
ከ 1 ሰአት በፊት
ሞሐመድ ሳላህ በእስራኤል-ጋዛ ግጭት በማሕበራዊ ሚዲያ የሰጠው ምላሽ ለሌሎች አርአያ ሊሆን ይገባል ሲሉ የቀድሞ የስፖርት ምሑራን ገለጡ።
ግብፃዊው የሊቨርፑል አጥቂ “ተጨማሪ የንፁሐን ነብስ ከመጥፋቱ በፊት የዓለም መሪዎች አንድ ነገር እንዲሉ” ሲል ባለፈው ወር ጥሪ አቅርቧል።
የ31 ዓመቱ ሳላህ በእስራኤልና ሐማስ መካከል እየተካሄደ ስላለው ግጭት አስተያየት ከሰጡ በማሕበራዊ ሚድያ ትልቅ ተከታይ ካላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው።
ሐማስ በዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታኒያ መንግሥታት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ መፈረጁ ይታወቃል።
ምስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ወደ እስራኤል ዘልቆ 1400 ሰዎችን ከገደለ እና ከ240 ያላነሱ ሰዎችን ካገት በኋላ ነው እስራኤል በጋዛ ጥቃት መሰንዘር የጀመረችው።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው በጋዛ በደረሰው ጥቃት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
“ሳላህ በዜግነቱ ምክንያት አንድ ጎን ሊይዝ ይችላል የሚል ጫና ያለበት ተጫዋች ነው” ይላሉ በስታፈርድሻየር የስፖርት ጋዜጠኝነት አስተማሪው ኢያን ቤይሊ።
“ነገር ግን ቆም ብሎ «እኔ የምቆመው ለሰላም እንዲሁም ስቃይ እንዲቆም ነው» አለ።”
- እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የትኞቹ አገራት ተቃወሙ? የትኞቹስ ደገፉ?ከ 6 ሰአት በፊት
- ጋዛ፡ “ባለቤቴ በ5 ደቂቃ ውስጥ ሞተች፤ እሷ ለእኔ ሕይወቴ ነበረች”6 ህዳር 2023
- ዶክተር፣ ልብስ ሰፊ፣ ጨቅላ ሕጻን…- በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደሉት መካከል የጥቂቶቹ አሳዛኝ ታሪክ5 ህዳር 2023
ምሑሩ እንደሚሉት የሳላህ መግለጫ በቂ አይደሉም የሚሉ ሰዎች አለ። እኒህ ሰዎች ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ ተብሎ የተሸለመው ሳላህ የበለጠ “ፖለቲካዊ አቋም እንዲይዝ” ይጠበቃሉ።
“መልዕክቱን ሲለቅ በርካቶች ለሰብዓዊ መብት በመቆሙ አድንቀውት ነበር፤ ሌሎች ደግሞ አቋሙ የበለጠ ለአረቡ ዓለም እና ለፍልስጤም ያደላ መሆን ነበረበት ሲሉ ተችተዋል” ይላሉ ኢያን።
“ነገር ግን ይህን ማድረግ አይችልም፤ ምክንያቱም ማሕበራዊ ሚድያን በተለመከተ የክለቡን ፖሊሲ መጣስ አይችልም።”
ቱኒዚያዊው የቴኒስ ኮከብ ኦንስ ጃብውር በያዝነው የአውሮፓውያኑ ወር መባቻ ከሽልማት ከሚያገኘው ገንዘብ የተወሰነውን ለፍልስጤማዊያን እለግሳለሁ ብሎ ነበር።
ይህ “ፖለቲካዊ መልዕክት ሳይሆን ሰብዓዊ ነው” የሚሉት ምሑሩ የቴኒስ ተጫዋቹን መልዕክት ያደንቃሉ።
እና ሳላህ፣ ኦንስ እና ሌሎች የስፖርቱ ዓለም ሰዎች ፖለቲካዊ አቋምን በተመለከተ ምን ያስተምሩናል? ያላቸውን መድረክ ተጠቅመው ምልከታቸውን ቢያሰራጩስ ምን አደጋ አለው?
