የፎቶ ባለሙያው አቤል ጋሻው
የምስሉ መግለጫ,አቤል በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም በመጓዝ በኢትዮጵያዊ ዓይን ዓለም የመሰነድ ራዕይ ሰንቋል።

ከ 9 ሰአት በፊት

አንዳችን ያለ አንዳችን ብንኖር ዓለም ምን እንደምትመስል አስባችሁት ታውቃላችሁ?

ለምሳሌ ሁሉም ያደገ አገር ቢሆን። አሊያም ሁሉም አገር በማደግ ላይ ያለ ድሃ አገር ቢሆን።

አሊያም የዓለም ሕዝብ ሁሉ ሙስሊም፤ አሊያም ክርስቲያን።

ሁሉም ሰው ረጅም አሊያም ሁሉም ሰው አጭር።

አንድ ዓይነት ምግብ። እንጀራ ከሆነ በቃ ሁልጊዜ እንጀራ።አሰልቺ የምትሆን አይመስላችሁም ?

ዓለም በልዩነት ተሰብዛ የተሰራችውም ለዚህ ይመስላል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ልዩነቶች ውበት መሆናቸው ቀርቶ የስጋት ምንጭ ሆነዋል።

አንዱ የሌላውን ከማክበር ይልቅ እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ ፉክክር ውስጥ ተገብቷል።

በዚህም ምክንያት ጥቃቶች፣ ግጭቶች ተፈጥረው የበርካቶች ሕይወት አልፏል። ብዙ ንብረት ወድሟል።

በዚህ ሁሉ መካከል ደግሞ ይህንን ልዩነት በፍቅር ለማጥበብ ደፋ ቀና የሚሉት ጥቂቶች አይደሉም።

የሙሉ ጊዜ የፎቶግራፍ ባለሙያው አቤል ጋሻው፣ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው።

አቤል ማንኛውም ሰው በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ በጎ አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት ብሎ ያምናል።

ለዚህም ነው በተሰማራበት የሙያ ዘርፍ የበኩሉን ለማድረግ እየጣረ ያለው።

ተቻችሎ ስለመኖር፣ የሁሉም መኖር እንደሚያስፈልግ፣ የሁሉም ሃይማኖታዊ እና ብሔራዊ ማንነት አስፈላጊ እንደሆነ እና ውበት እንዳለው ለማሳየት ይሞክራል።

አንዱ የሌላውን ሃይማኖት፣ የሌላውን ብሔረሰብ ክዋኔ እና ባህላዊ ትውፊቶች ማየት እንዲችል በተለያዩ ሁነቶች ላይ በመገኘት ፎቶግራፍ ያነሳል።

አቤል በዚህ ሃሳብ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ምክንያት የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት በመስቀል አደባባይ ከተካሄደው የጎዳና ላይ አፍጥር ፕሮግራም ጋር በተያያዘ የተነሳው ውዝግብ ነበር።

“ያኔ ሁሉም ሰው ጎራ ለይቶ አንዱ በአንዱ ላይ እንደተነሳ ሲገልጽ እንጂ፣ አንዱ የራሱን ማንነት እና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ማሳየት እንደፈለገ ሲገልጽ አልነበረም” ይላል።

እንደ አውሮፓውያኑ 2021 በመስቀል አደባባይ የተካሄደው የጎዳና ላይ አፍጥር ፕሮግራም በፎቶ
የምስሉ መግለጫ,ከሁለት ዓመት በፊት በመስቀል አደባባይ የተካሄደው የጎዳና ላይ አፍጥር ፕሮግራም ውዝግቦች ተነስተውበት ነበር።

በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በመስቀል አደባባይ የጎዳና ላይ የአፍጥር ፕሮግራም ሊካሄድ ከታቀደ በኋል ውጥረት ነግሶ ነበር።

ከበርካታ ውዝግቦች በኋላም ፕሮግራሙ በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ ተወሰነ።

