋር ተነሳሽነት ያላቸው፣ ታጋዮች” ሲሉ አሞግሰዋል።

ኢራን በጥቃቱ እጇ እንደሌለ ገልጻለች።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን መጀመሪያ ላይ አስታራቂ ሚና ለመያዝ ነበር የሞከሩት። ጋዛ ውስጥ የሚገኘው አል-አህሊ ሆስፒታል ላይ የደረሰውን ፍንዳታ ተከትሎ ግን ይህ ተለውጧል።

ስለ ፍንዳታው ብዙ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። በጋዛ ሰርጥ ያለው የጤና ሚኒስቴር 500 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።

በኢስታንቡል ፍልስጤምን የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ ሲካሄድ፣ ኤርዶዋን እስራኤልን “የጦር ወንጀለኛ” ብሎ ለመፈረጅ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንደ ሌሎች የኔቶ አባል አገራት እና የአውሮፓ ኅብረት፣ ቱርክ ሐማስን አሸባሪ ቡድን ብላ አትፈርጅም።

ኤርዶዋን ሐማስን “የፍልስጤምን መሬት ለማስከበር የቆመ የነጻነት ታጋይ” ብለው ነው የገለጹት።

የተመድን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብን ቱርክ ደግፋለች።

ድምጸ ተአቅቦ ያደረገች ብቸኛ የቀጠናው አገር ኢራቅ ናት። ሌሎቹ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሐሳቡን ሲደግፉ እስራኤል ብቻ ተቃውማለች።https://flo.uri.sh/visualisation/15650991/embed?auto=1

ፍልስጤማውያን ታዳጊዎች ከጋዛ ውስጥ ፍርስራሽ መካከል
የምስሉ መግለጫ,ፍልስጤማውያን ታዳጊዎች ከጋዛ ውስጥ ፍርስራሽ መካከል

ሩሲያ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሐማስን ጥቃት ተከትሎ ለጥቂት ቀናት አስተያየት አልሰጡም።

ኋላ ላይ የተፈጠረውን ቀውስ “የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲ ውድቀት” ውጤት ነው ብለዋል።

ጦርነቱ በተቀሰቀሰ በሳምንቱ ፑቲን “ያልተጠበቀ ጥቃት እስራኤል ከሐማስ በኩል ገጥሟታል” ብለው እስራኤል በራሷ የጭካኔ መንገድ ምላሽ እየሰጠች እንደሆነ ገልጸዋል።

ለእስራኤል ሐዘናቸውን አልገለጹም። ሐማስንም አላወገዙም።

ሩሲያውያንን ጨምሮ የታገቱ ሰዎችን ለማስፈታት ጥቅምት 26 በሞስኮ ከሐማስ ልዑካን ጋር ውይይት ተካሂዷል።

ሩሲያ እና ቻይና አሜሪካ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችውን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ድምጽን በድምጽ ሽረዋል። ሩሲያ የምትደግፈው የውሳኔ ሐሳብ በቂ ድጋፍ ሳያገኝ ቀርቷል።

የተመድን የውሳኔ ሐሳብ ሩሲያ ደግፋ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ድምጽ ከሰጡ አገራት ጎን ቆማለች።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ሐማስ የፍልስጤምን መሬት ለመጠበቅ የሚታገል ቡድን ነው ብለዋል
የምስሉ መግለጫ,የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ሐማስ የፍልስጤምን መሬት ለመጠበቅ የሚታገል ቡድን ነው ብለዋል

እስያ

አጠቃላይ የእስያ አገራት የተኩስ አቁም እንዲደረግ በተመድ ድምጽ ሰጥተዋል።

ቻይና ሰላም የማውረድ ሚና ለመጫወት እየሞከረች ነው።

“የሚመለከታቸው አካላት ንጹሃንን ለመጠበቅ ሲባል ግጭቱን በአፋጣኝ ማቆም አለባቸው” ብላለች ቻይና።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ከግጭቱ መውጣት የሚቻልበት መንገድ የሁለት አገራት መፈጠር በመፍትሄ ነው። ነጻ የፍልስጤም አገር መፈጠር አለበት” ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ይ እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ያለው “ራስን ከመከላከል ያለፈ ነው” ብለዋል። የእስራኤል መንግሥት “የጋዛን ሕዝብ በጅምላ መቅጣት ማቆም አለበት” ሲሉም አክለዋል።

ሕንድ ድምጸ ተአቅቦ ካደረጉ አገራት መካከል ናት።

የሕንድ ተቃዋሚዎች ይህንን እርምጃ “አስደንጋጭ” ብለውታል።

ሕንድ ነጻነቷን ካገኘች በኋላ ከፍልስጤም ጋር ቅርብ ትስስር ነበራት። ሁለት አገራት መፈጠራቸውንም ትደግፍ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲና ቀኝ ዘመም መንግሥታቸው ሥልጣን ከያዘ በኋላ ከእስራኤል ጋር ተቀራርበዋል።

