
ከ 4 ሰአት በፊት
የእስራኤል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሊሰነዝር መሆኑን ቀድመው የሚያውቁ መቀመጫቸውን በጋዛ ያደረጉና ለምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን የሚሠሩ አራት ጋዜጠኞች እንደነበሩ አስታወቀ።
ሚንስትሩ ሽሎሞ ካርሂ ለሮይተርስ፣ ለኤፒ፣ ለሲኤንኤን እና ለኒውዮርክ ታይምስ “በድርጅታችሁ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች… ስለእነዚህ አሰቃቂ ድርጊቶች ቀደም ብለው ያውቁ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።
ሮይተርስ፣ ኤፒ፣ ሲኤንኤን እና ኒውዮርክ ታይምስ ስለ ጥቃቱ ቀድመው እንደማያውቁ ገልጸዋል።
እንዲህ ያሉ “መሠረተ ቢስ ውንጀላዎች” ባለሙያዎችን አደጋ ላይ ይጥላሉ ሲል ኒውዮርክ ታይምስ አክሎ አስታውቋል።
ሃማስ መስከረም 26 በደቡባዊ እስራኤል ያልተጠበቀ ጥቃት ከፍቶ ከ1400 በላይ የእስራኤል ሲቪሎች እና ወታደሮችን ሲገድልእና ከ240 በላይ ሰዎችን አግቷል።
ጥቃቱ በተፈጸም ዕለት መገናኛ ብዙሃን የሚቃጠል የእስራኤል ታንክ፣ የሐማስ ታጣቂዎች የእስራኤል ድንበርን ጥሰው ሲገቡ እንዲሁም እና የጥቃቱ ሰለባዎችን የሚያሳዩ ምስሎች ይፋ አድርገው ነበር።
ካርሂ ጥቃቱ የተፈፀመው ፎቶግራፍ አንሺዎች በተገኙበት ወቅት መሆኑን ገልፀው፤ “እነዚህን አስፈሪ ድርጊቶች በመዘገብ እና አሰቃቂ ክስተቱ ውጤታማ እንዲሆን ተሳታፊ ሆነዋል” በማለት ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃኑን ተችተዋል።
ይህ የተባለው የፎቶግራፍ አንሺዎቹ በቦታው መገኘት “የዕቅዱ አካል” ሊሆን እንደሚችል የእስራኤል ደጋፊ የሆነው ኦነስት ሪፖርቲንግ ድረ-ገጽ ያቀረበውን ሀሳብ ተከትሎ ነው።
የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባል የሆኑት ቤኒ ጋንትዝ በበኩላቸው የፎቶ ጋዜጠኞቹ የመስከረም 26ቱን ጥቃት አስቀድመው እንደሚያውቁ ከተረጋገጠ እንደ አሸባሪ ሊቆጠሩ ይገባል ብለዋል።
ከጥቃቱ በኋላ መንግሥትን የተቀላቀሉት የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩት ጋንትዝ፣ “ጋዜጠኞች ስለ ጭፍጨፋው ቀድመው አውቀው ህጻናት ሲጨፈጨፉ ተመልካች ሆነው መቆምን ከመረጡ ከአሸባሪዎቹ ስለማይለዩ በተመሳሳይ መንገድ መስተናገድ አለባቸው” ሲሉ ኤክስ ላይ አስፍረዋል።
- በምዕራብ ሐረርጌ የባለቤቱን መራቢያ አካል በእሳት ያቃጠለው በጽኑ እስራት ተቀጣከ 6 ሰአት በፊት
- ኬንያዊያን መታወቂያ ለማውጣት እንዲከፍሉ መንግሥት ያወጣውን ትዕዛዝ ፍርድ ቤት አገደከ 5 ሰአት በፊት
- ኳታር ምዕራባውያን አሸባሪ ያሉትን ሐማስ ለምን አስጠለለች? ማደራደሩስ ይሳካላታል?ከ 6 ሰአት በፊት
የገዢው ሊኩድ ፓርቲ የፓርላማ አባል ዳኒ ዳኖን በበኩላቸው ጋዜጠኞቹ በጥቃቱ ውስጥ በመሳተፋቸው እንዲገደሉ ከተለዩ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እንደሚካተቱ ተናግረዋል። በሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ውስጥ የኮማንዶ አባላትን ለመከታተል እና ለመግደል የሚያገለግል ክፍል መቋቋሙን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሮይተርስ፣ ኤፒ፣ ሲኤንኤን እና ኒውዮርክ ታይምስ በጉዳዩ ላይ ባወጡት መግለጫ ጋዜጠኞቹ ፎቶ እንዲያቀርቡ አስቀድሞ የተደረገ ምንም አይነት ዝግጅት አልነበረም።
“ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅት የኤ.ፒ.ኤ ሠራተኛ በድንበር ላይ አልነበረም። የትኛውም የኤፒኤ ሠራተኛ በማንኛውም ጊዜ ድንበር አልተሻገረም” ሲል ኤጀንሲው በመግለጫው አስታውቋል።
“የፍሪላንስ ፎቶዎችን ስንቀበል የምስሎቹን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ትልቅ ጥንቃቄ እናደርጋለን።”
ኤጀንሲው ቀደም ሲል ፎቶው ከሐማስ የጋዛ መሪ ያህያ ሲንዋር ጋር ከታየው ጋዜጠኛ ሃሰን ኢስላያ ጋር አብሮ መሥራት እንዳቆመ ገልጿል። ሲ ኤን ኤንም በተመሳሳይ ከኢስላያ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያቋርጥ ተናግሯል።
ድርጅቱ አክሎም ስለ ጥቃቶቹ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለው አስታውቋል።
ኒውዮርክ ታይምስ በበኩሉ ክሱን “ከእውነት የራቀ እና የማይረባ” ሲል ገልጾታል።
“በእስራኤል እና በጋዛ ያሉ ጋዜጠኞችን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እንዲህ አይነት ውንጀላ ማቅረብ ግድ የለሽነት ነው” ሲል በመግለጫው አስታውቋል።
“ዘ ታይምስ የመስከረም 26ቱን ጥቃት እና ጦርነቱን በፍትሃዊነት፣ በገለልተኝነት እና በግጭቱ ውስብስብነት በሚያሳይ መልኩ በሰፊው ዘግቧል።”
ሮይተርስ ስለ ጥቃቱ አስቀድሞ የሚያውቀው ነገር ስለመኖሩ ወይም በመስከረም 26ቱ ጥቃት “ጋዜጠኞቹን ከሐማስ ጋር አካተዋል መባሉን” አስተባብሏል።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ) ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በትንሹ 39 ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሠራተኞች ተገድለዋል ብሏል። ከእነዚህም መካከል 34 ፍልስጤማውያን፣ አራት እስራኤላውያን እና አንድ ሊባኖሳዊ ይገኙበታል።