
ከ 9 ሰአት በፊት
በአውሮፓ ድንበር ለመሻገር በራስ ሕይወት ላይ የመፍረድ ያህል እየሆነ ነው።
ፍልሰተኛ አስተላላፊዎች ከምዕራብ ባልካን አገሮች ወደ አውሮፓ ኅብረት አገራት ለመሻገር አሁን አሁን በሞት መንጋጋ ማለፍ ይጠይቃል።
ሕገ ወጥ የሰዎች አስተላላፊዎች እርስ በእርስ በሚያደርጉት የተኩስ ልውውጥ መሀል ፍልሰተኞች ይገደላሉ። በመኪና ድንበር ለማቋረጥ ሲሞከር በርካቶች ሕይወታቸው ይቀጫል።
ይህ ሁሉ እየሆነ የፍልሰተኞች ቁጥር በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየጨመረ ነው።
ባፈለው ሳምንት በሁለት የሕገ ወጥ አስተላላፊ ቡድኖች በተነሳ ጸብ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል። ሟቾቹ አፍጋኖች ናቸው።
የተኩስ ልውውጡ የነበረው በሰርቢያ እና በሃንጋሪ ድንበር ላይ ነበር።
ፖሊስ እንደሚለው ሕገ ወጥ አስተላላፊ ቡድን የሞሮኮ፣ የአፍጋን እና የሶሪያ አደገኛ ቡድኖች መካከል በሚነሳ ጸብ ነው ስደተኞች ችግር ውስጥ እየወደቁ ያሉት።
ከሰርቢያ የምትዋሰንበት የሃንጋሪ ደቡባዊ ድንበር በእነዚህ ቡድኖች ቁጥጥር ሥር ወድቋል ይላሉ ዘገባዎች።
ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሰርቢያውያን ፖሊስ ሰላማቸውን እንዲመልስላቸው እየተማጸኑ ነው።
አንዳንዶች ፖሊስ ራሱ በሰርቢያም በሃንጋሪም በኩል ከወንጀለኞቹ ጋር ይተባበራል ሲሉ ይከሳሉ።
የኦስትሪያ እና የስሎቫክ መንግሥታት በሃንጋሪ ላይ ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን፣ ብዙ ስደተኞች ወደ ድንበራቸው እየተጠጉ ያሉት በሃንጋሪ በኩል ስለሆነ መንግሥት ጥበቃውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
በሃንጋሪ በኩል ምንም እንኳ ጠንካራ ድንበር ቢገነባም፣ በየዕለቱ በርካታ ስደተኞች እየታሠሩ ቢሆንም ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም።
- ኳታር ምዕራባውያን አሸባሪ ያሉትን ሐማስ ለምን አስጠለለች? ማደራደሩስ ይሳካላታል?10 ህዳር 2023
- “ሐሎ! ከእስራኤል ደኅንነት ቢሮ ነበር የምደውለው። ቤትህን ልናጋየው ትዕዛዝ ተሰጥቶናል”9 ህዳር 2023
- እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የትኞቹ አገራት ተቃወሙ? የትኞቹስ ደገፉ?8 ህዳር 2023

ስደተኞች ላይ ጠንካራ አቋም አላቸው የሚባሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ስደተኞችን ለማስቆም ጥረታቸው ብዙም የሰመረ አይመስልም።
ሳዳር የ33 ዓመት ወጣት ነው። ቀድሞ በአፍጋኒስታን ጦር ውስጥ አገልግሏል። አስተላላፊዎቹ “አንዳንድ ጊዜ እጅግ ጨካኝ እና ቁጡ ሆነው ስደተኞችን ይደበድባሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ደግነታቸው ወደር የለውም፤ ምግብ እና መኝታ ሁሉ ያቀርባሉ” ይላል።
ሳዳር በሃንጋሪ ድንበር በኩል ተሻግሮ ነው ያለው። እዚህ የደረሰው በአውቶቡስ ተሳፍሮ ነው። ድንበር መሻገር የቻለው በቡልጋሪያ በኩል ከ25 ቀናት ከአሰቃቂ እና ከአደገኛ ጉዞ በኋላ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።
