
12 ህዳር 2023, 09:11 EAT
በጋዛ የሚገኘው አል ሺፋ ሆስፒታል ከፍተኛ ችግር ውስጥ ውድቋል።
ሆስፒታሉ ሥራ ለማቆም የተቃረበው በአካባቢው በሐማስና እሰራኤል መካከል ከባድ ጦርነት እየተደረገ መሆኑን ተከትሎ ነው።
በሆስፒታሉ ታማሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ጦርነትን ሸሽተው የተጠለሉ በርካታ ፍልስጤማዊያን ይገኙበታል።
ከሆስፒታሉ አቅራቢያ በሚገኙ ጎዳናዎች ጦርነቱ የተፋፋመ ሲሆን እስራኤል እስከ አሁን በዚህ ሆስፒታል ላይ ጥቃት አላደረስኩም ብላለች።
የሆስፒታሉ ሐኪሞች በጨቅላ ማሞቂያ ክፍል የሚገኙ ሁለት ሕጻናት መሞታቸውን ተናግረዋል። 37 ሌሎች ጨቅላዎችም በሞት አፋፍ ላይ ናቸው ብለዋል።
እስራኤል በበኩሏ በአል ሺፋ ሆስፒታል የሚገኙ ሕጻናት ወደ ሌላ ሆስፒታል ቢወሰዱ መልካም ነው ስትል መክራለች።
ቢቢሲ 20 የሚሆኑ ጨቅላ ሕጻናት ምስሎች ደርሰውታል።
ጨቅላዎቹ የሚገኙት በአል ሺፋ የቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ እንደሆነና ለሆስፒታሉ የኤሌክትሪክ አግልግሎት በፍጥነት ካልተለቀቀ ሁሉም ሊሞቱ እንደሚችሉ በዚያ የሚገኙ ሐኪሞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሆስፒታሉ የሚወጡ መረጃዎች አስጨናቂና የሚያውኩ ሆነዋል። በተለይ በቅርብ ጊዜ ቀዶ ጥገና አድርገው ያልዳኑ ታማሚዎችና ሕጻናት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።
አስክሬኖች በሆስፒታሉ መተላለፊያ ጭምር ተከምረው ግብአተ መሬት ለመፈጸም እንኳ አስቸጋሪ ሆኗል ይላሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሐኪሞች።
ባለፉት ሁለት ቀናት ከባድ ፍልሚያ በሚደረግበት አል ሺፋ ሆስፒታል በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከጦርነቱ ከለላን ፍለጋ ተጠግተው ይገኛሉ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ይህ ሆስፒታል ከምድር በታች የሐማስ ማዘዣ ዋና ማዕከል ነው ሲል ይከሳል።
ሐማስ በበኩሉ ይህ ሐሰት ነው ሲል ያስተባብላል።
ዶ/ር መርዋን አቡ ሳአድ የተባሉ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ለቢበሲ እንደተናገሩት በእያንዳንዷ ደቂቃ የተኩስ ድምጽና የቦምብ ድምጽ ይሰማል።
የተከመሩ አስክሬኖችን ለመቅበርም በፍጹም የሚቻል አልሆነም ይላሉ ዶ/ር መርዋን።
ሐኪሙ ምናልባት አስክሬኖች ባለመቀበራቸው አንዳች ወረርሽኝ በሆስፒታሉ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ፍርሃት አላቸው።
አስክሬን ማቀዝቀዣ ክፍል ኤሌክትሪክ ባለመኖሩና ጄኔሬተር ለማንቀሳቀስ ደግሞ ነዳጅ በማለቁ የሬሳ ማቆያ ክፍል ከጥቅም ውጭ ሆኗል።
- ማክሮን እስራኤል ሕጻናት እና ሴቶችን በቦምብ ከመደብደብ ትቆጠብ አሉ5 ህዳር 2023
- የጦርነት ዳፋ የመጨረሻው ውጤት የሚታየው ጦር ሜዳ ላይ ሳይሆን ቤተሰብ ውስጥ ነው – ይፍቱሥራ ምትኩ12 ህዳር 2023
- የሰው ልጅ ትኋንን ማጥፋት ያልቻለበት ምክንያቱ ምንድነው?12 ህዳር 2023
