
ከ 6 ሰአት በፊት
በእስራኤል ድብደባ እየተፈጸመባት ባለው ጋዛ የሚኖሩ አራት ሰዎች የእለት ከእለት ሕይወታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።
ምግብና ውሃ ፍለጋ እንዴት ለሰዓታት እንደሚንገላቱ፣ ከአየር ጥቃት ለመሸሽ እንዴት በሌሊት እንደሚሰቃዩም ተናግረዋል።
እስካሁን በእስራኤል ጥቃት ከ11 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገልጿል።
ስልክና ኢንተርኔት ማግኘት ቀላል ባይሆንም አራቱ የጋዛ ነዋሪዎች ታሪካቸውን አካፍለዋል።
ማሳሰቢያ፡ ይሕ ጽሑፍ ሊረብሽ የሚችል ይዘት አለው።
አርብ ጥቅምት 13
እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎች ለደኅንነታችው ሲሉ እንዲወጡ አስጠነቀቀች።
ፋሪዳ፡ 26 ዓመቷ ነው። በጋዛ እንግሊዘኛ ታስተምራለች።
“ሦስት ጎረቤቶቼ ቤታቸው ወድሟል። መውጣት አለብን። መሄጃ ግን የለንም። ብዙ ጓደኞቼ ጠፍተዋል። ሞተውም ሊሆን ይችላል። ስለ ቤተሰቦቼ አላውቅም።”
ይህ ለቢቢሲ የላከችው የመጀመሪያ መልዕክት ነው።
ከቤተሰቦቿና ስድስት ልጆቿ ጋር በእግር ወደ ደቡባዊ ጋዛ አቀኑ። አንድ ሳምንት ገደማ ሲጓዙ መንገድ ላይ እየተኙ ነበር። ዋዲ ጋዛን ማለፍ ነው ሕልማቸው።
አዳም፡ በካሀን ዩኑስ አዳም በጎ ፈቃደኛ ነው። በአምስት ቀናት ለአምስተኛ ጊዜ ለመውጣት እየሞከረ ነው።
“ከሰሜን ጋዛ ወደ ደቡብ ጋዛ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንዲጓዙ ተጠይቋል። ሆኖም ግን ካሀን ዩኑስም ድብደባ አለ። ቤቴ አቅራቢያ ራሱ ተደብድቧል።”
እስራኤል ሙሉ ከበባ ስላደረገች መድኃኒት፣ ምግብ፣ ነዳጅ ተመናምኗል። አዳም ለአረጋዊ አባቱ እንክብካቤ መስጠት አልቻለም። ፓርኪንሰን አለባቸው። ሆስፒታል አልጋ ስላላገኙ መሬት ላይ ነው የተኙት።
ካሊድ፡ በጃባላ ነው የሚኖረው። መድኃኒት አቅራቢ ነው። ከቤቱ ጥሎ ለመውጣት ፈቃደኛ አይደለም።
“የት እንሄዳለን? የትም ቦታ ደኅና አንሆንም። የትም ብንሄድ እንሞታለን።”
ይህን መልዕክት በቪዲዮ ለቢቢሲ ሲልክ ከጀርባው የፍንዳታ ድምጽ ይሰማል። የአጎቱ ሁለት ልጆች ከጥቃት ከተረፉ በኋላ ከሱ ጋር ናቸው።
“የመድኃኒት እጥረት አለ። የተጎዳው ሰው በርካታ ነው። አንዳንድ መድኃኒት ማቀዝቀዣ ውስጥ መቀመጥ አለበት። መብራት ግን የለም።”
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ መድኃኒት ማድረስ አልቻለም።
ሰኞ ጥቅምት 16
ንጹኃንን ይዞ ወደ አል-ዲን ጎዳና እየተጓዘ የነበረ መጓጓዣ ተመታ። በአብዛኛው ሴቶችና ሕጻናት የሆኑ ሰባት ሰዎች ተገደሉ። የእስራኤል መከላከያ እጄ የለበትም ብሏል።
በደቡብ ጋዛ የአየር ጥቃት ሲባባስ ፍልስጤማውያን በሰሜን ጋዛ ቤታቸው መቆየት መረጡ። ወደ ደቡብ የተጓዙም ለመመለስ ወሰኑ።
ፋሪዳ፡ ለቀናት ጎዳና ላይ ተኝታለች።
“የሚሰማኝና እየሆነ ያለውን ለመግለጽ ቃላት የለኝም። ብዙ ቦምብ እየተጣለ ነው። በአቅራቢያችን ሕጻናት ያለቅሳሉ። የት መሄድ እንደምንችል አናውቅም።”
