November 8, 2023

“የፕሪቶርያውን ውል የፈረምነው የትግራይ መሬት አሳልፈን ለመስጠት አይደለም” የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር

የፕሪቶርያው ውል የፈረምነው የትግራይ መሬት አሳልፈን ለመስጠት ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ መሰረት መፈታት አለበት ስለተባለ ነው ሲል የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ገለጸ።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ከክልሉ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ “የመሬት ይገባኛል የሚባል እውነት የሚመስል ጥያቄ በሌላኛው ወገን ማለትም በአማራ ክልል ያለ አስመስሎ ማቅረብ ነው፣ እንደ እኔ እምነት ግን የለም የሚል እምነት ነው ያለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሬዝደንቱ አክለውም፤ ምዕራብ ትግራይ እና ደቡብ ትግራይ ወደ ነበረበት አስተዳደር መመለስ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ቦታዎች ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ወደ ትግራይ መካለል እንዳለባቸው እና ምርጫም ሆነ ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ በጊዜያዊ ሳይሆን በተመረጠ የትግራይ ክልል መንግሥት የሚከወን መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

እንዲሁም “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር “አጨቃጫቂ” ናቸው በሚባሉ የትግራይ ግዛቶችን ማስተዳደር የለበትም” የሚሉ የፌደራል መንግሥቱ ተደራዳሪዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ፕሬዝደንቱ አክለውም፤ “የፕሪቶሪያ ውል የተኩስ ድምፅ የማቆም ስምምነት ነው” ያሉ ሲሆን፤ “ከዚህ አኳያ ስኬታማ ውልና ስምምነት ነው” ብለዋል። ነገር ግን “ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ብዙ ይቀረናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የግጭት መቆሙ፣ የህወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዝ እና የበጀት መለቀቅ በስምምነቱ መሰረት የታዩ መሻሻሎች እንደሆኑ ገልጸው፤ አልተፈጸሙም ያሏቸውን በርካታ ነጥቦች ዘርዝረዋል።

በዚህም ተፈናቃዮች ከሰኔ 21/2015 በፊት ወደ ቀያቸው ለመመለስ ቃል ቢገባም ተግባራዊ አለመደረጉን አንስተዋል።

እንዲሁም በስምምነቱ መሰረት የትግራይ ግዛትን የተቆጣጠሩት ኃይሎችን ማስወጣትና በትግራይ ግዛት በአማራ ሃይሎች የተመሰረቱት አስተዳደሮች የማፍረስ ጉዳይ የፌደራል መንግሥት ግዴታዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በመንግሥት የሚነሳው በትጥቅ መፍታት እና የመቀላቀል ጉዳይ በበጀት እጥረት ምክንያት የተፈለገውን ያህል አለመሄዱን የገለጹም ሲሆን፤ “ለዚህ ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቻ አይወቀስም” ብለዋል።

የፌደራል መንግሥት “ስምምነቱን ለመፈጸም ረጅም ርቀት ብሄድም፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ‘እግር የመጎተት አዝማሚያ’ እያሳየ ነው” የሚል ትችት ማቅረቡን አስመልክቶም ጌታቸው “ክሱ የተጋነነ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በመጨረሻም “ኹሉም ልዩነቶች ሰላም ብቻ ነው መፈታት ያለባቸው፡፡ ከጥይት ተኩስ ለውይይት ቦታ መስጠት አለብን። ትግራይ የአውዳሚ ጦርነት መናህሪያ እንድትሆን አንፈቅድም ” ብለዋል።

ከሰሞኑ የፕሪቶሪያው ስምምነት አንደኛ ዓመት አስመልክቶ የተለያዩ አካላት መግለጫ ያወጡ ሲሆን፤ በስምምነቱ ውስጥ የተፈጸሙ ነገሮች መኖራቸውን በማንሳት ነገር ግን ወደ ተግባር ያልተቀየሩ በርካታ ነገሮች መኖራቸው መግለጻቸውን አዲስ ማለዳ ስትዘግብ መቆየቷ የሚታወስ ነው።