
November 8, 2023

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረ መስቀል ጫላ (ዶ/ር)
በናርዶስ ዮሴፍ
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች ውስጥ በ2015 በጀት ዓመት 248 ሚሊዮን ዶላር በማስገባት አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የጫት የወጪ ንግድ ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት፣ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ላይ ተወስዶ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሥር መደረጉ ተገለጸ።
ይህ ውሳኔ የተገለጸው ትናንስ ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረ መስቀል ጫላ (ዶ/ር) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ሒደቱ የኮንትሮባንድ ጫት ንግድ እንዲስፋፋ፣ አገሪቱም ከምርቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን እንዲያሽቆለቁል በማድረጉ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በክልሎች የጫት ላኪነት ንግድ ፈቃድ የተሰጣቸው 4,991 ላኪዎች ሲኖሩ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ ከሦስት ሺሕ በላይ ፈቃዶች በወረዳ ጽሕፈት ቤቶች መሰጠታቸው ተገልጿል። ነገር ግን በ2014 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ጫት የላኩ የንግድ ፈቃድ ባለቤቶች 645 ብቻ እንደሆኑ፣ ከእነዚህም 162 ያህሉ በ2015 በጀት ዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ እንኳን ሳይልኩ መቅረታቸውንና በ2015 በጀት ዓመት የላኪዎቹ ቁጥር አሽቆልቁሎ 486 መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።
ገብረ መስቀል (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹እነዚህ የንግድ ፈቃድ ኖሯቸው ነገር ግን ወደ ውጭ የማይልኩ ድርጅቶች፣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ወደ ሶማሌ ክልል ነው በሚል ከወሰዱ በኋላ፣ በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገር ሶማሊያ በማሻገር ሕጋዊ ላኪዎች ማግኘት የሚገባቸውን እንዳያገኙ፣ አገሪቱም የሚገባትን ያህል የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዳታገኝ ምክንያት እንደሆኑ በጥናት ስለተደረሰበት አዲስ አሠራር ተዘርግቷል፤›› ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ባዋለው የጫት ላኪነት ንግድ ሥራ ፈቃድን በተመለከተ የወጣ የቅድመ ፈቃድ መሥፈርት መሠረት፣ ማንኛውም ጫት ወደ ውጭ መላክ የሚፈልግ ማኅበርም ሆነ ነጋዴ፣ በመሥፈርቱ የተካተቱትን አምስት ነገሮች በማሟላት እንደ አዲስ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መመዝገብ ይኖርበታል።
እነዚህም መሥፈርቶች የጫት ምርት ማጓጓዝ የሚችል መሸፈኛ መረብ ያለውና ጂፒኤስ የገጠመ ተሽከርካሪ ለማቅረብ ግዴታ የሚገባ፣ አዲስ ፈቃድ ጠያቂ ከሆነ በበጀት ዓመቱ ቢያንስ ከ100 ሜትሪክ ቶን ጫት በላይ ለመላክ ግዴታ የሚገባ፣ ነባር ባለፈቃድ ከሆነ ደግሞ ከ100 ሜትሪክ ቶን ጫት በላይ ለመላኩ ማረጋገጫ የሚያቀርብ መሆን አለበት ተብሏል።
የንግድ ፈቃድ አመልካቾች በአገር ውስጥ የጫት ንግድ ሥራ ላይ በማናቸውም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የማይሰማራ መሆኑን ግዴታ የሚገባ፣ በጫት ላኪነት የወጪ ንግድ ሥራ በባንክ የተበላሸ የውጭ ምንዛሪ (Delquent list) ዝርዝር ውስጥ ያልገባ ለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ የሚችል መሆን እንዳለበትም ተጠቅሷል።
ወለሉና ግድግዳው ከኮንክሪት የተሠራ ስፋቱ ከመቶ ሜትር ከፍታው ከአምስት ሜትር ያላነሰ፣ በቀላሉ አየር ማስገባት የሚችል፣ መስኮት ያለው መጋዘን ማቅረብ የሚችል፣ ቀደም ሲል የንግድ ሥራ ፈቃድ ያወጣ ወይም ያደሰ ማንኛውም የጫት ላኪነት የንግድ ሥራ ፈቃድ ያለው ነጋዴ፣ ከጥቅምት 27 እስከ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ቀርቦ አዲስ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት በመውሰድ የንግድ ፈቃዱን ማደስ ይኖርበታል ተብሏል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረ መስቀል (ዶ/ር) ሚኒስትሩ ቅድመ መሥፈርት ለማውጣት የተገደደበትን ሦስት ምክንያቶችን ጠቅሰዋል።
ከጫት የውጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ መሄዱ ተቀዳሚ ሆኖ ሲቀርብ፣ በክልሎች ያሉ ኬላዎች አንድ የጫት መኪና ላይ የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ቀረጥ የማስከፈል ሒደትና የጫት ኮንትሮባንድ ንግድ መፋፋም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን ዕርምጃ እንዲወስድ እንዳስገደደው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከጫት የውጭ ንግድ በ2013 በጀት ዓመት 402.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገብታ የነበረ መሆኑን፣ ይህ መጠን በ2014 ዓ.ም. በአሥር ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ብሎ 392.2 ሚሊዮን ዶላር መድረሱ፣ በ2015 የበጀት ዓመት 248 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲያስገባ፣ ከ2013 የበጀት ዓመት ገቢ ጋር ሲነፃፀር በ144 ሚሊዮን ዶላር ማነሱ ተመላክቷል።
ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ በክልሎች ያሉ ኬላዎች ተደጋጋሚ ቀረጥ የማስከፈል ድርጊት አርሶ አደሩ እጅግ ርካሽ በሆነ ዋጋ እንዲሸጥ አስገድዶት እንደቆየ ገልጸዋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጫት ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆነችው ሶማሊያ ውስጥ ከኬንያ ጫት ጋር በሚደረገው ውድድር፣ የኬንያ ጫት ከሚሸጥበት አራት ዶላር የኢትዮጵያ ጫት ከፍ ብሎ በአሥር ዶላር እንዲሸጥ የራሱን አስተዋጽኦ ሲያበረክት እንደቆየም ተገልጿል፡፡ በአዲሱ አሠራር ወደ ውጭ የሚላክ ጫት በክልሎች ምንም ዓይነት ቀረጥ እንዳይጣልበት ተወስኗል። በሶማሊያ የኢትዮጵያ ጫት ከኬንያ ጫት ጋር ያለው ዋጋ በንግድ ውድድሩ ብልጫ እንዳያገኝ እያደረገው ስለመሆኑ አፋጣኝ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ የገለጹ ሲሆን፣ የጥናት ውጤቱን ተመርኩዞ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢዎች ለመሸጥ ነው በሚል ለውጭ የኮንትሮባንድ ገበያ ለመቅረብ የሚጓጓዙ የጫት ምርቶችን ለማስቆምም፣ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚውለውን የኮታ መጠን በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ እንደሚወሰን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር ኮንትሮባንድን በተለይም በሶማሌ ክልል የድንበር አካባቢዎች፣ በኦሮሚያ፣ በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ የተለያዩ ሥፍራዎች የሚካሄዱ የጫት ኮንትሮባንዶችን ለማስቀረት የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስና የጉምሩክ ጠባቂዎችን ያዋቀረ ኃይል፣ ልዩ ኦፕሬሽኖችን ለማካሄድ ከዓርብ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ፣ ገብረ መስቀል (ዶ/ር) ገልጸዋል።