
የጽሁፉ መረጃ
- ፀሐፊ,አሌክስ ደ ዋል*
- የሥራ ድርሻ,የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ
- ከ 42 ደቂቃዎች በፊት
በኢትዮጵያ አዲስ ጦርነት ሊነሳ ነው የሚሉ ወሬዎች በርክተዋል። ይህ እውነት ቢሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአምስት ዓመታት ሥልጣን አራተኛው መሆኑ ነው።
ከኤርትራ ጋር ሰላም በማውረድ የ2019 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ከውጭ ጦር መሳሪያዎችን እያስገቡ እና ሠራዊታቸውን እያስታጠቁ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ ትኩረት ውስጥ ሊገባ የሚችለው የኤርትራ አካል የነበረው ቀይ ባሕር ወደብ የሆነው አሰብ ነው።
ከ1990 የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ የአሰብ ወደብ ገቢ ወጪው ተቀዛቅዟል፤ ኢትዮጵያም ምርቶቿን የምትልከው እና ወደ አገር የምታስገባው በጂቡቲ በኩል አድርጋለች።
ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት በጂቡቲ በኩል ወጪ ገቢ ምርቶቿን ማንቀሳቀስ ቢቻላትም ጂቡቲ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም።
ለዚህም ሊሆን ይችላል ኢትዮጵያውያን እና የጎረቤት አገር ሰዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጀርባ ሌላ ትርጉም እንዳለ አድርገው ተረድተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃይል ለመጠቀም እየዛቱ ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግን በይፋ ኤርትራን የመውረር ዕቅድ እንደሌላቸው በቅርቡ በተደረገ ወታደራዊ ትርዒት ላይ ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ሌላ አገር ወርራ አታውቅም፤ ወደፊትም ይህን አታደርግም” ሲሉ ትርዒት ለማቅረብ ለተሰበሰበ የአገሪቱ ጦር አባላት ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነመንግሥት ድርጅት (ኢጋድ) በኩል አስቸኳይ ስብሰባ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ፍላጎት እና በጦር መሳሪያ እራሷን ለማጠናከር የምታደርገው እሽቅድምድም መዘዝ ይኖረዋል።
- እስራኤል ወታደሮቿ መሃል ጋዛ ከተማ መግባታቸውን አስታወቀች5 ህዳር 2023
- ማሕበራዊ ሚድያና የጋዛ ግጭት፡ ሞሐመድ ሳላህ ለስፖርቱ ዓለም “አርአያ” ነውከ 1 ሰአት በፊት
- እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የትኞቹ አገራት ተቃወሙ? የትኞቹስ ደገፉ?ከ 6 ሰአት በፊት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትን ሰብስበው “የባሕር በር በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን። ይህ የማይሳካ ከሆነ ግን ኃይል እንጠቀማለን” ማለታቸው ተዘግቧል።
አንዳንዶች ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በአገር ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት በመሻት ነው ሲሉ ይደመጣሉ።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ እና ታላቋን ኢትዮጵያ የሚሰብኩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ምሁራንን ለመማረክ ያሰበም ይመስላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ቡድን ሁለት ዓመት ከፈጀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በኋላ ከህወሓት ጋር ስምምነት ሲፈጽሙ ወደ ጎን ገፋ አድርገውት ነበር።
ይህ ብቻ ሳይሆን በትግራይ ጦርነት ወቅት ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ የነበሩት የፋኖ አባላት ትጥቅ እንዲፈቱ ከተባለ በኋላ በተፈጠረ አለመግባባት ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ በክልሉ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል።
