የእርዳታ እህል የተሸከመ ሰው

ከ 5 ሰአት በፊት

የአሜሪካ መንግሥት በዓለም አቀፉ የተርድዖ ድርጅቱ ዩኤስኤይድ አማካኝነት በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካቢዎች ለሚገኙ ሰዎች ያቀርበው የነበረውና አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ ከ15 ቀናት በኋላ ዳግም ሊጀምር እንደሆነ አስታውቋል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ስታቀርብ የቆየችው የምግብ እርዳታ ላልተገባ ዓላማ እንደዋለ ከገለጸች በኋላ ማስተካከያ እስከሚደረግ በሚል በሁሉም አካቢዎች የነበረውን የምግብ እርዳታ ባለፈው ዓመት አቋርጣ ነበር።

የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት ወይም ዩኤስኤይድ ትናንት ማክሰኞ ኅዳር 4/2016 ባወጣው መግለጫ ተቋርጦ የቆየው እርዳታው ከኅዳር 21/2016 ጀምሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነትና በምስራቅ አፍሪካ ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተከሰተው የከፋ ድርቅ በኢትዮጵያ ያለው የምግብ አቅርቦት ቀውስ እንዲስፋፋ ሰበብ ሆኗል።

ዩኤስአይዲ ባወጣው መግለጫ የምግብ እርዳታው ላልተገባ አላማ እንዳይውል ያደረገውን ማሻሻያ በቀጣዩ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙከራ እንደሚያደርግ ገልጿል።

በዚህ የሙከራ ጊዜ በዩኤስኤይድ፣ በኢትዮጵያ መንግሥትና በአጋሮች የሚተገበረውን የአዲሱን አሰራር ውጤታማነት በተከታታይ እንደሚቆጣጠርና እንደሚገመግም አስታውቋል።

ዩኤስኤይድ በኢትዮጵያ አቋርጦት የቆየውን እርዳታ ለመጀመር ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችና ድርድር ሲደረግ መቆየቱን በመግለጫው ጠቅሷል።

በዚህም ሳብያ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን ባደረገው የማሻሻያ ስራ የእርዳታ ምግብ ተደራሽ የሚሆንበት አዲስ መዋቅር መዘጋጀቱን አሳውቋል።

ይህ ማሻሻያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በተገቢ መንገድ እርዳታ እንዲደርሳቸው የሚያስችል ነው ተብሏል።

ዩኤስኤይድ ባወጣው መግለጫ አዲሱ የእርዳታ ማሰራጫ መዋቅር በኢትዮጵያ ያለውን የምግብ እርዳታ ስርዓት እንደሚቀይረው ያመላከተ ሲሆን “ትክክለኛ የምግብ ዋስትና ችግር ያጋጠማቸውን ተደራሽ ለማድረግ ይረዳል” ሲልም አክሏል።

አዲሱ አሰራር የእርዳታ ተደራሽነትን ለመቆጣጠርና ለመከታተል እንደሚያግዝ የተመላከተ ሲሆን ይህንኑ አሰራር ለመተግባር የሚያስችል ለውጦች ለማደረግ የኢትዮጵያ መንግሥት መስማማቱን ገልጿል። በተጨማሪም መንግሥት ያልተስተጓጎለ የእርዳታ አቅርቦት ተደራሽነት ለመፍቀድ ቁርጠኛ ነው ብሏል።

ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ዩኤስኤይድ በኢትዮጵያ የሚያቀርበው እርዳታ ለስርቆት መዳረጉን በመግለጽ አቅርቦቱን ማቋረጡን ገልጾ ነበር።

ከሳምንታት በፊት ደግሞ ተቋርጦ የቆየውን እርዳታ ለስደተኞች ብቻ መጀመሩን አስታውቋል።

በተመሳሳይ ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ እርዳታ ላልተገባ ዓላማ በመዋሉ በመጥቀስ ለአገሪቱ የሚያደርገውን የምግብ ዕርዳታ አቋርጫለሁ ማለቱ ይታወሳል።