
ከ 6 ሰአት በፊት
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት ከ1400 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከ200 ሰዎች በላይ አግቶ ወስዷል።
ታጋቾቹን የማስለቀቁ ተግባር ለትንሿ በነዳጅ የበለጸገች አገር ኳታር ተሰጥቷል።
የሐማስ አንዱ ቢሮ የሚገኘው በኳታር ነው።
ከአረብ አገራት ለምዕራባውያን ቅርብ አጋር እንደ ኳታር ያለ ብዙም የለም።
አሁን የታጋቾቹ ሕልውና በኳታር እጅ ላይ የወደቀ ይመስላል? ለምን?
ምክንያቱም ኳታር በዚህ ውጥንቅጥ ልዩ ስፍራን ትይዛለች። የሁለት በነፍስ የሚፈላለጉ ቡድኖች ‘ወዳጅ’ አገር ናት። በሁለት ጠላቶች እምነት የሚጣልባት ሆናለች።
ጆ ባይደንም ሆነ ሪሺ ሱናክ ኳታርን አድንቀዋል።
የኳታርን ኢሚር “ውለታዎ አለብን” ብለዋል። ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እና አሜሪካ ብቻ አይደሉም ለኳታር ዕውቅናን የሰጡ መሪዎች። የእስራኤሉ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ለኳታር ያላቸውን አድናቆት አልሸሸጉም።
ኳታር መደማመጥ፣ ትዕግስት እና መነጋገር ካለ ታጋቾቹ ይለቀቃሉ የሚል ጠንካራ እምነት አላት።
ነገር ግን የእስራኤል ወደ ጋዛ እግረኛ ጦር መግባት ድርድሩን አጣብቂኝ ውስጥ መክተቱ አይቀርም።
የኳታር ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ የሚለቀቁት ታጋቾች ጥምር ዜግነት ያላቸው ወይም የእስራኤል ዜግነት የሌላቸው ነው የሚሆኑት።
ሐማስ የእስራኤል ዜጎች እና ወታደሮችን ለመልቀቅ በርካታ በእስራኤል እስር ቤት የሚገኙ አባሎቹ እንዲለቀቁ መደራደሪያ እንደሚያደርጋቸው ይገመታል።
ይህ ደግሞ ኳታርን የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ ይከታታል።
አሰቃቂው የሐማስ ጥቃትን ተከትሎ ብዙ ሰዎች አንድ ጥያቄ ይጠይቃሉ።
ኳታር ዋንኛ የምዕራባውያን አጋር ሆና፣ የአሜሪካ ጦር ሰፈር የሚገኝባት አገር ሆና ስለምን በብዙ አገሮች አሸባሪ ተብሎ ለተፈረጀ ቡድን መጠለያ ትሆናለች?
ይህን ጥያቄ ቆየት ብለን እንመለስበታለን።
ይሁንና ኳታር በማደራደሩ ተግባር ባይሳካላት ፈተና ውስጥ ልትገባ ግድ ይሆናል።
ሐማስ ታጋቾቹን ለመልቀቅ አሻፈረኝ ካለ ወይም ኳታር ሐማስን በዚህ ረገድ ማሳመን ካልቻለች ምናልባት ምዕራባዊያን የሐማስ የዶሓ ቢሮውን እንድትዘጋ በኳታር ላይ ጫና ሊያደርሱባት ይችላሉ።
ለዚህም ነው ይህ ድርድር ለኳታር ስሱ ጉዳይ የሚሆነው።
ጋዛ ለ2.3 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን መኖሪያ ናት። ሐማስ ይህን ሰርጥ ከ2017 (እአአ) ጀምሮ ያስተዳድራል።
ጋዛ 24 ሰዓት በሚባል መልኩ በአየር እየተደበደበች ነው።
እስከ አሁን ከ5ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ይህ አሐዝ ግን ሐማስ በሚያስተዳድረው ጤና ሚኒስቴር የተገለጸ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ተኩስ አቁም ይደረግ እያለ ይጎተጉታል።
እስራኤል ሐማስን ከምድረ ገጽ ሳላጠፋ አልመለስም ስትል ዝታለች። ሐማስ በዩኬ፣ በአሜሪካ እና በሌሎች አገሮች አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ድርጅት ነው።
ስለዚህ አሸባሪ የተባለውን ድርጅት እና እስራኤልን ሊያደራድር የሚችል ከኳታር የተሻለ አገር የለም ማለት ይቻላል።
- እስራኤል ሌሊቱን ባካሄደችው ጥቃት በርካታ የሐማስ ተዋጊዎችን መግደሏን ገለጸች29 ጥቅምት 2023
- አፄ ኃይለ ሥላሴን የሚዘክር ዝግጅት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ተካሄደ30 ጥቅምት 2023
- በአርጩሜ ገላቸው እስኪተለተል የሚገረፉት የኬንያ ተማሪዎች ሰቆቃ30 ጥቅምት 2023
ድርድሩ የሚካሄደው እንዴት ነው?

