ዛሬ ህደር 3 ቀን 2016 ዓ.ም በመቐለ የታክሲ አገልግሎት ተቋርጦ ውሏል።
የመቋረጡ ምክንያት የታክሲ ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች በአጠቃላይ አድማ ላይ በመሆናቸው ነው።
የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ አባል የመቐለ ታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች አጠቃላይ አድማን ተከትሎ የተፈጠረውን መስተጓጎል በአካል ተገኝቶ ቃኝቷል።
ከለሊቱ 11:30 የታክሲ ረዳቶች ጩኸት የማይለይባት የመቐለ ከተማ ያለወትሮዋ የህዝብ ታክሲ የጠፉባት ሆና ውላለች።
ከከተማዋ የተለያዩ ጫፎች ወደ መሃል ከተማ ከ20 እስከ 10 ብር በመክፈል ሰው በሰው ላይ ተደራርበው ተጨናንቀው የሚጓጓዙት ተሳፋሪዎች በመንገድ ዳር ቆመው በብዛት ታክሲ ሲጠብቁ ነበር።
ተገልጋዮች ዝር የሚል ታክሲ ሲያጡ የመክፈል አቅም ያላቸው በባጃጅ ኮንትራት ከፍለው ሲጓዙ አቅሙ የሚያጥራቸው ደግሞ በእግራቸው ለመጓዝ ተገደዋል።
የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ሪፓርተር ረፋድ አከባቢ ታክሲዎች አድማ መምታቸውን ለመገንዘብ ችሏል።
የታክሲ አገልግሎቱ መቋረጥ አስመልክቶ ተገልጋዮች አነጋግሯል።
ወዲ ቐሺ ፣ ዘርኣያዕቆብና ሰናይት የተባሉት ተጠቃሚዎች እንደሚሉት ፤ ” የታክሲዎች አድማ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታየው በሃይል በመጫን ፍላጎት ለማሳካት የመሻት ዝንባሌ ነው ” ብለዋል።
የታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ግን የተገልጋዮቹን አስተያየት ፍፁም በመቃረን ፤ ህዝብ የመበዝበዝና የማጉላላት ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸዋል።
ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመሄድ ላይ የሚገኘው የኑሮ ሁኔታ ፣ የመኪና እቃ መለዋወጫ መወደድ (የመኪና 5 ሊትር ዘይት ከብር 500 በአምስት እጥፍ ጨምሮ ወደ ብር 2500 ከፍ ማለቱ እንደ ማሳያ ይጠቅሳሉ) ፤ የሹፌርና የረዳት ክፍያን ገበያ ላይ ባለው ታሪፍ መሸፈን እጅግ እንደከበዳቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ገልፀዋል።
የታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች በማከልም አሁን ባለው 10 ብር ለአንድ ተሳፋሪ ታሪፍ ኑሮአቸውን አሸንፈው የመኪኖቻቸው ድህንነት ለመጠበቅ እንደሚቸገሩ ፤ ስለሆነም መንግስት ታሪፉ እንዲያስተካክል ከአንድ ወር በፊት በማህበራቸው በኩል ጥያቄ እንዳቀረቡ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ መንግስት ጥያቄያቸው መመለስ ትቶ አንድ ሰው ተርፍ ጭነው ከተገኙ ብር 500 መቅጣቱ አጠቃላይ የስራ የማቆም አድማ እንዲያደርጉ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።
የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ አባል ስለ ጉዳዩ የመንግስት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፤ ከመንግስት የሚሰጠው ምላሽና የታክሲ ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች ቀጣይ እርምጃ ተከታትሎ ያቀርባል።
@tikvahethiopia