ከጥቃቱ በኋላ “የሕንድ ሕዝብ ከእስራኤል ጎን ይቆማል። ማንኛውንም የሽብር ድርጊት ሕንድ ታወግዛለች” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ፓኪስታን ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የላትም። ፕሬዝዳንት አሪፍ አልቪ “ተጨማሪ ደም መፋሰስ እንዳይኖር እና የሰዎች ሕይወት እንዳይጠፋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ። በአስቸኳይ ተኩስ አቁም ያስፈልጋል” ብለዋል።

ጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ላይ በአውሮፓውያኑ ኅዳር 1 ጥቃት ሲፈጸም የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጊቱን አውግዞ “እስራኤል ኋላ ቀር ጥቃት ፈጽማለች” ሲል ኮንኗል።https://flo.uri.sh/visualisation/15650839/embed?auto=1

የአፍሪካ አገራት

55 አባል አገራት ያሉት የአፍሪካ ኅብረት ጥቅምት 7 ፍልስጤምን የሚደግፍ መግለጫ አውጥቷል።

“የፍልስጤማውያን መሠረታዊ መብት የሆነውን ነጻ እና ሉዓላዊ አገር ምሥረታ መንፈግ የእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት መንስኤ ነው” ብሏል።

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ በሬ እንዳሉት ሐማስ አሸባሪ ነው ብሎ መንግሥታቸው አያምንም። ለሐማስ ድጋፍ ለማድረግም ዝግጁ ናቸው።

ቱኒዚያ “ሙሉ እና ቅድመ ሁኔታ የሌለው” ድጋፍ ለፍልስጤም እንደምትሰጥ ገልጻለች።

በተመድ ግን ድምጸ ተአቅቦ ነው ያደረገችው።

የቱኒዚያው ፕሬዝዳንት ካይስ ሳይድ በእስራኤል እየተፈጸመ ስላለው “የዘር ጭፍጨፋ ዓለም አቀፍ ዝምታን” ተችተዋል።

የቱኒዚያ ፓርላማ ከእስራኤል ጋር በቀጥተኛም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚደረግ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርግ ረቂቅ ላይ እየተወያየ ነው።

ኢትዮጵያ፣ ካሜሩን፣ ደቡብ ሱዳን እና ዛምቢያ በተመድ ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።

ብራዚል ውስጥ በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ በሚጠይቅ ሰልፍ ላይ የተሳተፈች ሴት
የምስሉ መግለጫ,ብራዚል ውስጥ በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ በሚጠይቅ ሰልፍ ላይ የተሳተፈች ሴት

ላቲን አሜሪካ

በላቲን አሜሪካ በርካታ አገራት በተመድ የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ደግፈዋል።

እስራኤል በጋዛ ጥቃት ከከፈተች በኋላ ቦሊቪያ ግንኙነቷን ከእስራኤል ጋር በማቁረጥ ቀዳሚዋ የላቲን አሜሪካ አገር ሆናለች።

የቦሎቪያ መንግሥት በጋዛ እየደረሰ ያለውን ጥቃት “ነውጠኛ እና ያልተመጣጠነ” ሲል ነው ያወገዘው።

እስራኤል በምላሹ “ለሽብር እጅ መስጠት” ስትል መግለጫውን አጣጥላለች።

ኮሎምቢያ እና ቺሊ በጋዛ ሰብአዊ ቀውስ ከመባባሱ ጋር በተያያዘ አምባሳደሮቻቸውን ጠርተዋል።

ከአረብ አገራት ውጭ ከፍተኛ የፍልስጤማውያን ቁጥር ያላት ቺሊ እስራኤል እየፈጸመች ያለው “ተቀባይነት የሌላው ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕግ ጥሰት ነው” ብላለች።

ኮሎምቢያ በጋዛ ላይ እስራኤል እየፈጸመች ያለውን ወረራ በጽኑ ነው ያወገዘችው።

ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ “የዘር ጭፍጨፋን አንደግፍም” ብለዋል። ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚያቋርጡም ተናግረዋል።

የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ሉላ ዳ ሲልቫ መጀመሪያ ላይ የሐማስን ጥቃት አውግዘው ታጋቾች እንዲለቀቁ ቢጠይቁም፣ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ወረራ አውግዘዋል።

ጥቅምት 25 ፕሬዝዳንቱ “ይሄ ጦርነት አይደለም። የዘር ጭፍጨፋ ነው። ከጦርነቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው 2,000 ገደማ ሕጻናት ተገድለዋል። የጦርነቱ ሰለባ ናቸው” ብለዋል።

ከደቡብ እና መካከለኛው አሜሪካ አገራት መካከል ፓራጉዋይ እና ጓቲማላ ብቻ ናቸው የተመድን ረቂቅ ሐሳብ የተቃወሙት።