ድሮን

ከ 6 ሰአት በፊት

የየመን ሁቲ አማፂያን የዩኤስ ወታደራዊ ድሮን መትቶ መጣሉን የአሜሪካ ባለሥልጣናት እና በኢራን የሚደገፈው የሁቲ ንቅናቄ ገልጧል።

የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት እንዳሉት ኤምኪው9 የተባለው ድሮን ተመትቶ የወደቀው በየመን ጠረፍ አቅራቢያ ነው።

የሁቲ ወታደራዊ ንቅናቄ ድሮኑ ተመትቶ መውደቁን አረጋግጠዋል።

ዋሺንግተን በመካከለኛው ምስራቅ በኢራን የሚደገፉ ንቅናቄዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በንቃት እየተጠባበቀች ሳለ ነው ይህ የሆነው።

የአሜሪካ የቅርብ አጋርና የኢራን ባላንጣ የሆነችው እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከሐማስ ጋር ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።

ባለፈው ወር የአሜሪካ ባሕር ኃይል የጦር መርከብ ከየመኑ ሁቲ አማፂያን የተሰነዘረበትን በርካት የክሩዝ ሚሳዔልና የድሮን ጥቃት መመከቱን ገልጦ ነበር።

የእስራኤል-ጋዛ ጦርነትን ተከትሎ አሜሪካ የአየር ኃይል መሣሪዎችን ጨምር በርካታ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ማንቀሳቀሷ ተነግሯል።

የአሜሪካ ወታደሮች በየን እና እስራኤል መካከል በሚገኘው ቀይ ባሕር ላይ ሰፍረዋል።

የየመን ሁቲ አማፂያን በኢራን የሚደገፉ ሲሆኑ ከየመን ኦፊሴላዊ መንግሥት ጋር ለበርካታ ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል።

የየመን መንግሥት የኢራን ተቀናቃኝ በሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ሲረዳ ቆይቷል።

ሌላኛው በኢራን የሚመራው የሌባኖሱ አማፂ ቡድን ሒዝቦላህ ምክትል መሪ በያዝነው ሳምንት እስራኤል በጋዛ የምታደርገው ግድያ በቀጣናው ሰፊ ጦርነት እንዲነሳ ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሼኽ ናይም ቃሲም እንዳሉት “በቀጠናው በጣም አደገኛ ክስተቶች እየታዩ ነው፤ ምላሹን ደግሞ ማንም ሊያቆም አይችልም።”

በሌላ በኩል አሜሪካ ረቡዕ ዕለት እንደገለጠችው በምስራቃዊ ሶሪያ በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብና አጋር ድርጅቶች ጥቅም ላይ የሚውሉ ሥፍራዎች ላይ የአየር ድብደባ ፈፅማለች።

የፔንታገን ባለሥልጣን እንደገለጡት በቅርብ ሳምንታት ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው የአየር ድብደባ በኢራቅና በሶሪያ የአሜሪካ ሠራዊት ላይ ለደረሰው ጥቃት ምላሽ ነው።

የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት አየር ደብደባው በኢራን የሚደገፈው የሶሪያ አማፂ ቡድን ዘጠኝ አባላትን ገድሏል ቢልም መረጃው በገለልተኛ አካል አልተጣራም።