ማሕበራዊ ሚድያ “ታላቁ የለውጥ መንገድ”
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በርካታ የአፍሪካ በተለይ ደግሞ የሰሜን አፍሪካ እግር ኳስ ክለቦች፣ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ለፍልስጤማዊያ ያላቸውን ድጋፍ ገልጠዋል።
የአልጄሪያው አምበል ሪያድ ማሕሬዝን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾች የፍልስጤምን ባንዲራ ስታድየም ውስጥ አውለብልበዋል።
“በፍልስጤም እየተካሄደ ስላለው ነገር ከሞላ ጎደል ሁሉም አልጄሪያዊያን ተጫዋቾች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል” ይላል አልጄሪያዊው የስፖርት ጋዜጠኛ ማሔር ሜዛሒ።
ሜዛሒ የሳላህን መግለጫ “ታዋቂ ሰዎች እንዲናገሩ ጫና ሲያድርባቸው ምን ማለት እንዳለባቸው” የታየበት ነው ይላል።
የዲጂታል ሚድያ ስትራቴጂስት የሆነችው ኬንያዊቷ ካሮል ኪሙታይ ያለንበት ዓለም ይህ እንዲሆን ያስገድዳል ትላለች።
“ዘረኝነት፣ ኃይማኖት፣ የፆታ ጉዳይ፣ ግጭት የመሳሰሉ ርዕሶች ሲነሱ የስፖርቱ ዓለም ሰዎች ከፈለጉ መናገር ካልሆነ ዝም ማለት ይችላሉ” ትላለች።
“ነገር ግን ጉዳዩ ለግለሰቡ ቅርብ ሲሆን ሰዎች እውነተኛ ማንነት እንዲወጣ ይሻሉ። ጋዛ ለሳላህ ቅርብ ነው። ይህ እንደ ሳላህ ያሉ ተጫዋቾች ምን ያክል ቀላል ያልሆነ ውሳኔ እንደሚጠብቃቸው ያሳያል።”
ሳላህ ያደገው ናግሪግ በተሰኘው የግብፅ ክፍል ነው። ናግሪግ ከጋዛ 350 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው።

እንደ ክሪስታል ፓላስ ያሉ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ለእስራኤል ያላቸውን ድጋፍ ማሳየታቸውስ ችግር አለው?
የስኪማ ቢዝነስ ስኩል ፕሮፌሰሩ ሳይመን ቻድዊክ ዕይታ ይህ ችግር የለውም።
“ሁለቱ የክለቡ ባለቤቶች አይሁዳዊያን ናቸው። ሶስተኛው ባለቤትም ቢሆን ከአይሁዳዊ አሜሪካዊያን ጋር ቅርበት ያለው ሰው ነው። የክለቡ ባለቤቶች ማናቸው የሚለው የክለቡ ባሕል ወሳኝ ናቸው” ይላሉ።
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወተው ማኖር ሶሎሞን የሐማስን ጥቃት ካወገዙ ታዋቂ ሰዎች መካከል ነው።
የቶተንሃሙ ሶሎሞን ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከመምጣቱ በፊት በዩክሬን ይጫወት ነበር። በእስራኤል-ጋዛ ግጭት ምክንያት ቤተሰቦቼ “ገሃነም” ውስጥ ነበሩ ይላል።
ቤይሊ የማሕበራዊ ሚድያን ተፅዕኖ ይረዳሉ።
“ይህ ግጭት የዛሬ 30 ዓመት ሆኖ ቢሆን ኖሮ ተጫዋቾች ዘንድሮ በማሕበራዊ ሚድያ የሚደርስባቸው ተፅዕኖ አይደርስባቸውም ነበር” ይላሉ።
የማሕበራዊ ሚድያ አደጋ
ታዋቂው አሜሪካዊ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ሌብሮን ጀምስ ሐማስን አውግዞ ለእስራኤል ያለውን ድጋፍ በመግለጡ ከብዙዎች ነቀፋ ደርሶታል።
የቡጢ ተጋጣሚው ፍሎይድ ሜይዌዘርም እንዲሁ በተመሳሳይ በማሕበራዊ ሚድያ ትችት አስተናግዷል።
ከዚህ አልፎ ማሕበራዊ ሚድያ ላይ በለጠፉት ነገር ከክለቦቻቸው የዲሲፕሊን ቅጣት የተሰጣቸው አሉ።
ለፈረንሳዩ ኒስ የሚጫወተው አልጄሪያዊው ተከላካይ ዩሴፍ ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የለጠፈው መልዕክት ፀረ-ሴማዊ ነው በሚል እንዲያጠፋና ይቅርታ እንዲጠይቅ ተደርጓል።
የፈረንሳዩን ሊግ 1 የሚያስተዳድረው የሃገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዩሴፍ ሰባት ጨዋታ እንዲቀጣ ፈርዶበታል።
ኑሳይር ማዝራዊ ለፍልስጤም የሚያደላ ቪድዮ በኢንስታግራም ገፁ ለጥፎ ክለቡ ባየርን ሙኒክ ከሞሮኳዊው ተጫዋች ጋር ውይይት አድርጊያለሁ ካለ በኋላ መልዕክቱን ቀይሮ ለጥፏል።
በሌላ በኩል የሜይንዝ ተጫዋቹ ኔዘርላንዳዊው አንዋር ኤል ጋዚ የለጠፈውን መልዕክት ለማጣፋትና ይቅርታ ለመጠየቅ አሻፈረኝ በማለቱ ከክለቡ ጋር ያለው ውል ተቋርጧል።