November 8, 2023 – Abebe Bersamo 

ጥቅምት 25 ቀን 2016 ዓ/ም የብልጽግና አገዛዝ ለአራተኛ ጊዜ ትልቅ ኦፐሬሽን ጀምሯል፡፡ ታላቁ የፊዚክስ ሳይንቲስት አልበርት አነስታይን፣ ” አንድ ነገር እየደጋገሙ በማድረግ የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው” እንዳለው፣ ይህ የነ አብይ አህመእድ ዘመቻ፣ የእብደትና የድንቁርና ዘመቻ ነው፡፡ ነበርሱ እብደትና ድንቁርኛ መከላከያ የተባለውን ተቋም፣ የኦሮሞ ልዩ ኃይልን በግዳጅ ይሁን ብሬን ዎሽ ተድርገው፣ ወይንም በቅንነት አገር እናገለግል ብለው፣ የተቀላቀሉ የድሃ ልጆች እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው፡፡

👉 1ኛው የከሸፈው ዘመቻ

የመጀመሪያው ትልቅ ኦፐሬሽን የተጀመረው ሚያዚያ 20 ቀን 2015 ዓ/ም ነበር፡፡ በወቅቱ ፣ “የአማራ ልዩ ኃይል ተበትኗል” ብለው በጀብደኝነትና ህገ ወጥ በሆነ መልኩ አወጁ፡፡ በሁለት ሳምንት ውስጥ ፋኖን ትጥቁን ብቻ ሳይሆን ቀበቶዉንም እናስፈታለን ብለው ዛቱ፡፡ ፋኖዎች ለሶስት ወር በአስደማሚ ሁኔታ ጥቃቶችን መመከት ብች ሳይሆን ከሐምሌ 20 እስከ ሐምሌ 28 2015 ዓ/ም ባደረጉት የስምንት ቀናት ብቻ ዘመቻ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃንን ጨምሮ ከ46 በላይ ከተሞችን፣ ከመቶ በላይ ወረዳዎችን በመቆጣጠር የህዝብ ኃይል ምን ማለት እንደሆነ አሳዩ፡፡

👉 2ኛ የከሸፈው ዘመቻ

አገዛዙ ደነገጠ፡፡ ቆም ብሎ ፣ሽንፈቶቹን አይቶ የተሽለ አቋም ከመውሰድ፣ ችግሮችን በሰላም ከመፍታት፣ በጥጋቡ ላይ ጥጋብ ጨመረ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ፣ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ሁለተኛ የማጥቃት ዘመቻዉን አወጀ፡፡ በከተሞች ላይ ከባባድ መሳሪያዎች፣ ድሮኖችን እየተኮሰ፣ ከአለም አቀፍ የጦርነት ስነ መግባር ውጭ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የመጨፍጨፍ፣ ታሪካዊ ቅርሶች ለአደጋ የማጋለጥ ተጋብራት መፈጸም ጀመረ፡፡ የጦር ወንጀሎችን፡፡

ሃላፊነት የሚሰማቸው ፋኖዎች፣ የህዝብ ልጆች፣ ከተሞችንና ቅርሶችን ለመጠበቅ ከትላልቅ ከተሞች ለቀው ወጡ፡፡ አገዛዙም፣ “ዘራፊዎችን አሸነፍኩ፣ ክልሉን አረጋጋሁ” ብሎ በሚቆጣጠራቸው ሜዲያዎች ማስወራት ጀመረ፡፡ ተመጻቀ፡፡ ቦፈፈ፡፡

የፍልስተ ጾም፣ በኋላ አዲስ አመት ስለነበረ ፋኖዎች፣ አደረጃጀቶቻቸውን የበለጠ ከማጠናከርና ከመዘጋጅት ባለፈ አዲስ አመት እስኪገባ ድረስ፣ ከመከላከል ያለፈ የማጥቃት ዘመቻ አላደረጉም፡፡

መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ/ም፣ እነ ብርሃኑ ጁላ፣ “አሸንፈናቸዋልን፣ እነርሱን መለቃቀም ነው የቀረን” ያሏቸው ፋኖዎች፣ ሁለተኛ ዙር የማጥቃት ዘመቻቸውን ጀመሩ፡፡ ቀደም ባሉ ዘመቻዎች፣ እንቅስቃሴ ያላደረጉባቸው አካባቢዎች በመዝለቅ፣ በዚያ ያሉ የብልጽግና መዋቅሮችን አፈራረሱ፡፡ በአዊ ዞን፣ በቲሊሊ፣ እንጀባራ፣ ዳንጋላ፣ በሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራና በረከት ወረዳዎች ትላልቅ ድሎች ተቀዳጁ፡፡ የብልጽጋና መዋቅርን አፈራረሱ፡፡ እነ አረርቲን ብቻ ሳይሆን ከሞጆ ቅርብ ርቀት ላይ ያለችው ኢጄሬ ድረስ ዘለቁ፡፡

