
14 ህዳር 2023
ዩናይትድ ስቴትስ፤ ሶሪያ የሚገኙ በኢራን አብዮታዊ ዘብ ጥቅም ላይ የሚውሉ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በአየር ጥቃት ማውዷሟን ፔንታገን ገልጧል።
የመከላከይ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስቲን ይህ ምላሽ የተሰጠው ኢራቅና ሶሪያ ውስጥ በአሜሪካ መቀመጫዎች ላይ በኢራን የተደገፉ ኃይሎች ላደረሱት ጥቃት ነው ብለዋል።
መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው አንድ የጦርነት ሂደቶች ተቆጣጣሪ ቢያንስ ስምንት የኢራን ደጋፊ ታጣቂዎች ተገድለዋል ብሏል።
አሜሪካ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ የአየር ጥቃት ስታደርስ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ባለው ጦርነት ምክንያት ቀጣናው ውጥረት ላይ ባለበት ወቅት ነው አሜሪካ ጥቃቱን የሰነዘረችው።
ኦስቲን እንዳረጋገጡት ጥቃቱ የተፈፀመው በምስራቃዊ ሶሪያ አልቡ ካማል እና ማያዲን ከተሞች በሚገኝ የሥልጠና ማዕከል ላይ ነው።
ሚኒስትሩ አክለው ጥቃቱ እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጡት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን “አሜሪካ ራሷን፣ ወታደሮቿንና ጥቅሟን እንደምትከላከል ለማሳየት ነው” ብለዋል።
ፔንታገን ስለጥቃቱ ከዚህ የበለጠ መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
- የጋዛ ታሪኮች፡ “ስንሞት ማንም አያውቅም”13 ህዳር 2023
- በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ሥራ ለማቆም ተቃርቧል12 ህዳር 2023
- የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ወደ መቃብር ስፍራነት እየተቀየረ ነው- የዓለም ጤና ድርጅት12 ህዳር 2023
ነገር ግን የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ተቆጣጣሪ ስምንት ሰዎች ከመገደላቸው በተጨማሪ ሰባት ቆስለዋል፤ አብዛኛዎቹ ደግሞ ሶሪያዊያን አይደሉም ብሏል።
መቀመጫውን ዩኬ ያደረገው ይህ ድርጅት የአየር ጥቃቱ አቡ ካማል በተሰኘው የኢራቅ ድንበር ላይ የምትገኝ ከተማ ላይ መድረሱን አረጋግጧል።
ድርጅቱ አክሎ በኢራን የሚደገፉት ታጣቂዎች ምሽቱን ወደ አሜሪካ ወታደራዊ መቀመጫዎች ሮኬት ቢተኩሱም የተገደለ ሰው ግን የለም ብሏል።
ፔንታገን እንደሚለው የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በኢራን የሚደገፉት ኃይሎች ኢራቅ እና ሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ መቀመጫዎች ላይ 41 ጊዜ ጥቃት አድርሰዋል።
ሚኒስቴሩ አክሎ እንደገለጠው 56 ሰዎች አነስተኛ የአካልና የአእምሮ ጉዳት ቢደርስባቸውም እንክብካቤ ተደርጎላቸው ወደ ሥራ ተመልሰዋል።
አሜሪካ እንደምትለው ጥቃቶቹ እየተፈፀሙ ያሉት በኢራን በሚደገፉ በሥፍራው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ነው።
ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ለ12 ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ወዳለችው ሶሪያ አሰማርታ ለፕሬዝደንት ባሽር አል-አሳድ ድጋፍ ትሰጣለች ተብላ ትወቀሳለች።
አልፎም በሺዎች ለሚቆጠሩ የሺያ ሙስሊሞች ሥልጠና እና የገንዘብ ድጋፍ ትሰጣለች፤ በተለይ ደግሞ ለሌባኖሱ ሔዝቦላህ ድጋፍ ከማድረጓ ባለፈ በኢራቅ፣ አፍጋኒስታንና የመን የሚገኙ ታጣቂዎችን ትደጉማለች።
በጋዛ ሰርጥ ያለው ጦርነት እየተፋፋመ መሆኑን ተከትሎ ግጭቱ ወደቀጣናው ይስፋፋል፤ ኢራንም በእስራኤልና ሐማስ ጦርነት ገብቶ ሥፍራው ወደከፋ ጦርነት ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
አሜሪካ በቅርቡ ያደረጋቻቸው የአየር ጥቃቶች ከጋዛ ግጭት ጋር የሚያያዙ እንዳልሆኑና ከእስራኤል ጋር በመተባበር ያደረገችው እንዳልሆነ ትናገራለች።
ባለፈው ወር ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለኢራኑ ጠቅላይ ገዥ አያቶላህ አሊ ካሜኒ በቀጥታ በላኩት መልዕክት መካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ዒላማ ማድረግ እንዲያቆሙ ተናግረዋል።