ምንም እንኳን ስህተት ቢሆንም በርካታ ኢትዮጵያውያን ትልልቅ አገራት የባሕር በር እንዲያገኙ የዓለም አቀፍ ሕግ ዕድል ይሰጣል ብለው ያምናሉ።
ሌላኛው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ አገሪቱ በስምምነት ካልሆነም በኃይል የባሕር በር እንዲኖራት ያስቻሉ እና ለኢትዮጵያ ታላቅነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉ ተብለው መታወስ መፈለጋቸው ነው።
ለአስርታት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተገማች ነበር። የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ እንዲሆን የሚፈልግ ፖሊሲ ነው።
ይህ ደግሞ በከፊል ከተባበሩት መንግሥታት እና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን በሱዳን እና በሶማሊያ የሚካሄዱ የሰላም ማስከበሮች ላይ በመሳተፍ ታይቷል።
በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት እና ለአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ከፍተኛ ሠራዊት የምታዋጣ አገር መሆን ችላለች።
ሌላኛው ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የመጓጓዣ ኮሪደርን እና የኤሌትሪክ ኃይል ጨምሮ ያሉ ፍላጎቶች ናቸው።
የሕዳሴው ግድብ ለጎረቤት አገራት መሸጥ የሚያስችል ኃይል ማምረት እንዲችል ሆኖ የተሠራ ነው።
ከመነሻ ሃሳቡ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን አንድ የምጣኔ ኃብት አካል በማድረግ ለማስተሳሰር ያለመ ነው።

በአሁኑ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምንም ሁኔታ የማይገመቱ ናቸው እየተባሉ ነው። ይህም በአገር ውስጥ እና በውጭ ጉዳዮች ጭምር የሚነሳ ጉዳይ ነው።
በሚያስደንቅ ተገላቢጦሽ በአንድ ወቅት የአፍሪካ ቀንድን በማተራመስ ስትገለል የነበረችው ኤርትራ እራሷን ኃላፊነት የሚሰማው የአካባቢው ኃይል ሆና ቀርባለች።
ኤርትራ ለቀድሞ አጋሯ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጠችው ምላሽ “የሚመለከታቸውን ወገኖች ሁሉ ግራ ባጋባ” ባለችው ሁኔታ ውስጥ በሚደረግ “ንግግሮች” እንደሌለችበት ገልጻለች።
ጂቡቲ፣ ነጻ አገር ነኝ የምትለው ሶማሊላንድ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ ስጋታቸውን የሚያንጸባርቅ መግለጫ በማውጣት የኢትዮጵያን ሁኔታ ለመቆጣጠር ይፋዊ ባልሆነ መሰባሰብ የፈጠሩ ይመስላል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዋነኛ ደጋፊ ናት። በግልጽ እንደሚታየው አዲስ አበባ ውስጥ እየተገነባ ያለውን ቅንጡ ቤተ መንግሥት ወጪ በመሸፈን እንዲሁም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) እየሰጠች ነው።
በቅርብ ቀናት ውስጥ የአረብ ኤምርቶች አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ የአየር ኃይል ሰፈር ውስጥ ጭነቶችን ሲያራግፉ ታይተዋል።
ዱባይ በተጨማሪም፣ በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት የዋና ከተማዋን የካርቱምን ጨምሮ አብዛኛውን ሱዳን የተቆጣጠረውን በጄኔራል ሞሐመድ ሐማዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ትደግፋለች።
ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፍላጎት አደጋን እና መልካም ዕድልን የያዘ ነው።
አንደኛው ኢትዮጵያ የኤምሬቶች ታዛዥ አገር በመሆን በቀይ ባሕር ወሳኝ ኃይል ሊያደርጋት ይችላል ወይም በአፍሪካ ቀንድ አዲስ ጦርነት ተቀስቅሶ ሱዳን ውስጥ ያገኘችውን ወሳኝ ሚና ሊያሳጣት ይችላል።
በሌላ በኩል ከአሜሪካ ጋር በመሆን በሱዳን ተፋላሚ ወገኖች መካከል ተኩስ አቁም እንዲደረግ የምትጥረው ሳዑዲ አረቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እያደረጉት ባለው ሁኔታ መረበሿ እየተነገረ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳዑዲን የሚቀርቡ ከሆነ፣ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አንጻር ያላትን ስጋት ለማስወገድ ድጋፍ ልትሰጥ ትችላለች።
በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የምራቸውን ወደ ጦርነት የሚገቡ ከሆነ ሁለት ተግዳሮቶች ሊገጥሟቸው ይችላል። አንደኛው ማንነው ሊዋጋ የሚሰለፈው።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የአገሪቱ ሠራዊት ተዳክሟል። በመጀመሪያው ሠራዊቱ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በጦርነት ውስጥ የነበረ ሲሆን አሁንም አልተጠናቀቀም።
ሁለተኛው ደግሞ ከኤርትራ ጋር በመሆን ከህወሓት ጋር በተደረገው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት መሞታቸው፣ መቁሰላቸው ወይም የደረሱበት አልታወቀም።
ሦስተኛው ጦርነት ደግሞ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ በአማራ ክልል የተጀመረው እና ኤርትራ ታስታጥቀዋለች ከተባለው ከፋኖ ጋር የሚደረገው ውጊያ ነው። በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት በግጭት ማጥ ውስጥ ገብቷል።

ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት የምትገባ ከሆነ በአቀማመጧ የኤርትራ ተጎራባች የሆነችው እና በሁለት ዓመቱ ጦርነት የተዳከመችው ትግራይ ክልል ምናልባትም ተሳታፊ ልትሆን ትችላለች።
ትግራይ ውስጥ ድጋሚ ወደ ጦርነት ለመግባት ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች የሉም። ነገር ግን የኤርትራ ሠራዊት በፈጸመው ጭፍጨፋ ጥልቅ እና ሰፊ ቁጣ በኤርትራ ላይ አለ።
ስለዚህም የፌደራል መንግሥቱ ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት የሚገባ ከሆነ በእርግጠኝነት ትግራይም ተስባ መግባቷ አይቀርም።
አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ጦርነት አይቀሬ ነው ብለው ያስባሉ፤ ስለዚህም ወደ ጦርነቱ ከመግባታቸው በፊት ከሦስት ዓመት በፊት በአማራ ክልል የተያዙባቸው መሬቶች እንዲለቀቁላቸው እና አውሮፕላኖችን ጨምሮ የተወሰኑ ወታደራዊ መሳሪያዎችን መቆጣጠር አለብን ብለው ያስባሉ።
ሌላኛው ፈተና ደግሞ ለጦርነቱ የሚያስፈልገው ወጪ ነው። የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የዓለም ገንዘብ ድርጅትን፣ የዓለም ባንክን እንዲሁም ለጋሾችን ድጋፍ እየፈለገ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የገንዘብ ድጋፍ አገኛለሁ ብለው ተስፋ አድርገው ሊሆን ይችላል። ገንዘቡ ቢገኝ እንኳን ጦርነት ሊያስከትል የሚችለውን ግዙፍ ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳት ሊያካክሰው አይችልም።
እናም ኢትዮጵያ ጦርነት ጀመረችም አልጀመረች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጦርነት ጉዳይ የሚታሰብ ነገር አድርገውታል።
በአካባቢው ያለው የጦር መሳሪያ መታጠቅ እሽቅድድም እየተፋጠነ ነው።
ኢትዮጵያ ተጨማሪ መሳሪያዎችን እየገዛች ነው።
ኤርትራ እና ጂቡቲም ተመሳሳይ ነገር ማድረጋቸው አይቀርም። በትግራይ ያሉ ተዋጊዎችን የመበተኑ ሃሳብ ቆሟል። በሶማሊያ ያለው ግጭትም ሊባባስ ይችላል።
በአማራ ክልል ያለውን ጦርነት ለማባባስ ኤርትራ ለአማራ ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ ልታቀርብ ትችላለች።
ስለዚህም ማንኛውም ትንሽዬ ክስተት ከቁጥጥር ውጪ የመሆን አደጋ ተደቅኗል።
በአፍሪካ ቀንድ ፈጽሞ ሊኖር የማይገባው ነገር ቢኖር አዲስ ጦርነት መቀስቀስ ነው። ነገር ግን አሁን ያለው ሁኔታ ጦርነት የመነሳቱን ዕድል በሚያሳስብ ሁኔታ ከፍተኛ ነው።
____
*አሌክስ ደ ዋል አሜሪካው ተፍትስ ዩኒቨርስቲ በፍሌቸር የሕግ እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ውስጥ የዎርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ናቸው።