
November 12, 2023

አለባቸው ንጉሤ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር
በአገር አቀፍ ደረጃ ምን ያህል አምራች ኢንተርፕራይዞች እንዳሉና የትኞቹ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ አምራቾች እንደሆኑ ዝርዝር መረጃ እንደሌለ ተገለጸ፡፡
አምራች ኢንተርፕራይዞች ቁጥራቸው በውል ካለመታወቁ ባሻገር የት ይገኛሉ? ምን ያመርታሉ? የማምረት አቅማቸው ምን ያህል ነው? የሚንቀሳቀሱበት የገንዘብ መጠንና የሠራተኞች ብዛት ምን ያህል ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ዝርዝር መረጃ አለመኖሩን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት አስታወቀ፡፡
ከቀበሌ፣ ከወረዳና ከክልል የሚመጣ ጥቅል መረጃ በመደመር ካልሆነ በቀር እያንዳንዱ ኢንተርፕራይዝ መቼ ተመሠረተ? ምን ያመርታል? የሚሉ ዝርዝር መረጃዎችን የሚያሳይ አሠራር አልነበረም ሲሉ፣ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሤ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ጋር እየተሠራ መሆኑን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ምን ያህል አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች አሉ? የት ይገኛሉ? የሚሉትን ዝርዝር መረጃዎች ለመለየት በኢትዮጵያ ስታትስቲክስት አገልግሎት አማካይነት ከ40 በላይ የሚሆኑ መጠይቆች መዘጋጀታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
የአጠቃላይ ኢንተርፕራይዞች ቆጠራ ሲጀመር የማሽነሪና የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች አምራች ድርጅቶች፣ እንዲሁም በአግሮ ፕሮሰሲንግ የተሰማሩ አምራቾች ያላቸውን የጥራት ደረጃና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን ለመለየት የሚያስችል አሠራር እንደሚፈጠር ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ከዓለም ባንክ የተገኘ 200 ሚሊዮን ዶላር ብድር፣ በሥራ ላይ ላሉ ኢንተርፕራይዞች በግል ባንኮች በኩል የመሥሪያ ካፒታል ሲሰጣቸው መቆየቱን አለባቸው (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
ማንኛውም ኢንተርፕራይዝ የመሥሪያ ማሽነሪ መቀየር ወይም አዲስ መግዛት ከፈለገ በሥራ ላይ መሆኑ ተረጋግጦ ተጨማሪ ዋስትና ሳይጠየቅ በብድር ከወሰደ በኋላ፣ ሠርቶ ብድሩን ሲመልስ ማሽኑ በስሙ ይሆናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህም በማምረቻ ማሽን ላይ የሚታየውን ችግር ይቀርፋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ማሽነሪ አምራቾች ማኅበር የሚያመርታቸውን ማሽነሪዎች ከኢንተርፕራይዞች ጋር ለማገናኘት የሚከናወኑ ሥራዎች ደካማ መሆናቸውን የጠቀሱት አለባቸው (ዶ/ር)፣ በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ ምን ያህል የማሽነሪ አምራቾች አሉ የሚለውን መረጃ መሰብሰቡንና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡
ማሽነሪ አምራቾችን ብቻ ሳይሆን ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ አምራቾች ስንት ናቸው የሚለውን መረጃ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አክለዋል፡፡
የቴክኖሎጂ አምራቾች የትኞቹ ናቸው? ምን ዓይነት ምርት ያመርታሉ? የሚለው ከተለየ በኋላ የትኞቹ ኢንተርፕራይዞች ምን ዓይነት ማሽነሪ ይፈልጋሉ የሚሉትን ማወቅ፣ አምራቹን ከተጠቃሚው ጋር ለማገናኘትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞችን ለማበረታታት በወጣው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ አዋጅና ደንብ መሠረት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ የማምረቻ ማሽኖች መኖራቸውን የተናገሩት አለባቸው (ዶ/ር)፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁለት ችግሮች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
የመጀመሪያው ተጠቃሚዎች ሕጉን አለማወቅና መብታቸውን በአግባቡ አለመጠቀም ሲሆን፣ ሁለተኛው ሒደቱን የሚያስተናግዱ የጉምሩክ ተቋማት ባለመናበባቸው እንደሚስተጓጎል አስረድተዋል፡፡
‹‹ምርቱን ወደ ውጭ የሚልክ አምራች ታክስ አይከፍልም፣ ነገር ግን ከውጭ ወደ አገር ቤት ምርት የሚያስገባ እንዲከፍል ይገደዳል፤›› ያሉት አለባቸው (ዶ/ር)፣ ይህን ለማሻሻል የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
አሠራሩ እስኪሻሻል ድረስ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት በበኩሉ ከዓለም ባንክ ከተወሰደ ብድር ላይ በመቀነስ፣ 25 ሚሊዮን ዶላር ለአምራቾች ዕገዛ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም 61 ያህል አምራች ኢንተርፕራይዞች ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት መመዝገባቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ 25 የሚሆኑት ደግሞ ማስረጃቸውን ለልማት ባንክ አስገብተው በመጠባበቅ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