ጁሊየስ ማሌማ

ከ 2 ሰአት በፊት

ከቀናት በፊት ሁለት ታዋቂ ሰዎች ለኬንያውያን የሚያድርጉት ንግግር በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። በተመሳሳይ ሰዓት እና ቦታ ግን አልነበረም።

የሁለቱም ንግግር በቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭት አግኝቷል።

ሁለቱም ሰዎች ለፓን አፍሪካዊነት ጽንሰ ሐሳብ ህይወታቸውን አሳልፈው እንደሰጡ ምለው ተገዝተው ይገልጻሉ። ሁለቱም በከባድ የምጣኔ ሐብት ጉዳይ ራስ ምታት የሆነባቸውን አገራት ወክለዋል።

የሁለቱ መመሳሰል ግን እዚህ ጋር ያከትማል።

የመጀመሪያው ግለሰብ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ሲሆኑ በሰማያዊ ሙሉ ልብስ ነው ወደ ቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ያሉት።

ሌላኛው ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ተቃዋሚ መሪ ጁሊየስ ማሌማ ነው። ማሌማ ጥቁር ልብስ እና የማትለየውን ቀይ ቆብ ለብሶ ነበር።

የፕሬዚዳንቱ ብሔራዊ ንግግራቸውን በፓርላማ ሲያቀርቡ በስነ-ስርዓት ቢከታተሏቸውም የድካም መንፈስ ይታይባቸው ነበር።

ማሌማ ንግግር ያደረገው የፓን አፍሪካን ኢንስቲትዩት በተከፈተበት ወቅት ነው። ንግግሩም በፉጨት እና በጭብጨባ ድጋፍ ይቋረጥ ነበር።

ቀኑ በዚህ መልኩ ተጠናቆም የሁለቱ ሰዎች ንግግር በኬንያ የንጽጽር እና የክርክር ማዕከል ሆኗል። የማሌማ ንግግር በበርካታ የኬንያ ዲጂታል መገናኛ ብዙሃን በድጋሚ ተሰራጭቷል። ተቆራርጦ ደግሞ እንደ ዋትስአፕ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለብዙዎች ደርሷል።

ማሌማ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት በፕሬዚዳንት ሩቶ ላይ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝሯል። ዋናው ደግሞ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የገቡትን ቃል አልተገበሩም የሚለው ነው።

የዩናይትድ ኪንግደሙ ንጉስ ቻርለስ በቅርቡ ኬንያን ጎብኝተው ነበር።

ሩቶ፣ ብሪታንያ በቅኝ ግዛት ላደረሰችው ግፍ ንጉሱን ምንም አለማለታቸው በደቡብ አፍሪካዊው ፖለቲከኛ እንዲኮነኑ አድርጓቸዋል።

በአፍሪካ አንድ የተለመደ ጉዳይ አለ። እንግዶች ስለሄዱበት አገር መጥፎ ነገር እንዳይናገሩ የሚል ያልተጻፈ ህግ አለ። ማሌማ ይህንን ጥሰው ኬንያ ደርሰው የኬንያን መሪ ተችተዋል። ማሌማ በዚህ ድርጊታቸው ለምን ተቀባይነት እንዳገኙ ለማወቅ ጥቂት ወራትን ወደ ኋላ መመለስ እንደሚገባ የሚዲያ ተንታኝ ሆኑት ኤልቪስ ንድክዌ ይገልጻሉ።

“በቁጣ የተሞሉ የአፍሪካ አገራት ዜጎች የኑሮ ውድነትን ለመታገል በአንድ ቀን ወደ ጎዳና የወጡበት አጋጣሚ ነበር። ተቃውሞ በደቡብ አፍሪካ፣ኬንያ፣ናይጄሪያ እና ቱኒዚያ ተቀስቅሷል። ጁሊየስ ማሌማም ተቃውሞውን ከመሩት መካከል ናቸው።”

ንድክዌ አክለውም ኬንያ ቀደም ሲልም ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገውባታል። ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ የሚመሩት ጥምረት የ2022 ምርጫ ተጭበርብሯል በሚል ተቃውሟቸውን በየጊዜው እያሰሙ ነበር።