በምንጃሩ የፋኖ ዘመቻ የተደናገጠው አገዛዙ እጅግ በጣም ከፍተኛ ጦር በምንጃር እስከማሰማራት፣ ከሌሎች አካባቢዎች በስፋት እስከማስመጣት የደረሰበይ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ታንክ፣ ድሮን፣ ከባባድ መስሪያዎችን ሳይቀር በስፋት ተጠቀመ፡፡ ሆኖም፣ ምንጃርን ለማስገበር አልቻለም፡፡ በምንጅር የአገዛዙ ታጣቂዎች በየጊዜው የእሣት እራት እየሆኑ ነው፡፡

👉 3ኛ የከሸፈው ዘመቻ

ከፍተኛ ወታደራዊ ክስረት በሁሉም አቅጣጫ የደረሰባት አገዛዙ ። የመስከረም ዘመቻ በሚል፣ መስከረም ከማለቁ በፊት፣ የፋኖን ጉዳይ ለማጠናቀቅ ወሰነ። እንደገና ከፍተኛ ሰራዊት አሰማራ፡፡ መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ/ም ትልቅ ዘመቻ ከፈተ፡፡ ሆኖም ያሰማራቸውን ታጣቂዎች ከማስጨረሰ ውጭ ምንም ያስመዘገበው ድል የለም፡፡ እንደውም የአገዛዙ አስተማማኝ ቦታ የነበረችው የደሴ ከተማ በፋኖዎች እይታ ውስጥ ወደቀች፡፡ ፋኖዎች በአራት አቅጣጫ ወደ ደሴ እየተቃረቡ ነው፡፡ በደቡብ ምእራብ በኩል ከመንዝ፣ በምእራብ በኩል ወደ ጎጃም በሚወስደው መንገድ በአቃስታ በኩል፣ በሰሜን በወልዲያ ፣ መርሳ፣ ኡርጌሳ፣ ዉጫሌ ሃይቅ መስመር፡፡

👉 4ኛው እየከሸፈ ያለው ዘመቻ

ጥቅምት 25 ቀን 2015 ዓ/ም የተጀመረው አራተኛው ዙር ዘመቻ፣ በዋናነት ያተኮረው ጎጃም ላይ ነው፡፡ ዋና አላማውም፡

አንደኛ፣ በቅርቡ የተቋቋመው፣ በአዲስ አበባ እጅግ በጣም ትልቅ ድንጋጤ የፈጠረው፣ የጎጃም እዝ አመራሮች መቀመጫ ያሉትን፣ ደጋ ዳሞት አካባቢን መቆጣጠር ነበር፡፡ ከተለያዩ የጎጃም አካባቢዎች የመጡ ሻለቃዎች፣ ብርጌዶች በአንድ ላይ ተሰባስበው፣ ተመካከረው፣ አንድ እዝ አቋቁመው ፣ አመራሮች መርጠው ጠንካራ ሆነው የወጡት በደጋ ዳሞት ፈረሰ ቤት ከተማ ነበር፡፡ ፈረሰ ቤትንና እንዳላ ደጋ ዳሞትን ለመቆጣጠር፣ እቅድና ስትራቲጂ ነድፈው፣ ከፍተኛ ከባባድ መሳሪያዎችን አሰማርተው ነው፣ ቢያንስ በአምስት አቅጣጫ ወደ ደጋ ዳሞት ለመግባት የሞከሩት፡፡

ሁለተኛ፣ የደሴ ጎጃም ቁልፍ የአባይ ሸለቆ መስመርን መቆጣጠር ነበር፡፡ ከደሴ፣ በአቃስታ፣ መካነ ሰላም፣ መርጦ ለማርያም፣ ግንደ ወይን ያለውን መስመር፤፡

በጎጃም ዋና ዋና መንገዶች ከሚባሉት ውስጥ ከደጀን ወደ ባህር ዳር የሚወስዱት ሁለት አውራ ጎዳናዎች ናቸው፡፡ አንደኛው ከደጀን አድርጎ፣ በሉማሜ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደንበጫ፣ ጂጋ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ቡሬ፣ እንጀባራ፣ ቲሊሊ፣ ዳንግላ፣ መራዊ፣ መሸንቴ አድርጎ ባህር ዳር የሚገባው ነው፡፡ ሌላው ከደጀን፣ ቢቸና፣ ደብረ ወርቅ፣ ግንደወይን፣ ሞጣ፣ አዴት አድርጎ ባህር ዳር የሚገባው ነው፡፡ ሁለቱ መንገዶች መካከል ሰፊ ግዛት አለ፡፡ የጎጃም እምብርት የሚባል፡፡ የአባይ ወንዝ ምንጭ መነሻ ጊሽ አባይ ያለበት ሰከላ፣ ፈረሰ ቤት፣ ቋሪት የመሳሰሉ ከተሞች ያሉበት፡፡ አዎን የጎጃም እምብርት፡፡

ከጎንደር ሰባ አውቶቢስ የሚሆን ጦር ከአዘዞ ካምፕ ወደ ባህር ዳር እንዲመጣ ተደርጓል፡፡ ከሰሜን ምእራብ እዝ በተጨማሪ እንዳለ የምስራቅ እዝ ጎጃም ገብቷል፡፡ የተወሰኑ ከምእራብና ደቡብ እዞችም መጥተዋል፡፡