ሐማስ በኳታር ዋና ከተማ ዶሓ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2012 ጀምሮ ቢሮ አለው። የሚመራው ደግሞ በኢስማኤል ሐኒያህ ነው።
ድርድሩን የሚመሩት የኳታር ዲፕሎማቶች ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተውጣጡ ናቸው። ለዚህ ዓይነቱ የማደራደር ተግባር አዲስ አይደሉም።
አባላቱ ሰብአዊ እርዳታ እንዲሁም የጋዛን መሠረተ ልማት ለማስቀጠል በየዓመቱ ኳታር የምትሰጠውን ልገሳ የሚያስተባብሩም ናቸው።
በርካታ አደራዳሪዎች ጋዛን በአካል ያውቋታል። ከሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ጋር እውቂያ አላቸው።
ምንም እንኳ በ1990ዎቹ የእስራኤል ንግድ ቢሮ ብትከፍትም፤ ከጎረቤቶቿ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ባሕሬን በተለየ ኳታር ከእስራኤል ጋር መደበኛ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት የላትም።
ነገር ግን ኳታር ከእስራኤል ጋር በጓሮ በር ግንኙነቶችን ታደርጋለች። በተለይም እንዲህ ዓይነት የእገታ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ከእስራኤል ወኪሎች ጋር የስልክ ግንኙነት ታደርጋለች።
አንዳንድ ተንታኞች ሐማስ ታጋቾቹን ከእጁ በቶሎ ለመልቀቅ ይሻል። “ለስማቸው ጥሩ አይደለም” ይላሉ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ጀስቲን ክራምፕ።
ከዚህም ባሻገር በርካታ ቁጥር ያላቸውን ታጋቾች መቀለብ፣ መንከባከብ እና ደኅንነታቸው መጠበቅ በሐማስ ሎጂስቲክ ፈታኝ ይሆንበታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሐማስ ባገታቸው ሰዎች የተነሳ ጊዜ መግዛት ይሻል። ፋታ ማግኘት ይፈልጋል።
ምክንያቱም የታጋች ቤተሰቦች በእስራኤል መንግሥት እና በሌሎች አገራትም ላይ ነገሩ በሰላም እንዲያበቃ ጫና ማድረጋቸው አይቀርም። ወደ ጋዛ የመግባቱ ነገር ሊዘገይ የቻለውም አንዱ ምክንያት በዚህ የተነሳ ነው ይላሉ።
እንደሚፈራው ከሆነ የእግረኛ ጦር ወደ ጋዛ ጠልቆ መግባት ድርድሩ ባለበት እንዲረግጥ ያደርገዋል።
ሐማስ እነዚህን ታጋቾች በዋሻዎች ውስጥ እንደደበቃቸው ይገመታል።
እስከ አሁን የተለቀቁት ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ነው ተላልፈው የተሰጡት።
ነገር ግን 50 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ታጋቾችን ለማስረከብ ሐማስ ቢያንስ ያለማቋረጥ በጋዛ ላይ የሚካሄደው የአየር ጥቃት ጋብ እንዲልለት ይሻል። ጋብ ማለት ብቻም ሳይሆን የተኩስ አቁም እንዲደረግም መጠየቁ አይቀርም።
ይሁንና የኔታንያሁ መንግሥት በጭራሽ ይህ እንዲሆን አይሻም። ሐማስን ትንፋሽ መስጠት አይፈልግም። ተልዕኮውም ጨርሶውኑ ከምድረ ገጽ ማጥፋት ነው።

የኳታር የአደራዳሪነት ልምድ
ይህ ሐማስ እና እስራኤልን የማደራደሩ ተግባር ለኳታር አዲስ አይደለም።
ኳታር ከዚህ ቀደም ጊዜያዊ የታሊባን ኤምባሲ በዶሐ እንዲከፍት ፈቅዳ ነበር።
አሜሪካ ከታሊባን ጋር መደራደሪያ መስኮት ማግኘት የቻለችውም በዚሁ ቢሮ አማካኝነት ነው።
የዶሓ ነዋሪዎች ዛሬም ድረስ የታሊባን መሪዎች በዶሓ ውድ የገበያ ማዕከላት ከባለቤቶቻቸው ጋር ገበያ ሆነው ሲወጡ ያስታውሳሉ።
በረዣዥም ሪዛቸው እና አለባበሳቸው ይለይዋቸዋል።
ኳታር የደኅንነት ቁልፍ ሰዎቻቸውን በመጠቀም በኢራቅ እና በሶሪያ አይሲስ ያገታቸውን ምዕራባውያንን ለማስለቀቅ ቁልፍ ሚና ነበራቸው።
በቅርቡ ደግሞ ኳታር አራት ዩክሬናውያን ሕጻናት ለአገራቸው እንዲበቁ አድርጋለች። ልጆቹ በሩሲያ ታግተው የነበሩ እንደሆኑ ነው የተነገረው። ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በቀጥታ መነጋገር ስለማትችል ውክልናውን የሰጠው ለኳታር ነበር።
እነዚህ እና ሌሎች በርካታ አጋጣሚዎች ኳታር ቁልፍ የማደራደር ሚና እንዳላት የሚመሰክሩ ናቸው።
አሁን ኳታር ቁልፍ የሚባል ሚና እንድትጫወት ይጠበቃል።
ፍልስጤማውያን ለተኩስ አቁም ተስፋ ያደርጉባታል። ምዕራባዊያን የታገቱትን በሙሉ በሰላም እንድታስመልስላቸው ይጓጓሉ።
ያቺ ትንሽ አገር ከእነዚህ ትልልቅ ተስፋዎች የቱን ያህሉን እንደምታሳካ ጊዜ የሚነግረን ይሆናል።