
ከ 3 ሰአት በፊት
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየፈፀመችው ያለችው ግድያ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሊዛመት ይችላል ሲሉ በኢራን የሚደገፈው የጠንካራው የሄዝቦላህ ምክትል አዛዥ አስጠነቀቁ።
ሼክ ናይም ቃሴም ለቢቢሲ እንደተናገሩት “በአካባቢው በጣም አሳሳቢ እና በጣም አደገኛ ክስተቶች ሊፈጠሩ ከመቻላቸውም በላይ ማንም መዘዙን ሊያስቆም አይቻለውም” ብለዋል።
የሄዝቦላህ ምክትል መሪ በቤይሩት ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህንን ሲናገሩ፤ በጋዛ የሚገኘውና በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።
የእስራኤል ጥቃት የጀመረችው መስከረም 26 ሐማስ ባደረሰው ጥቃት 1 ሺህ 400 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነው።
“ከፍተኛ አደጋ ተደቅኗል። እስራኤል በሠላማዊ ዜጎች ላይ የምታደርገውን ጥቃት እያሰፋች እና ሴቶችን እና ህጻናትን እየገደለች ነው። ይህ ሁኔታ በአካባቢው አደጋ ሳያስከትል ሊቀጥል እና ሊጨምር ይችላልን? አይመስለኝም” ብለዋል።
የትኛውም የግጭት መባባስ ከእስራኤል ውሳኔ ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ገልጸዋል። “እያንዳንዱ ውሳኔ የራሱ ምላሽ ይኖረዋል” ብለዋል።
ሄዝቦላህ “የአምላክ ፓርቲ” በርካታ ዕድሎች አሉት።
- በላሊበላ በከባድ መሳሪያ ጭምር የሚካሄደው ውጊያ ለቅርሶች ደኅንነት ስጋት ሆኗልከ 6 ሰአት በፊት
- ከጦርነቱ በኋላ እስራኤል ጋዛን ይዛ መቆየት እንደሌለባት አሜሪካ አስጠነቀቀች5 ህዳር 2023
- ‘ልጄ መናገር አልጀመረም፤ ምን ማድረግ ይሻለኛል?’ከ 6 ሰአት በፊት
በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ እና በአረብ ሊግ በአሸባሪነት የተፈረጀው የሺአው ኢስላማዊ ቡድን በሊባኖስ ትልቁ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ሃይል ነው።
ቡድኑ እስካሁን ድረስ በጋዛ ጦርነት ላይ የሰጠው ምላሽ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የተገደበ ነው። እርምጃዎቹንም በጥንቃቄ ማስኬድን መርጧል።
እስራኤል እሑድ በደቡብ ሊባኖስ በሰነዘረችውው ጥቃት አንዲት ሴት እና ሶስት ህጻናትን ስትገድል፤ ሄዝቦላህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሮኬቶችን ተጠቅሞ አንድ እስራኤላዊ ገድሏል።
የሄዝቦላህ መሪ ሃሰን ናስራላህ በሊባኖስ የሚፈጸም እያንዳንዱ የሠላማዊ ሰው ሞት ከድንበር ባሻገር ተመሳሳይ ምላሽ እንደሚሰጠው ዝተዋል። ከእስራኤል ጋር ሁሉን አቀፍ ጦርነት ወደ መግባት ግን ምንም አላስፈራሩም።
“ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው” ያለው ቡድኑ በድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች ተወስኖ በዋናነት ወታደራዊ ዒላማዎችን በማጥቃትላይ ይገኛል።
ከ60 በላይ ተዋጊዎቹ ቢገደሉም እነሱን መተካት የሚችሉ በጦርነቱ ጥርሳቸውን የነቀሉ ደጋፊዎች አሉት። በዚህ ሳምንት በቤይሩት የተቀበረ አንድ ተዋጊ አምስተኛው ከቤተሰቡ ለሄዝቦላህ ህይወቱን አሳልፎ የሰጠ ተዋጊ ሲሆን ምን ያህል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደተላለፈ ያሳያል ተብሏል።
ምንም እንኳን እስራኤልን ለማጥፋት ቁርጠኛ ቢሆንም እና እአአ በ 2006 ድንበር ተሻግሮ ሁለት ወታደሮችን በማገት ከእስራኤል ጋር ጦርነት ከፍቶ የነበረ ቢሆንም በቃለ መጠይቁ ወቅት የድርጅቱ ምክትል መሪ ሄዝቦላህን እንደ መከላከያ ድርጅት ለማሳየት ሞክረዋል።
ሼክ ቃሴም እንዳሉት ከሆነ እስራኤል “በጋዛ ላይ ጥቃትን የጀመረችው አስከፊ በሆነ መንገድ ነው።”
ቢቢሲ መስከረም 26 እስራኤልን ያጠቃው ሐማስ መሆኑን ቢገልጽም ምክትል መሪው እስራኤል የፍልስጤም መሬቶችን ስለያዘች የተሰጠ አይቀሬ ጥቃት ነው ብለዋል።
ሐማስ ሳይሆን የእስራኤል ጦር በርካታ የእስራኤል ሠላማዊ ዜጎችን ገድሏል የሚል መሰረተ ቢስ አባባል ደጋግመዋል። የሐማስ ታጣቂዎች በቆባቸው ላይ በነበረው ካሜራ ሠላማዊ ሰዎችን ሲገድሉ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስልስ?
“ለምን እስራኤል ጋዛ ውስጥ የሠራችውን አንመለከትም። ሲቪሎችን ከመግደል ባለፈ ቤቶችን አውድማለች” ሲሉ በጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።
የሐማስ ጥቃት የፍልስጤማውያን ጭቆናን አልቀበልም ባይነት ውጤት ነው ሲሉ ገልጸዋል። መዘዙ የከፋ መሆኑን ግን አስተባብለዋል። ከዚያን በኋላ የተገደሉት 10 ሺህ ጋዛውያንስ? “በእስራኤል የተፈጸመው እልቂት ፍልስጤማውያን መሬታቸውን የሙጥኝ እንዲሉ የበለጠ እያነሳሳው ነው” ሲሉ መልሰዋል።
ኢራን ሄዝቦላህን “እንደምትደግፍ እና የገንዘብ ድጋፍ እንደምታድርግ” ቢያምኑም፤ ጥቃት እንዲፈጸም አላዘዙም ብለዋል። ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ግን ሁሉን አቀፍ ጦርነት ውስጥ ለመሳተፍ ወይም ላለመሳተፍ የምትወስነው ቴህራን ነች።
እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር ተጨማሪ ጦርነት ከከፈተች ከአብዛኞቹ አገራት የበለጠ መሳሪያ ካለው ጠላት ጋር ትገጥማለች። ታጣቂው ቡድን 150 ሺህ የሚገመቱ ሮኬቶች እና ሚሳኤሎች በመያዝ ከሐማስን አንጻር ትልቅ ጦር መሆኑን አሳይቷል።
መቀመጫውን በቤይሩት ያደረገው የመከላከያ እና የደህንነት አማካሪው ኒኮላስ ብላንፎርድ እንደሚለው ከሆነ ሄዝቦላህን ልዩ ሃይሎችን፣ መደበኛ ተዋጊዎችን እና ተጠባባቂዎችን ጨምሮ 60 ሺህ ያህል ተዋጊዎች አሉት።