1ኛ ♦ በጎጃም ያለውን ሁኔታ በቅርብት የሚከተላለው ጦማሪ ምስጋናው ዘግዮን እንደዘገበው፣ አገዛዙ ወደ ደጋ ዳሞት በዋናነት በቲሊሊ፣ ጅጋ፣ አዴት፣ ደንምበጫና ከሞጣ በቅርበት ላይ ላይ ባሉ አካባቢዎች በኩል ለመግባት እየሞከረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ጦማሪ ተስፋዬ ወልደስላሴ፣ በቲሊሊ አድርጎ ሰከላ ለመግባት ያሰበው የአገዛዙ ሰራዊት ፣ ከፍተኛ ሽንፈት ተከናንቦ፣ ወደ ቲሊሊ መመለስ ብቻ ሳይሆን፣ ከቲሊሊም በመውጣት ወደ ፍኖተ ሰላም እንዲሸሽ መደረጉን፣ ከደምበጫ ወደ ፈረስ ቤት ሲጓዝ የነበረውም፣ የአገዛዙ ጦር ፋኖዎች በቆረጣ ገብተው ጉዳት አድርሰውበት ወደ ኋላ ለማፈግፈግ መገደዱን፣ በሻለቃ ዝናቡ የሚመሩት የደጋ ዳሞት እና ደምበጫ ፋኖዎች በጥምረት ሆነው፣ ከ20 መኪና የአገዛዙን ታጣቂዎች ደምስሰው፣ መኪኖቹን ሙሉ በሙሉ መማረካቸውን ዘግቧል፡፡

2ኛ ♦ በተመሳሳይ ሁኔታ በአዴት በኩል ወደ ቋሪት የመጣዉን የአገዛዙ ጦር በደፈጣ ውጊያ እንደተበታተነ፣ ብዙ ቁስለኞችና ሙርኮኞች አንዳሉም በስፋት እየተዘገበ ነው፡፡

3ኛ ♦ በደሴ ጎጃም መስመር፣ ከፍተኛ ጦር ከወሎ በመካነ ሰላም በኩል፣ እንዲሁም ከግንደ ወይን መርጦ ለማሪያም በኩል፣ በአባይ ሸለቆ ያለውን የፋኖዎች ነጻ አካባቢ ለመቆጣጠር ተሰማርቶ የነበረው፣ ከፍተኛ ሽንፈት እንደተከናነበም፣ ኢትዮ360 ዘግቧል፡፡

4ኛ ♦ የጎጃምን ዘመቻ ለማገዝ ፣ ከባህር ዳር የተንቀሳቀሱ ያገዛዙ ታጣቂዎች፣ በባህር ድርና አዴት መካከል። በጣና ሃይቅ ምእራብ በኩል፣ ከጎንደር ተነስተው፣ ከጯሂት ወደ ጎጃም ለመንቀሳቀስ የሞከሩት፣ ገና ጎጅም ሳይገቡ እዚያ ጎንደር ደምቢያ ላይ በደምቢያ ፋኖዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው፣ ከሞት የተረፉት ወደ ጯሂት ተመልሰዋል፡፡

አሁንም በጎጃም ከፍተኛ ውጊያ እየተደረገ ሲሆን፣ ወደ መሃል ጎጃም እንዲበተን የተደረገው የአገዛዙ ሰራዊት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳለ ነው እየተነገረ ያለው፡፡

5ኛ ♦ ከጎጃም ባለፈ፣ በሰሜን ወሎ ላስታ፣ በላሊበላ አካባቢውም ከፍተኛ ውጊያ እየተደረገ ነው፡፡ በደቡብ ወሎ፣ ከወልዲያ እስከ ደሴ ባለው ዋና አውራ ጎዳና መስመርም ባሉ ከተሞችና ቀበሌዎች፣ ፋኖዎች ያገዛዙን ታጣቂዎች ቁም ስቅላቸውን እያሳስያቸው ነው፡፡

6ኛ ♦ ፋኖዎች በደቡብ ወሎ አድማሳቸው የበለጠ በማስፋትም ፣ ከዋናው አውራ ጎዳና በስተምስራቅ ፣ ከሃራ እስከ ጆምቦልቻ ባለው የባቡር መስመር ቆላማ አካባቢ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ ከምስራቅ አማራ ፋኖ ጋር የተቀላቀለው፣ የባለሽርጦቹ የጊራና ብርጌድ ፋኖ፣ በወረባቦ ወረዳ፣ ከወረባቦ ወረዳ ዋና ከተማ፣ ከቢስቲማ በስተሰሜን ምስራቅ በቅርብ ርቀት ላይ ያላችዋን የቦከክሳ ከተማን እንደተቆጣጠረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቢስቲማ ከሃይቅ ከተማ በስተምስራቅ፣ ከሃይቁ ዳር ላይ ያለች ከተማ ናት፡፡ ከቢስቲማ በሰተደቡብ ደግሞ የምትገኘው ኮምቦልቻ ናት፡፡