
ከ 6 ሰአት በፊት
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን አንድ ባል ከሚስቱ ጋር የተፈጠረን አለመግባባት ምክንያት በማድረግ የባለቤቱን መራቢያ አካል ሆን ብሎ በጭካኔ በእሳት በማቃጠል በቀረበበት ክስ በጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተፈረደበት።
ይህ ዘገባ የአንባቢዎችን ስሜት ሊረብሽ ይችላል።
ለተጎጂዋ እና ለቤተሰቧ ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ደኅንነት ሲባል ቢቢሲ የተጎጂዋንም ሆነ የባለቤቷን፣ እንዲሁም የምትኖርበትን አካባቢ ስም ከመጥቀስ ተቆጥቧል።
ተከሳሹ “የሁለት ልጆቹ እናት የሆነችውን ሚስቱን የመራቢያ አካል በማቃጠል ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ፈጽሟል” ሲሉ የወረዳው ፖሊስ ወንጀል መርማሪ የሆኑት ሳጅን አሕመድ ሱፊያን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ድርጊቱ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 4/2015 ዓ.ም. የተፈጸመ ሲሆን፣ ግለሰቡ ጥቃቱን ለመፈጸሙ ምክንያት የሆነው “ከባለቤቱ ጋር ‘አብረሺኝ ተኚ፣ አልተኛም’ በሚል ከተጨቃጨቀ በኋላ” መሆኑን የፖሊስ የምርመራ መዝገብ አመልክቷል።
- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ወንድማቸውን የገደሉት እህትማማቾች በእስራት ተቀጡ26 ጥቅምት 2023
- በምሥራቅ ሐረርጌ በውርስ ምክንያት አባቱን በመግደል የተጠረጠረው በቁጥጥር ሥር ዋለ9 ህዳር 2023
- በጅግጅጋ በደቦ ተደፍራ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችው የ11 ዓመት ታዳጊ አባት “ፍትሕን እሻለሁ” አሉ31 ነሐሴ 2023
በዚህም ሳቢያ ተከሳሽ የሚስቱን የመራቢያ አካል እና ከፊል ጭኗን እና ከኋላዋ በኩል በእሳት በማቃጠል ከፍተኛ ጉዳት አድርሶባታል ብለዋል ጉዳዩን ይዘውት የነበረው መርማሪ ፖሊስ።
“በገጠር አካባቢ በቤት ውስጥ ፍልጥ እንጨት ማንደድ እና እሳቱ ተዳፍኖ እንዲቆይ ማድረግ የተለመደ ነው። ተከሳሹም አለመግባባቱ ሲፈጠር እሳት የያዘ ፍልጥ እንጨት ከእሳት ውስጥ አውጥቶ የአካሏን የተለያዩ ክፍሎች አቃጥሏል” ብለዋል ሳጅን አሕመድ።
በባለቤቱ ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰው የ21 ዓመቱ ወጣት ወንጀሉን ከፈጸም ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በአካባቢው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ምርመራ ተደርጎበት ጉዳዩ በአካባቢው ፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል።
ተከሳሹ የፈጸመው ወንጀል በሰው እና በሕክምና ማስረጃ ከተረጋገጠ በኋላ የወረዳው ፍርድ ቤት ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በአምስት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፈርዶበታል።
ግለሰቡ የፈጸመው ድርጊት በባለቤቱ ላይ ከባድ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳትን ከማስከተሉ በላይ የማኅብረሰቡን እሴት የጣሰ በመሆኑ የተላለፈበት ብይን ለሌሎች አስተማሪ ነው ሲሉ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት መርማሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በባለቤቷ በተፈጸመባት ጥቃት ጉዳት የደረሰባት ሴትም ባለፉት ወራት የሕክምና ድጋፍ እና ክትትል አግኝታ አሁን ላይ በጤናዋ ላይ መሻሻል እያሳየች መሆኑን ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።