“በጋዛ ሁሉም ሌሊቶች ላይ ነገ ከእንቅልፍ ስለመንቃታችን እርግጠኛ አይደለንም። ሂጃቤን አድርጌ ከቤተሰቤ ጋር ተቀምጫለሁ። ለሚገጥመን አየር ጥቃት ራሴን ማዘጋጀት አለብኝ።”
- እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የትኞቹ አገራት ተቃወሙ? የትኞቹስ ደገፉ?8 ህዳር 2023
- ዶክተር፣ ልብስ ሰፊ፣ ጨቅላ ሕጻን…- በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደሉት መካከል የጥቂቶቹ አሳዛኝ ታሪክ5 ህዳር 2023
- “ይሄ የትንሿ ልጄ ፒጃማ ነው” 11 የቤተሰቡን አባላት በአንድ ጥቃት ያጣው የጋዛው አባት2 ህዳር 2023
ማክሰኞ ጥቅምት 17
አል-አሂል ሆስፒታል ፍንዳታ ደረሰ። 471 ሰዎች ተገደሉ። በሆስፒታሉ ሴቶችና ሕጻናት ተጠልለው ነበር። ከሞቱት መካከልም ይገኙበታል። እስራኤል እጄ የለበትም ብላ የፍልስጤም ኢስላሚስት ጂሀድን ተጠያቂ አድርጋለች።
አብደልከሪም፡ ጦርነቱ ከመነሳቱ ከወራት በፊት በሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ተመረቀ። አል ቡሬጅ ስደተኞች ማቆያ ነው የሚኖረው። በሆስፒታሉ ፍንዳታ ወቅት ብዙ ጓደኞቹ እዚያ እንደነበሩ ይናገራል። አንዱ ሲጎዳ ሌላው መላ ቤተሰቡን አጥቷል።
“23 ዓመቴ ነው። ለአሁን በሕይወት አለሁ። በሕይወት ሳለሁ ታሪኬ ስለመነገሩ እንጃ። ከላዬ ላይ በሚበሩት አውሮፕላኖች እገደል ይሆናል።”
“ውሃ የለንም። መድኃኒት የለንም። መብራት የለንም። ለሦስት ቀናት ምግብ አልቀመስኩም። ትንሽ ዳቦ ከቤተሰቤ ጋር ተካፍለን ነበር። ለ10 ወይም 12 ሰዓታት እኔም ቤተሰቦቼም አልተኛንም። ደክሞናል። ስለፈራን መተኛት አልቻልንም።”
ይህም መልዕክት ለቢቢሲ የላከው ባትሪ አብርቶ በቀረጸው ቪድዮ ነው።
እርዳታ በማከፋፈል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣል።
“እርዳታና ብርድልብስ እያዘጋጀን ነው። ልጆች ሳይቀሩ ያግዛሉ። እርዳታ ከግብፅ እስከሚመጣ ከመጠበቅ ይሄ ይሻላል።”

አርብ ጥቅምት 20
የአብደልከሪም ቤት በእስራኤል አየር ጥቃት ወደመ። የወደመውን ሕንጻ ቪድዮ ልኳል። ከኋላ ቤተሰቦች ለመውጣት ሲሞክሩ ጩኸት ይሰማል።
አብደልከሪም፡ “ቁጭ ብለን ነበር። ድንገት በሮኬት ተመታን። እንደምንም ከቤቱ ወጣን። ጎረቤቶቻችን አሁንም ፍርስራሽ ሥር ናቸው። ልንፈልጋቸው ሄድን። ግን ማንም የለም። እያንዳንዱ ደቂቃና ሰዓት ሞት አጥልቶበታል።”
“ቤተሰቤና እኔ በተዓምር ተረፍን። ቤታችንን ለማደስ እየሞከርን ነው። ቤታችን ሆነን ሞትን እንጠባበቃለን።”
ረቡዕ ጥቅምት 25
አብደልከሪም የሚኖርበት ሰፈር በድጋሚ በቦምብ ተመታ።
አብደልከሪም፡ “ልረዳቸው አልቻልኩም። በየቦታው የሰው አስክሬን ሳይ ደንዝዤ ቀረሁ። እዚህ ማንም ደኅና አይደለም። ሁላችንም መስዋዕት እንሆናለን።”
ይህን የላከው እያለቀሰ ነው። ከድምጽ መልዕክት በላይ መላክ አልቻለም።
የእርዳታ መኪና በራፋ ድንበር እንዲገባ ተፈቀደ። ግን ለጋዛ ተፈናቃዮች አይበቃም። ተመድ 1.4 ሚሊዮን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።
