
12 ህዳር 2023, 10:32 EAT
የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በሰላማዊ ሰልፈኞች መካከል የተነሳውን ነውጥ አወገዙ።
ሱናክ “ነውጡ ተቀባይነት የሌለው ነው ካሉ በኋላ ”ቀኝ አክራሪዎችን” እና “የሐማስ ተቆርቋሪዎች” ያሏቸውን ተጠያቂ አድርገዋል።
ከ300ሺህ በላይ እንደሆኑ የሚገመቱ የፍልስጥኤም ደጋፊዎች “የተኩስ አቁም ይደረግ” በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉት ትናንት ቅዳሜ ነበር።
ይህ የተቃውሞ ሰልፍ የእስራኤልና ጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ትልቁ እንደሆነ ተነግሯል።
ይህን ሰልፍ ተከትሎ ትይዩ የተቃውሞ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን ፖሊስ ዋናውን ለፍስጤማዊያን የሚደረገውን የድጋፍ ሰልፍ ሊያውኩ ሞክረዋል ያላቸውን 126 የቀኝ አክራሪ ሰልፈኞች በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ብሏል።
በፍልስጤም ደጋፊዎችና ይህንኑ በሚቃወሙት ቀኝ አክራሪዎች መሀል ነውጥ የታየው በለንደን ከተማ፣ በተለይም ቻይናታውን እና ሴኔታፍ በሚባሉ ቦታዎች ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ “ማንኛውም ነውጥና ነውጠኛ በሕግ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለበት” ብለዋል በኤክስ ገጻቸው።
የፖሊስ ጽሕፈት ቤት ረዳት ኮሚሽነር ማት ትዊስት ነገሩ እየከረረ የመጣው ባለፉት ቀናት በእንግሊዝ በሰልፉ ዙርያ የተደረጉ ክርክሮች ናቸው ብለዋል።
የመጀመርያው ግጭት የሴንጆርጅን ባንዲራ በያዙ ቀኝ አክራሪዎች የተጀመረ ሲሆን ወደ ዋይትሆል ካልገባን በሚል ፖሊስን ጥሰው ወደ ሴኔታፍ አደባባይ ቅጥር ገብተዋል።
በሴኔታፍ አደባባይ 103 ዓመት ያስቆጠረው መታሰቢያ ሐውልት የሚገኝበት ነው።
ይህ ሐውልት በተለያዩ የዓለም ጦርነቶችና ከዚያም ወዲህ በጦር አውድማ ለሞቱ የብሪታኒያ ወታደሮች ለመታሰቢያነት የቆመ ነው።
ይህ ነውጥ በሚከሰትበት ወቅት ደግሞ ‘የአርምስቲስ ቀን” እየተከበረ ነበር። የ2 ደቂቃ የሕሊና ጸሎትም እየተደረገ በነበረበት ሰዓት ነው ቀኝ አክራሪዎች ድምጽ ሲያሰሙ የነበረው።
አርምስቲስ ዕለት በ1ኛው የዓለም ጦርነት የተሳተፉት የተባበሩት ኃይሎችና ጀርመን ጦርነቱን ለማቆም የተፈራረሙበትን ቀን የሚዘከርበት ነው።
ከ80 በላይ የሚሆኑ ዋናውን የፍልስጤም የድጋፍ ሰልፍ ለማወክ ያለሙ በፖሊስ ቁጥጥር ውለዋል ብለዋል የፖሊስ አዛዥ።
ሌሎች 10 የሚሆኑት ደግሞ አደገኛ ዕጽ በመያዝ፣ ያልተፈቀዱ መሣሪያዎችን በመታጠቅ ተይዘው ታሰረዋል።
በሌላ በኩል ጸረ አይሁድ መፈክሮችን አሰምተዋል፣ የጥላቻ ምልክቶችንም ይዘው ተገኝተዋል የተባሉ ሰልፈኞችም ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሏል።
ፖሊስ እንደሚለው የፍልስጤምን የድጋፍ ሰልፍ ለማወክ ከሞከሩት ውስጥ ብዙዎቹ በእግር ኳስ ነውጥ የሚታወቁ ናቸው።
“ነጻ የፍልስጤም አገር” እና “ተኩስ አቁም አሁኑኑ” የሚሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች በሃይድ ፓርክ ተሰባስበው ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የሰልፉ ርዝመት ፓርክ ሌን ከሚገኘው ሒልተን ሆቴል ተነስቶ ‘ናይን ኤልምስ’ የሚገኘው አሜሪካ ኤምባሲ ይደርሳል።
