
ከ 1 ሰአት በፊት
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም እና በአገሪቱ ምዕራባዊ ክልል ዳርፉር ውስጥ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ።
በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል አዲስ በተቀሰቀሰው እና ሐሙስ ዕለት በተባባሰው ውጊያ ምክንያት በኦምዱርማን ከተማ ጎዳናዎች ላይ አስከሬኖች ወድቀው እንደሚገኙ የዐይን እማኞች ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ተናግረዋል።
“ትናንት ሐሙስ ከተካሄደው ውጊያ በኋላ ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች አስከሬኖች በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል በሚገኙ ጎዳናዎች ላይ ወድቀው ይገኛሉ” በማለት አንድ የዐይን እማኝ ተናግሯል።
በሱዳን ምዕራባዊ ክፍል በምዕራብ ዳርፉር ግዛት ውስጥ ደግሞ በተካሄዱ ግጭቶች 700 የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) መግለጹን ድርጅቱ ያወጣውን መግለጫ በመጥቀስ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
መግለጫው ጨምሮም የምዕራብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ኤል ጄኒና ውስጥ ከ300 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ውጊያውን ተከትሎ የደረሱበት አለመታወቁን ገልጿል።
- የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሙሉ ሱዳንን እቆጣጠራለሁ አለ3 ህዳር 2023
- የዳጋሎ ኃይል የአገሪቱን ጦር ኃይል ከሱዳን ሁለተኛ ትልቋ ከተማ ማስወጣቱ ተገለጸ27 ጥቅምት 2023
- አሜሪካ የሱዳን የሲቪሎች ልዑክ በአዲስ አበባ ያደረጉትን ውይይት እደግፋለሁ አለች27 ጥቅምት 2023
በግጭቱ ወቅት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወታደሮች አረብ ያልሆኑ ነዋሪዎችን ኢላማ በማድረግ እና በመግደል የዐይን ምስክሮች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን ከሰዋል።
በካርቱም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም የዐይን እማኞችን መረጃ መሠረት አድርጎ “የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና በእነሱ የሚደገፉ ሚሊሻዎች በሚፈጽሙት ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መረበሹን” ገልጿል።
ነገር ግን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ “የጎሳ ግጭት” ብሎ በገለጸው ጥቃት ውስጥ ኃይሎቹ እንዳልተሳተፉ በመግለጽ የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።
በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል ውስጥ እየተባባሰ ያለውን ግጭት በመሸሽ ባለፉት ጥቂት ቀናት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሱዳንን ድንበር በመሻገር ወደ ጎረቤት ቻድ ተሰደዋል።
ከተቀሰቀሰ ወራትን ባስቆጠረው በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት አስካሁን ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ቀያቸውን ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸው ተዘግቧል።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ በኃያላኑ የአገሪቱ የጦር ጄኔራሎች በሚመሩት በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሱዳንን ቀውስ ውስጥ አስገብቷታል።
አስካሁን የተኛውም ወገን በጦርነቱ የበላይነትን ያልያዘ ሲሆን፣ ሁለቱ ኃይሎች ዋና ከተማዋን ሱዳንን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ከባድ ጦርነት እኣካሄዱ ይገኛሉ።
ባለፉት ወራት ጦርነት በማቆም ከስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ድርጅት እንዲሁም የአካባቢው አገራት ለማሸማገል ጥረት ቢያደርጉም አስካሁን አልተሳካላቸውም።