ያኔ የሌላ እምነት ተከታይ የሆነው አቤል ካሜራውን ይዞ ወደ ሥፍራው አመራ።

ፍላጎቱም ከሃይማኖቱ ተከታይ ውጭ ያሉ ሰዎች ያን ፕሮግራም እንዴት ነው የሚያዩት? የሚለውን ሃሳብ ለመረዳት ነበር።

ምስሎችንም በካሜራው አስቀረ። “ሕብረቱ፣ ሥርዓቱ ደስ ይል ነበር” ይላል።

በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ከጠበቀው በላይ እንደነበር ያስታውሳል።

የፎቶግራፍ ጥበቡንም በመጠቀም ጥልቅ የሆነው ጥበብ፣ ባህል፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ጠብቆ ለማቆየት፣ ለመሰነድ እና በቦታው መገኘት ላልቻሉት በፎቶ ማሳየት መቻሉንም ይናገራል።

“የመስቀል አደባባዩን የአፍጥር ፕሮግራም ያነሳሁት የእስልምና እምነት ተከታይ ያልሆነው ሰው ላይ የሚፈጥረውን ስሜት ለመረዳት እና ምላሻቸውን ለማወቅ ነበር” የሚለው አቤል፣ ፎቶዎቹን አንስቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ካጋራው በኋላ ፎቶው በብዙ ሺዎች ተጋርቷል።

“ፎቶዎቹን በብዛት የተጋሩት የሌላ እምነት ተከታዮች ናቸው”

አቤል እንደሚለው ከሁለት ዓመት በፊት በመስቀል አደባባይ የተካሄደው የጎዳና ላይ አፍጥር ፕሮግራም የተካሄደው የሕዳሴው ግድብ ውዝግብ ባየለበት ወቅት ነበር።

በፕሮግራሙ ላይም “ግድቡ የእኔ ነው!” የሚሉ መፈክሮች ታይተዋል።

አቤል በካሜራው ያስቀራቸውን እነዚህ ምስሎች በአብዛኛው የተጋሯቸው የሌላ እምነት ተከታዮች ናቸው ይላል።

“ፎቶውን ያነሳሁትም እንደዚህ ዓይነት አንድነትን እና መቀራረብን ለመፍጠር ነው” ብሏል።

በእስልምና ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝቶ ፎቶ ሲያነሳ የመጀመሪያው እንደነበር የሚናገረው አቤል፣ በወቅቱ ታድመው ከነበሩ የእምነቱ ተከታዮች ጋር የነበረው ግንኙነት እና የተለዋወጠው ሃሳብ የማይረሳው እንደሆነ ይናገራል።

አቤል ፎቶግራፍ ማንሳት ከጀመረበት የታዳጊነት ጊዜው ጀምሮ የሁነት፣ ዘጋቢ እና የጉዞ ፎቶዎችን ማንሳት ላይ ትኩረት ያደርጋል።

በርካታ ፎቶዎችንም አንስቷል። በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ብሔረሰባዊ ሁነቶች ላይ ተገኝቶ ምስሎችን በካሜራው አስቀርቷል።

ይሁን እንጂ የመስቀል አደባባዩ የጎዳና ላይ አፍጥር ፕሮግራም ልዩ ቦታ ከሚሰጣቸው የጥበብ ትሩፋቶቹ አንዱ ነው።

አቤል ሌሎች “የእኔ ምርጥ” የሚላቸው ፎቶግራፎችም አሉት። ከእነዚህ መካከል በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ያነሳቸው ፎቶግራፎች ይገኙበታል።

“እነዚህን ፎቶዎች ሕይወቴን ለአደጋ አጋልጬ ያነሳኋቸው ናቸው” ይላል።

የትግራይ  ኃይሎች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ሲጠቀሙበት የነበረው ታንክ
የምስሉ መግለጫ,በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት የትግራይ ኃይሎች ሲጠቀሙበት የነበረው ታንክ በሰሜን ወሎ ጋሸና

ከአባት የተወረሰ ጥበብ

አቤል ፎቶግራፍ ማንሳት የጀመረው ገና የ13 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው። የጀመረውም ‘ኒከን ዲ 100’ በሚባል ባለ አንድ ሌንስ ካሜራ ነበር። ካሜራው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለ ሥራውን ከሚወዱለት የተበረከተለት ነው።