ይህም ማለት ሰልፈኞቹ 2.5 ማይልስ ርዝመት ያለው አካባቢን ሸፍነዋል።
የፍልስጤም ድጋፍ ሰልፍ አስተባባሪዎች በሰልፉ የተገኙት 800ሺህ ሰዎች ናቸው ይላሉ። የፖሊስ ግን አሐዙን ወደ 300ሺህ ዝቅ ያደርገዋል።
- የሰው ልጅ ትኋንን ማጥፋት ያልቻለበት ምክንያቱ ምንድነው?12 ህዳር 2023
- ማክሮን እስራኤል ሕጻናት እና ሴቶችን በቦምብ ከመደብደብ ትቆጠብ አሉ5 ህዳር 2023
- ማኅበራዊ ሚድያ እና የጋዛ ግጭት፡ ሞሐመድ ሳላህ ለስፖርቱ ዓለም “አርአያ” ነው8 ህዳር 2023

አንድ ሰልፈኛ ለቢቢሲ ሲናገር፣ “እኛ የምንሻው ተኩስ አቁም እንዲደረግ ነው፣ ሕጻናት በፎቅ ፍርስራሽ ውስጥ እየሞቱ ነው፤ ማንም ግን ስለነርሱ ሕይወት ግድ ያለው አይመስልም።” ብሏል።
የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ሰልፍ በአርምስቲስ ዕለት እንዳይደረግ ጠይቀው የነበረ ሲሆን በዚህ ቀን ይህን ሰልፍ ማድረግ ለዕለቱ ክብር መንሳት ይሆናል የሚል መንፈስ ያለው አስተያየት ሰጥተዋል።
ይህ አስተያየት ለቀናት በዩኬ ሲያጨቃጭቅ ከርሟል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት ያበሳጨው አንድ ሰልፈኛ ለቢቢሲ “ይልቅ ክብር መንሳት ማለት ሕጻናት ሲሞቱ ምንም አለማድረግ ነው” ሲል ተናግሯል።
ሌላ ሰልፈኛ ደግሞ “እንዲያውም ይህን ሰልፍ ለማድረግ ትክክለኛው ቀን የአርምስቲስ ቀን ነው። አርምስቲስ ቀን ማለት እኮ ተኩስ ማቆም የተደረገበት ነው። ጦርነት የቆመበት ነው፤ የኛም ጥያቄ ይኸው ነው።” ብሏል።
በዚህ ሰልፍ ላይ በቪክቶሪያ ጣቢያ ድንገት የተገኙት ሚኒስትር ማይክል ጎቭ በሰልፈኞች ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸው በፖሊስ አጀብ ነው ከዚያ መውጣት የቻሉት።
“በእርስዎ አፍረንብዎታል” የሚሉ ተቃዋሚዎች የፍልስጤምን ባንዲራ እያውለበለቡ ታይተዋል።
ሚኒስትሩ በዚያ የተገኙት በአጋጣሚ እንደነበር ተነግሯል።
ይህንን ለፍስጤማዊያን ድጋፍ የተጠራውን ሰልፍ በተለየ ሁኔታ አጨቃጫቂ ያደረገው የዩኬ የአገር ውስጥ ሚኒስትር የሆኑት ስዌላ ብረቨርማን ከሰልፉ በፊት የሰጡት ቃለ ምልልስ ነበር።
የፍልስጤም ደጋፊዎች ላይ ያነጣጠረው ይህን የሚኒስትሯን አስተያየት ብዙዎችን ያስቆጣ ሲሆን የሌበር ፓርቲ አስተያየቱን “ከፋፋይ” ሲል ተችቶታል።
የለንደን ከንቲባ ሳዲቅ ካን በበኩላቸው ሚኒስትሯ ሥልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።
የሌበር ፕሬዝዳንት ሰር ኪየር ስታርመር በበኩላቸው “በሕዝብ አገልግሎት ቆይተው ሕዝብን በመከፋፈል፣ እንግሊዛዊያን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ እንዲነሱ፣ ጥላቻና አለመተማመን እንዲዳብር ማድረግ የቻሉ ብዙ አይደሉም” ሲሉ ስቴላ ብረቨርማንን በጽኑ አውግዘዋታል።
የስኮትላንድ ዋና ሚኒስትር የሆኑት ሐምዛ ዩሱፍም ሚኒስትሯ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ሚኒስትሯ ለዚህ ትችት የዳረጋቸው ፍልስጤምን ደግፈው ሰልፍ የሚወጡ ሰልፈኞች “የጥላቻ ሰልፈኞች” ብለው መጥራታቸው ነው።
ከዚህም ሌላ ፖሊስ ለቀኝ አክራሪዎች ያደላል የሚል መንፈስ ያለው ሐሳብ ሰጥተው ነበር።
