
ከ 5 ሰአት በፊት
የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብሔራዊ መታወቂያ ካርድ ለማውጣት ዜጎች ክፍያ እንዲፈጽሙ መንግሥት ያወጣውን መመሪያ አገደ።
የኬንያ መንግሥት ይህን መመሪያ ማውጣቱን ተከትሎ ዜጎች ቅሬታቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
ማጋሬ ጊኬንይ የተባሉ ሐኪም ናቸው መንግሥት አዲሱን መመሪያ ያወጣው “ድንገተኛ እና ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ” ነው ሲሉ የሕዝብ ድምፅ በማሰባሰብ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት።
የተሰበሰበው የሕዝብ ድምፅ እንደሚለው በአዲሱ መመሪያ መሠረት “በርካታ ዜጎች መታወቂያ ካርድ በቀላሉ ማግኘት አይችሉም።”
ከዚህ ቀደም በነፃ ይሰጥ የነበረው ብሔራዊ መታወቂያ ካርድ አሁን 1 ሺህ ሺልንግ [370 ብር ገደማ] እንዲሆን መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አዟል።
መታወቂያ ለማሳደስ ደግሞ ኬንያዊያን 2 ሺህ ሺልንግ እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል።
ኬንያዊያን እያሻቀበ ባለው የኑሮ ግሽበት ምሬታቸውን እየገለጡ ባሉበት ወቅት ነው መንግሥት ገቢውን ለማሳደግ ሲል ዜጎች ከዚህ ቀደም በነፃ አሊያም በርካሽ የሚያገኟቸውን አገልግሎቶች በበለጠ ክፍያ እንዲሆን ያደረገው።
በርካታ ኬንያዊያን በሚከፍሉት ግብር አማካይነት ተግባራዊ እየሆኑ ላሉ የመንግሥት ግልጋሎቶች ተጨማሪ ክፍያ መጠየቃችን ተገቢ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።
በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት መባቻ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ መንግሥት የጫናቸውን ግብሮች በመቃወም በጠራዊ ሃገር አቀፍ ሰልፍ ምክንያት 24 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
- የመንግሥት ኃይሎች ላሊበላ ከተማን መልሰው መቆጣጠራቸው ተነገረ9 ህዳር 2023
- ኳታር ምዕራባውያን አሸባሪ ያሉትን ሐማስ ለምን አስጠለለች? ማደራደሩስ ይሳካላታል?ከ 6 ሰአት በፊት
- በምዕራብ ሐረርጌ የባለቤቱን መራቢያ አካል በእሳት ያቃጠለው በጽኑ እስራት ተቀጣከ 6 ሰአት በፊት
አዲሱ መመሪያ መታወቂያ ካርድ ብቻ ሳይሆን ፓስፖርት፣ የጋብቻ ወረቀት፣ የሥራ እና የመኖሪያ ፈቃድ እንዲሁም የልደት እና ሞት ምስክር ወረቀት ለማውጣትም ክፍያ ይጠይቃል።
አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት አሊያም ለማሳደስ ይጠየቅ የነበረው ክፍያ 50 በመቶ ሲያድግ የልደት እና ሞት ወረቀት ለማውጣት የሚጠየቅ ክፍያ በአራት እጥፍ አድጎ 200 ሺልንግ ገብቷል።
መንግሥት በተጨማሪ ዜግነት አሊያም የመኖሪያ ፈቃድ ለማስጠት የሚጠይቀውን ክፍያ እጥፍ አድርጎታል።
ከኬንያዊያን ዜጎች በውጭ ሃገር የተወለዱ ልጆች የኬንያ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቁት ክፍያ 1 ሚሊዮን ሺልንግ ሆኗል።
በደንገት የተጫኑት የክፍያ መመሪያዎች አቅም የሌላቸው ዜጎች የመንግሥትን ግልጋሎት ተጠቅመው አስፈላጊ ወረቀት ለማግኘት ሊቸገሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ጭሯል።
“ቀልዱን እንተወውና ለመታወቂያ ካርድ ክፍያ መጠየቁ የተወሰኑ ሰዎች አቅም ስለሌላቸው ለምርጫ መመዝገብ አይችሉም ማለት ነው። ይህ ደግሞ የመምረጥ መብታቸው ተነፈገ ማለት ነው” ሲል አንድ ግለሰብ ኤክስ ላይ አስተያየቱን አስፍሯል።
እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ከሆነ 27 በመቶ ኬንያዊያን ከድኅነት ወለል በታች ይኖራሉ። የቀን ገቢያቸው ደግሞ ከ2.15 ዶላር በታች ነው።
ከዜጎች ባለፈ አንዳንድ ፖለቲከኞች አዲሱን መመሪያ ሲቃወሙ የተወሰኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደግሞ በመመሪያው እንደማይማሙ ገልጠዋል።
የዳያስፖራ ጉዳዮች ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሮዜሊን ንጆጉ ከኬንያዊያን ለሚወለዱ ሕፃናት ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለመስጠት የወጣው የክፍያ መመሪያ “በስህተት የገባ ነው” ይስተካከላል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት መስከረም ወደ ሥልጣን የመጡት የፕሬዝደንት ሩቶ መንግሥት በርካታ የግብር ዓይነቶችን ዜጎች ላይ የጣለ ሲሆን የነዳጅ ዋጋ ከፍ እንዲልም አድርጓል።
የብሔራዊ ፓርክ መግቢያ ዋጋን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት አገልግሎቶች ክፍያ ከፍ እንዲልም ሆኗል።
ባለፈው ሳምንት የገቢዎች መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት ወደ ኬንያ የሚመጡ ዜጎችም ሆኑ ጎብኝዎች ከ500 ዶላር በላይ ተመን ያለው ዕቃ ይዘው ከተገኙ ይቀረጣሉ ማለቱ ተቃውሞ ገጥሞታል።
ፕሬዝደንት ሩቶ እስካሁን ስለ ዋጋው ጭማሪ ያሉት ነገር ባይኖርም ሐሙስ ዕለት ለሃገሪቱ ዜጎች ባስተላለፉት መልዕክት ኬንያዊያንን ከዕዳ ጫና ለማላቀቅ “ቀላል ያልሆኑ ግን አስፈላጊ” ውሳኔዎችን ለመውሰድ ተገድጃለሁ ብለዋል።