ገና በለጋነቱ በፎቶግራፍ እና በሥዕል ጥበቦች ልቡ የሸፈተው በአባቱ የሥዕል ሥራዎች ስለሚማርኩት ነበር።

አዲስ አበባ ከተማ ተወልዶ ያደገው አቤል፣ አባቱ ጥንታዊ የቤተክርስቲያን ሥዕሎችን በመሳል እንዲሁም ፎቶግራፎችንም በማንሳት ይታወቃሉ።

ወላጆቹ በሥራ ምክንያት ተዛውረው ጎንደር በቆዩበት ጥቂት ዓመታትም በርካታ ሥዕሎችን ሲስሉ ተመልክቷል።

የአባቱ የሥዕል ሥራዎች አሁንም ድረስ በጨጨሆ ቤተ ክርስቲያን እና በነፋስ መውጫ ትምህርት ቤት ውስጥ በሚገኙ የሥነ ጥበብ ማዕከላት ተጠብቀው ይገኛሉ።

“ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎችን በደንብ የተረዳሁት በአባቴ ሥዕሎች ነው” ይላል።

አቤል እንደሚለው አባቱ የሚስሏቸው ሥዕሎች ሃይማኖታዊ እና የኢትዮጵያን ውበቶች የሚያሳዩ ነበሩ።

ቤት ውስጥም ካሜራዎች እና የሥዕል መሳያ ቁሳቁሶች ነበሩ።

“አባቴ፤ እናቴን ይስላት ነበር” ይላል አቤል።

የ10 ዓመት ታዳጊ እያለ አባቱ በሞት ቢለዩትም የእርሳቸውን ፈለግ ተከትሎ የፎቶግራፍ ሙያን የሙሉ ጊዜ ሥራው አድርጎ ይዞታል።

በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የወንጪ ሐይቅ
የምስሉ መግለጫ,በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የወንጪ ሐይቅ

“ዓለምን በኢትዮጵያዊ ዐይን የመሰነድ ህልም አለኝ”

አቤል ጋሻው የመጀመሪያ ዲግሪውን በኮምፒዩተር ሳይንስ ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል።

የፎቶግራፍ ትምህርት አልተማረም። ሙያውን ያሳደገው በልምምድ እንዲሁም አንድ ኮሪያዊ ፎቶግራፈር እና ኢትዮጵያዊቷ ፎቶግራፈር አይዳ ሙሉነህ ባጋሩት እውቀት ነው።

አቤል ሁነቶችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ካነሳ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ የማጋራት ልምድ አለው።

ለአውደ ርዕይ የሚያቀርባቸውም አሉ።

በሰሜኑ ጦርነት ውስጥ ሆኖ ያነሳቸውን ፎቶግራፎችም በመጽሐፍ መልክ ለማቅረብ ዕቅድ አለው።

አቤል በፎቶግራፍ ሥራዎቹ ተወዳጅነትን በማትረፍ የፎቶ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ከተለያዩ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ አግኝቷል።

ለትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ፎቶ ለማንሳትም ዕድል አግኝቷል። ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የዜና ተቋማት፣ የጉዞ ድርጅቶች እና የመዝናኛ ተቋማት ፎቶግራፎቹን ገዝተውታል።

አቤል በሙያው ሊያሳካቸው የሚፈልጋቸው ብዙ ህልሞች አሉት።

ኢትዮጵያ ውስጥ የፎቶግራፍ ጥበብ እንዲያድግ አስተዋፅኦ ማበርከት ቀዳሚው ነው። ከዚያም ወጣት ፎቶግራፈሮችን ማገዝ፣ እውቀቱን ማጋራት ይፈልጋል።

በፎቶግራፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀሩ የሚሉ ቦታዎችን ዞሮ በማየትና በካሜራው በማስቀረት ለዓለም ማሳየትም ዕቅዱ ነው።

“ኢትዮጵያ ብዙ ኅብር ያለባት አገር ናት፤ ነገር ግን ሁሉም ተሰንዷል ብዬ አላምንም” የሚለው አቤል የሚችለውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ህልም ሰንቋል።

አሁን ላይ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ወደ ሚገኙ ሦስት አገራት ተጉዞ ያያቸውን ሰንዷል።

አፍሪካን በደንብ ሰንዶ በኢትዮጵያዊ ዐይን ለዓለም ማሳየት፣ ከዚያም ዓለምን ተዟዙሮ በማየት ያሉትን ነገሮች የመሰነድ ራዕይ አለው።