ዘንድሮ በኬንያ ተቃውሞ በተደጋጋሚ ተከስቶ ነበር

“ብዙ ኬንያውያን በተለይም ወጣቱ ትውልድ ከጁሊየስ ማሌማ ጋር ተመሳሳይነት ላለው ዓላማ ሲታገሉ ቆይተዋል። ይህንንም ለጨቋኝ ወይም ቸልተኛ መሪዎች የተደረገ ተቃውሞ አድርገው ወስደውታል” ብለዋል።

ማሌማን ወደ ኬንያ የጋበዘው አዲሱ የፓን አፍሪካ ኢንስቲትዩት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ፒኤልኦ ሉሙምባ ሲሆን የንድክዌን ሃሳብ ይደግፋል።

“ማሌማ የፓን አፍሪካን ጉዳዮች ወሳኝና ብዙሃኑን በሚስብ መልኩ መግለጽ የጀመረውን ወጣት አፍሪካዊ ይወክላል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

“አስታውሱ፣ ይህ በጣም ወጣት አህጉር ነው” ከማለት ባለፈ አፍሪካ ወጣት መሪዎች ያስፈልጋታል ብሏል።

የ58 ዓመቱ ሩቶ ባለፈው ዓመት ራሳቸውን የመጪው ትውልድ ዕጩ በማድረግ ከ78 ዓመቱ ራይላ ኦዲንጋ ጋር ለፕሬዝዳንትነት ተፎካክረዋል። ማሌማ ገና 42 ዓመቱ ነው። ይህም የአብዛኛውን ወጣት መራጮችን ችግር ለማወቅ ቅርብ ነው።

በመጋቢት ወር በአራት አገራት ከተካሄዱ ሰልፎች በፊትም ማሌማ በኬንያ ብዙ ተከታዮች አሉት። ስሙም የገነነ ነው። አፓርታይድን በመኮነን፣ ደቡብ አፍሪካዊ መሬት የማግኘት መብቱ እንዲሁም በምጣኔ ኃብት ተጠቃሚነቱ ሊረጋገጥ ይገባል ሲልም ይሰማል።

በቀይ ቱታ ፓርላማ በመግባት የኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተር ፓርቲ አባላት በሚያደርጉት የጦፈ ክርክር በማድረግ፣ እንደ እሳት ወላፈን በሚጋረፉ ንግግሮቻቸው እና ፓርላማውን ለቀው በመውጣት ይታወቃሉ።

በፓርላማ የሚሰጧቸው አስተያየቶችን ኬንያውያን በስፋት ይቀባበሏቸዋል። ባለፈው ዓመት ሲዘዋወሩ ከነበሩ በአንዱ ቪዲዮ ስር አንድ ሰው አስተያየቱን “መቼም ቢሆን የማሌማን ንግግር አልጠግበውም …… የእውነት አምባሳደር እወድሃለሁ… ፍቅሬ ከኬንያ ይድረስህ” ሲል አስፍሯል።

እናም ማሌማ ኬንያ ሲደርስ በጉጉት የሚጠብቀው ታዳሚ መኖሩ እሙን ነው።

ንደክዌ እንደሚሉት ከሆነ ማሌማ ለፕሬዚዳንት ሩቶ ብቻ ሳይሆን ለተቀናቃኞቻቸውም ፈተናን ደቅነዋል።

“ለአንዳንድ ኬንያውያን ማሌማ የሌላቸውን ግን የሚፈልጉትን የተቃዋሚ መሪ የሚወክል ነው። ብዙዎችም ከራይላ ኦዲንጋ ጋር ያነጻጽሩታል። ማሌማ ወጣት፣ ኃለኛ፣ ደፋር እና የማይፈራ ነው። ሌሎችን ሊያናድድ ቢችልም ሃሳቡን ያስተላልፋል። የኬንያ ወጣቶች ይህን መሰሉን ባህሪ ራይላ ላይ አይመለከቱም።”

በኬንያ የሚኖርና ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ አንድ ጋዜጠኛ “የፕሬዚዳንቱ ብሔራዊ ንግግር መንግሥታቸው ከዚህ ቀደም የገባውን ቃል ቢደግሙም ማንም ጥያቄ አላነሳባቸውም” ብለዋል።

“ማሌማ መንግስትን በመቃወም አማራጭ ድምፅ ይሆናል። ከተለመደውና ብዙዎች ከተሰላቹበት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግርም ፋታ የሚሰጥ ነው።”