መቀመጫውን እስራኤል ያደረገው “ሐኪሞች ለሰብአዊ መብቶች” (Physicians for Human Rights Israel) የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ቡድን በአል ሺፋ ሁለት ጨቅላዎች በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት በሆስፒታሉ መሞታቸውን ጠቅሶ ምናልባት በሚቀጥሉት ቀናት 37 ሌሎች አዲስ የተወለዱ ጨቅላዎች ሊሞቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
እስራኤል ሆስፒታሉ ላይ ከበባ እንዳልፈጸመችና ምሥራቃዊው የሆስፒታሉ ክፍል አሁንም ቢሆን አካባቢውን ለመልቀቅ ለፈለገ ሰው ክፍት እንደሆነ ተናግራለች።
ቃል አቀባይ አድሚራል ዳኒኤል ሐጋሪ “ጨቅላዎቹ ወደ ሌላ ሆስፒታል መውሰድ ከተፈለገ ድጋፍ እናደርጋለን” ብለዋል።
ከዚህ አስተያየት ቀደም ብሎ ኮሎኔል ሞሼ ቴትሮ በሐማስና በእሰራኤል ጦር መካከል የተኩስ ልውውጥ በሆስፒታሉ አቅራቢያ መኖሩን ተናግረው ነበር።
ቢቢሲ የደረሰው የፎቶ መረጃ እንደሚያሳያው ወደ 20 የሚጠጉ ጨቅላዎች በብርድ ልብስ ተጀቡነው በአዋቂዎች ክፍል ተደርድረው ይታያሉ።
ብዙዎቹ ሰውነታቸው ላይ ነጭ ፕላስተር የሚታይ ሲሆን ይህም ምናልባት ኦክሲጂን እንደሚያስፈልጋቸው የሚጠቁም ነው።
ሐኪም አቡ ሳአድ ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ “ጨቅላዎቹን በዚህ መልኩ ለቀናት መተው ሌላ ምንም ሳይሆን እንዲሞቱ መፍቀድ ነው።” ብለዋል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ምክትል አስተባባሪ በበኩላቸው “ተኩስ አቁም ካልተደረገ በዚህ ሆስፒታል ያሉ በሙሉ ይሞታሉ፤ ሆስፒታሉም ወደ መቃብርነት ይቀየራል” ሲሉ መጪውን አስከፊ ሁኔታ ለቢቢሲ አጋርተዋል።
የጋዛ ሰርጥ 2.2 ሚሊዮን ፍልስጤማዊያን መኖርያ የነበረ ሲሆን አሁን ጦርነቱ ከወር በፊት መጀመሩን ተከትሎ 1.5 ሚሊዯን ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።
ይህን ያለው የተባበሩት መንግሥታ የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ነው።
ሐማስ ከወር በፊት መብረቃዊ ጥቃት ፈጽሞ 1200 እስራኤላዊያንን ከገደለና 200 አግቶ ከወሰደ ወዲህ እራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ከ11ሺህ ፍልስጥኤማዊያን በላይ ተገድለዋል።
ከሟቾቹ መካከል 4ሺህ 500 የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው። ይህ አሐዝ በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ያወጣው ነው።
ከትናንት በስቲያ አርብ ከቢቢሲ ጋር ቃል ምልልስ ያደረጉት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ”እስራኤል በጋዛ ሴቶችና ሕጻናትን መግደል ማቆም አለባት” ሲሉ ተናግረዋል።
ማክሮን የተኩስ አቁም እንዲደረግ የጠየቁ ሲሆን አሜሪካና ዩኬ ይህን ሐሳባቸውን እንዲጋሩ ጥሪ አቅርበዋል።
