
ከ 8 ሰአት በፊት
ኔፓል በቲክቶክ የሚተላለፉ ይዘቶች ‘ማኅበራዊ መስተጋብርን ያደፈርሳሉ’ በሚል ምክንያት ግዙፉን የቻይና መተግበሪያ አገደች።
ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ ወርሃዊ ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክቶክ በሕንድ እና ፓኪስታን ጨምሮ በተለያዩ አገራት እግድ ተላልፎበታል። ሞንታና መተግበሪያውን በማገድ የአሜሪካ የመጀመሪያዋ ግዛት መሆኗ ይታወሳል።
ቲክቶክ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ ይሰጣል ከተባለ በኋላ በበርካታ መንግሥታት በአይነ ቁራኛ ይታያል።
የኔፓል የኮሚኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስትር ሬክሃ ሻርማ በቲክቶክ የሚተላለፉ ይዘቶች አሉታዊ ተጽእኖ ያላቸው ናቸው ብለዋል።
ሚንስትሯ ጨምረውም የእግድ ትዕዛዙ በአስቸኳይ የሚፈጸም መሆኑን እና የቴሌኮም አስተዳዳሪዎች ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንደተነገራቸው ጨምረው ተናግረዋል።
- የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ወደ መቃብር ስፍራነት እየተቀየረ ነው- የዓለም ጤና ድርጅት12 ህዳር 2023
- “ኢትዮጵያ በኤርትራም ሆነ ጅቡቲ ላይ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የላትም ” ጠ/ሚ ዐቢይ14 ህዳር 2023
- በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው ውይይት በምን ሁኔታ ላይ ነው?14 ህዳር 2023
የኔፓል መንግሥት መተግበሪያውን የሚያግደው ይዘቶቹ ጎጂ ናቸው በሚል ምክንያት ይሁን እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ውሳኔው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፍ ነው ብለዋል።
ጋጋን ታፓ የተባሉ የምክር ቤት አባል መንግሥት በቲክቶክ የሚተላለፉ ይዘቶችን ሳንሱር ማድረግ አለበት እንጂ መተግበሪያውን ጨርሶ መዝጋቱ የመብት ጥሰት ነው ብለዋል።
ቲክቶክ ከተጠቃሚዎች ቁጥር አንጻር ከፌስቡክ እና ኢንስታግራም ጋር ባይነጻጸርም ወጣት የሆኑ ተጠቃሚዎቹ በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረለት ነው።
በኔፓል ብዙ ተጠቃሚዎች ካሏቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎች መካከል ቲክቶክ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