አፍጋኑ ሳዳር የተነሳው ከኢስታንቡል ሲሆን፣ ጀርመን ለመድረስ 10 ሺህ ዶላር ከፍሏል።
ቢቢሲ በተመለከተው አንድ ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ አንድ አፍጋናዊ ለሰዎች አስተላላፊዎች ክፍያ ሳይፈጽም ድንበር ለመሻገር ሲሞክር ተይዞ ክፉኛ ሲደበደብ ይታያል።
በሃንጋሪ በኩል ያለው ድንበር የሽቦ እና የኤሌክትሪክ አጥር ያለበት 175 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው። ይህን አጥር በቁጥጥራቸው ሥር ያስገቡት ሕገ ወጥ የሰው አስተላላፊዎች ነው። ማን መሻገር እንዳለበት የሚወስኑት እነሱ ናቸው።
ቀደም ሲል አንድ ዘዴ ይጠቀሙ ነበር ስደተኞች። በተመሳሳይ ጊዜ አጥሩን ለማለፍ መሞከር። የተወሰኑት ይያዛሉ፣ በለስ የቀናቸው ያልፋሉ።
አሁን ያ ዘዴ አይሠራም።
ከኮሶቮ የመጡ አውቶማቲክ ጠመንጃዎች በአስተላላፊዎች እጅ ላይ ወድቀዋል። በሞሮኳውያን እና በአፍጋኒስታናውያን በተያዘው ድንበር ሙሉ ቁጥጥር እና የበላይነት ለመያዝ በየጊዜው ከፍተኛ ጸብ ይነሳል። ይህ ደግሞ በተኩስ የታጀበ ነው።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ብቻ አንዲት የ16 ዓመት ሴት ስትሞት፣ 7 ስደተኞችም ክፉኛ ቆስለዋል።
ከሳምንት በፊትም ተመሳሳይ የተኩስ ልውውጥ ነበር።

ጸቡ የተነሳው የሶሪያ አደገኛ የሰዎች አስተላላፊዎች ቡድን ቦታውን ተቆጣጥሮ በነበረው የአፍጋን አስተላላፊዎች ቡድን ላይ የበላይነትን ለመያዝ ተኩስ በመክፈቱ ነበር።
በሰሜን ሰርቢያ በኩል የሃንጋሪን ድንበር ለመሻገር የሚሞክሩት በብዛት የሶሪያ እና የአፍጋኒስታን ተወላጆች ቢሆኑም ኩርዶች፣ ፓኪስታኖች እና ሌሎችም በርካታ ዜጎች ይገኙበታል።
“በሃንጋሪ ድንበር ላይ ያለው የሽቦ አጥር ጥቅሙ አንድ ብቻ ነው” ይላል ቭላድሚር ፖሎቪና። ቭላድሚር የስደተኛ ጉዳዮች አክቲቪስት ነው።
“ይህ አጥር ጥቅሙ ስደተኞችን ማቆም ሳይሆን ገንዘብ መቀበያ ጣቢያም ሆኖ ማገልገል ነው” ይላል።
“አጥሩን የተቆጣጠረ ከእያንዳንዱ ተሻጋሪ ዩሮ የመቀበል መብትን ያገኛል።”
የሃንጋሪ ፖሊስ እንደሚለው 80 ሰዎች በየምሽቱ ሲሻገሩ ይያዛሉ።
የሃንጋሪ ፖሊሶችም ብዙ ስደተኞችን ሲደበድቡ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ።
የሃንጋሪ ፖሊስ ግን እንዲያ ያለ ድርጊት አልፈጽምም ይላል።
የተሰባበሩ እና የተቃጠሉ መኪኖችም በድንበር አካባቢ ይታያሉ። ይህም ሕገ ወጥ አስተላላፊዎች ስደተኞችን ለማሳለፍ በሚያደርጉት ጥረት የወደሙ ናቸው።
ባለፈው ዓመት ብቻ ከ20 በላይ ተመሳሳይ አደጋዎች ተከስተዋል።
አስተላላፊዎቹ ፖሊስን ለማምለጥ በከፍተኛ ፍጥነት ስለሚነዱ አደጋው ይከሰታል። ኦስትሪያ ተመሳሳይ 70 የሚሆኑ አደጋዎች ተመዝገበዋል ትላለች።
ለዚህ የመኪና አደጋ መበራከት ዋናው ምክንያት አደገኛ ወሮበሎች እና ሕገ ወጥ የሰዎች አስተላላፊዎች ባወጡት አዲስ ሕግ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
አሽከርካሪዎች ገንዘብ የሚከፈላቸው ስደተኞቹን ካስተላለፉ ብቻ ነው። ካላስተላለፉ ገንዘብ አይከፈልም። ይህም ስደተኞቹን ለማሳለፍ ለከፍተኛ ፍጥነት ስለሚጠቀሙ አሰቃቂ አደጋ ያጋጥማል።