በማሌማ አስተያየት የኬንያ መንግስት ቁጣ የተቀላቀለበት ምላሽ ሰጥቷል። ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቻጉዋ “ጎብኚዎች ሲስተናገዱ የሚጎበኛቸውን አገራት መሪዎች እንዲያከብሩ ልንጠይቃቸው እንወዳለን። ወደ ባሕር ማዶ ስንጓዝ የእነዚያን አገራት መሪዎች አናንቋሽሽም። በፖለቲካ ጉዳያቸውም ላይ ጣልቃ አንገባም” ሲሉ ምክር ቢጤ ሰጥተውታል።

“እዚህ የመጣው ሰው ሁሉን አዋቂ ነው። በሰዓታት ውስጥ ስለኬንያ ከእኛ የበለጠ የሚያውቅ ይመስለዋል። በታህሳስ አገሩን ጎበኝቼ ነበር። መብራት ለሰባት ሰዓታት ብቻ በፈረቃ ይዳረሳል። ስለምናከብራቸው ግን ምንም አላልንም።” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

ምላሽ የሰጠው ግን መንግሥት ብቻ አይደለም። ብዙ ኬንያውያን የውጭ አገር ዜጋ የውስጥ ጉዳያቸውን እንዴት እንደሚመሩ ማስተማር እንደሌለበት ገልጸዋል። ሌሎች ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ንግግር ባደረጉበት ዕለት እሳቸውን በመተቸቱ ቅር ተሰኝተዋል።

በአንዲት አጭር ጉብኝት ይህ ሁሉ ሁካታ ከመፍጠሩ አንጻር የአዲሱ የፓን አፍሪካ ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች ማሌማን ለምን ወደ ኬንያ ጋበዙት?

ታዋቂው እና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኙ ፕሮፌሰር ሉሙምባ “ምርጫው በአንዳንድ መሠረታዊ ነገሮች የተገለፀ ነበር” ብለዋል።

“አንዱ ማሌማ የአፍሪካ አህጉርን በሚመለከቱ በአፍሪካ ያልተገደበ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር፣ በአፍሪካ የሰዎች ነጻ እንቅስቃሴ እና አፍሪካውያን ጉዳዮቻቸውን እንዲመሩ ማድረግ ላይ በድፍረት በመናገሩ ነው።“

“በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ማሌማ ‘አፓርታይድን ገድለናል ብትሉም እንኳን አፓርታይድ አሁንም በህይወት አለ’ የሚለውን ትውልድ ይወክላል። ይህ ደግሞ ለእኛም ያስተጋባል። በተጨማሪም ደፋር በመሆኑ ምን ያስከትልብኝ ይሆን ሳይል ያለ ምንም ፍርሃት ይናገራል። ብዙዎቻችን ቃላቶቻችንን የምንመርጠው ውጤቱን ስለምንፈራ ነው።”

ብዙ ኬንያውያን ማሌማን የተቀበሉት ለምን ይሆን? ተብለው ፕሮፌሰር ሉሙምባ ተጠይቀዋል።

“በኬንያ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ እየሆነ ባለው እና እየተከሰተ ባለው ነገር ቅር የተሰኘ እና ዝምታ ውስጥ ያሉ ብዙ ኬንያውያን አሉ። ምክንያቱም በመድረክ ላይ ያሉት ኬንያውያን በአጠቃላይ ግብዞች ናቸው። ማለት የሚፈልጉትን እንደፈለጉ አይናገሩም። ስለዚህ ማሌማ እንደ እንግዳ መጥቶ መናገር የምንፈልገውን ነገር ግን የማንናገረውን ነገር ተናገረ።”

ብዙ ኬንያውያን ማሌማን ቢደግፉም ወደ አገሩ ደደቡብ አፍሪካ ስንመለስ ግን የዘር ግጭት ቀስቅሷል በሚል የሚከሰስ አከራካሪ ሰው ነው።

በተደጋጋሚ በጥላቻ ንግግር ተከሷል። ፓርቲው የ13 በመቶ መራጮችን ድጋፍ በማግኘት በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከህዝብ የተሰበሰቡ አስተያየቶች ያሳያሉ።

ባለ ቀይ ኮፍያው ግለሰብ ኬንያን ለቆ ወጥቷል። ሰማያዊ ሱፍ የለበሱት ፕሬዝዳንት ግን ለኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸው መፍትሔ ለመሻት ከባድ ኃላፊነት አለባቸው።