አዳም፡ “ጠዋት ተነስቼ እወጣለሁ። ምግብ ለማግኘት ረዥም ሰለፍ ይጠብቀኛል። ሁኔታው እየተባባሰ ነው።”
ምግብ ለማግኘት ቤተሰቡ ፍለጋ ቀጥሏል።
ካሊድ፡ “ቦምብ መጣላቸውን ቀጥለዋል። ያለ ዳቦ እንዴት እንኖራለን? ምግብ ማቆያም የለም። የተበላሸ ምግብ እንበላለን። ከተበላሸው ምግብ ውስጥ ነፍሳት እየወጡ ነው። የተበላሸውን ትተን ደኅና የሆነውን መመገብ ነው። ቆሞ ዳቦ መለመን ይሰብራል።”
ፋሪዳ፡ “ቤተሰባችን ወደ ሰሜን ለመመለስ ወስኗል። በደቡብ ጋዛ የምንፈልገውን ለማግኘት መቆያ የለንም። ቦምቡ ከፍተኛ ነው። ቤታችን ተመልሰን ቢያንስ በክብር እንቀመጥ።”
ከተመለሱ በኋላ የሚኖሩበት ጎዳና ተመትቶ ከፊል ቤታቸው ተጎድቷል።

አርብ ጥቅምት 27
ኢንርኔትና ስልክ በጋዛ ተቋረጠ። ለ48 ሰዓት በጋዛ ሰርጥ ግንኙነት ማድረግ አልተቻለም። እስራኤል በእግረኛ ጦር ወረራ ጀመረች። ቢቢሲ ከአዳም፣ አብደልከሪም፣ ፋሪዳ እና ካሊድ ጋር መገናኛት አልቻለም። ስልክ ሲሠራ ያሳለፉትን ጨለማ ጊዜ ተናግረዋል።
አብደልከሪም፡ “ትላንት ከፍተኛ ድብደባ ነበር። አምቡላንስ መጥራት እንኳን አልተቻለም። ሰው በየፍንዳታው ቦታ ሞተ።”
አዳም፡ “ይመስገነው ፈጣሪ ደኅና ነኝ። ስልክ ተቋርጦ ሳለ ግን አባቴ ሞተ። ነፍሱ በሰላም ትረፍ። የቅርብ ሰዎች ጋር ለመደወል እንኳን አቅም አጣሁ። ከጎኔ እንዲሆኑ መጠየቅ፣ የተፈጠውን መንገር አቃተኝ።”
ፋሪዳ፡ “ጓደኛዬን፣ ቤቴን አጣሁ። ወንድሜ ተጎድቷል። ሐዘን ልቤን በላው። ተሰብረናል።”
ካሊድ፡ “ቀኑ ደኅና ይመስል ነበር። ኢንተርኔት ሲመለስ ዜናውን ሰማን። ቤቶች፣ መንደሮች ወድመዋል። ሙሉ ቤተሰብ ተገድሏል። ያሳዝናል። ጭፍጨፋውን ሲጀምሩ ከዓለም ቆራረጡን።”

ሰኞ ጥቅምት 30
የእስራኤል ታንክ በጋዛ ከተማ ታየ። በዋና መተላለፊያው ሳሀል አል-ዲን ጎዳናም ጭምር።
ካሊድ፡ “አልወጣም። አሁን የምናስበው ቀጣዩ ቦምብ መጥቶ ገድሎን ሰላም እንድናገኝ ነው።”
እስራኤል በጃባሊያ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ቢቢሲ ካሊድን ለቀናት አላገኘም። በጥቃቱ ቢያንስ 101 ሰዎች ሲገደሉ፣ 382 ተጎድተዋል።
እስራኤል ዒላማዋ ከፍተኛ የሐማስ ኮማንደሮች እንጂ ንጹኃን እንዳልሆኑ ገልጻለች።
ፋሪዳ፡ “ሕልም አለኝ። ጥሩ ጓደኞችና ቤተሰቦች አሉኝ። መልካም ሕይወት ነበረኝ። አሁን ግን የማስበው ‘ስንሞት ማንም ሰው ምን እየተከናወነ እንደሆነ አያውቅም’ ብዬ ነው። እባካችሁ የምለውን ሁሉ ጻፉት። ታሪኬን ዓለም እንዲሰማ እፈልጋለሁ። ቁጥር ብቻ አይደሉም።”
አዳም፡ “ሁሉንም ታሪክ የምነግራችሁ እንዲመዘገብ ነው። ይሄ እንዲሆን የፈቀደው ዓለም እስከ ወዲያኛው መሸማቀቅ አለበት።”
የተመድ ባለሙያዎች በጋዛ “የዘር ጭፍጨፋን” ለማቆም ጊዜ እያለቀ ነው ብለው አስጠንቅቀዋል።
በጦርነቱ አራት ሳምንታት ከ10 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። አብዛኞቹ ንጹኃን ናቸው። ከ4 ሺህ በላይ ሕጻናትም ይገኙበታል።