
14 ህዳር 2023, 11:32 EAT
በኦሮሚያ ክልል ለዓመታት የዘለቀውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በፌደራሉ መንግሥትና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል በታንዛንያ እየተካሄደ ያለው ሁለተኛው ዙር ንግግር ሳምንት አስቆጠረ።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በዋና አዛዡ ኩምሳ ድሪባ እና በምክትሉ ገመቹ አቦዬ በሚመራ ልዑካን የታንዛንያው የሰላም ውይይት ተሳታፊ መሆኑንም ትናንት ህዳር 3/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ውይይቱ ሳምንት ቢሆነውም የጦር አዛዦቹ ተሳታፊ መሆናቸው ይፋ የተደረገው በትናንትናው ዕለት ነበር።
የጦር አዛዦቹ ከኦሮሚያ ጦር ግንባር ወደ ታንዛንያ የሚያደርጉት ጉዞ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ዘግየት ብሎ መግለጹንም ሰራዊቱ አስታውቋል።
በመጀመሪያው ዙር ውይይት የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ ከቅርብ ቀናት በፊት ታንዛንያ መግባታቸውንም ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ልዑካን በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተዛምቶ ለበርካቶች እልቂት ለሆነው ጦርነት እልባት ለማግኘት የፌደራሉን መንግሥት ወክለው በፕሪቶሪያ ከህወሓት ጋር የተደራደሩት ልዑካን አባል መሆናቸው ይታወሳል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል በዳሬሰላም ሐያት ሬጀንሲ ሆቴል እየተካሄደ ያለው የሰላም ንግግር “በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ” መሆኑን ውይይቱን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች ከቀናት ውይይት በኋላ “በተጨባጭ ጉዳዮች ላይ” ወደ መነጋገር መሸጋገራቸውንም አዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የሁለተኛውን ዙር ውይይት የተሳካ ለማድረግ ዝግጅቶች ቀደም ብለው መደረጋቸውን የገለጹልን አንድ ምንጭ አሁን ውይይቱ እየሄደ ያለበት መንገድ “ተስፋ ሰጪ ነው” ብለዋል። ይኸው ምንጭ ውይይቱ ፍሬ ማፍራት ከቻለም የሰላም ስምምነት ሊፈረምም እንደሚችልም ተስፋቸውን ተናግረዋል።
“የህዝባችንን ምኞት እውን የሚያደርግ እና የሰማዕት ጓዶቻችንን መስዋዕትነት የሚያከብር ሰላማዊ የፖለቲካ እልባት ለማበጀት ሁሌም ቁርጠኛ ነን” ብሏል የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ትናንትና ባወጣው መግለጫ
ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸውን በሰላም ለመቋጨት በሚያደርጉት ውይይት አሜሪካ፣ ኢጋድ፣ ኖርዌይ እና ኬንያ የአሸማጋይነት ሚና እየተጫወቱም እንደሆነ ቢቢሲ ለውይይቱ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሰምቷል።
- መንግሥትን እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ያገናኘችው ታሪካዊቷ ዛንዚባር12 ግንቦት 2023
- መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ያላስማማው የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጉዳይ መሆኑ ተነገረ3 ግንቦት 2023
- ኬንያ እና ኖርዌይ የመንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ንግግርን እያሸማገሉ እንደሆነ ተጠቆመ27 ሚያዚያ 2023
የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የትግራይ ኃይሎችን በማሸማገል ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በታንዛንያ እንደሚገኙም ተነግሯል።
በመጀመሪያው ዙር ንግግር ኬንያ እና ኖርዌይ የአሸማጋይነት ስፍራ የነበራቸው ሲሆን የአሜሪካ ዲፕሎማቶችም ድጋፍ እየሰጡ እንደነበር ቢቢሲ ለውይይቱ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሰምቶ ነበር።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በአምስት ከፍተኛ የጦር አዛዞዦች እና በሁለት የዲፕሎማሲ ተወካዮች በአጠቃላይ በሰባት ልዑካን ተወክሏል።
በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና ባለስልጣናትን ጨምሮ ሰባት ልዑካን በውይይቱ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
ከፌደራሉ መንግሥት ልዑካን በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልል ሁለት ተወካዮች በውይይቱ ላይ መገኘታቸውን ቢቢሲ ሰምቷል።
ከስድስት ወር በፊት በታንዛኒያ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ዛንዚባር ያደረጉት የመጀመሪያው ዙር የሁለቱ አካላት ንግግር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
በመጀመሪያው ዙር ውይይት ሁለቱን አካላት ካላስማሙ ጉዳዮች መካከል አንዱ የጋራ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ መሆኑ ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን እና ብልጽግናን ጨምሮ ሌሎች ፓለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ የጋራ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጠይቆ እንደነበርም ቢቢሲ ለውይይቱ ቅርበት ካላቸው አካላት ሰምቶ ነበር።
የጋራ የሽግግር መንግሥት ምሥረታው በፌደራል መንግሥቱ ተደራዳሪዎች በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱም ተዘግቦ ነበር።
