በሆስፒታሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተጠለሉ ይታመናል

ከ 5 ሰአት በፊት

አሜሪካ ሐማስ በጋዛ ከተማ በሚገኘው እና ትልቅ በሆነው አል-ሺፋ ሆስፒታል ስር የማዘዣ ማዕከል እንዳለው የሚያሳይ መረጃ እንዳላት ገለፀች።

የብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ የሆኑት ጆን ኪርቢ እንዳሉት ቡድኑ በዚያ መሳርያ እነደሚያከማች እና ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ መረጃ እስራኤል ሐማስ ሆስፒታሎችን የማዘዣ ጣብያዎቹን ለመሸሸግ ይጠቀምባቸዋል የሚለውን ውንጀላዋን የሚደግፍ ሲሆን ከአጋሮቿ የተሰማ የመጀመርያው መረጃም ነው።

መግለጫው የወጣው እስራኤል ንጹኀን ዜጎችን ከጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነት አለባት የሚል ጫና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት እየተሰነዘረባት ባለበት ሰዓት ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዳሉት አል-ሺፋ ሆስፒታል በዙሪያው ከሚደረጉ ከባድ ውግያዎች “መጠበቅ አለበት” ያሉ ሲሆን የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕጎች መሰረት መንቀሳቀስ አለባት ብለዋል።

ከቅርብ ቀናት ወዲህ በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል በሆነው አል-ሺፋ ዙርያ ያለው አካባቢ ከባድ ውግያ የሚካሄድበት የጦር ቀጠና ሆኗል።

በሆስፒታሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ይታመናል።

ሚስተር ኪርቢ አሜሪካ ከተለያዩ ወገኖች ያሰባሰበቻቸው የራሷ የደህንነት መረጃዎች ነበሯት ያሉ ሲሆን፣ ሐማስ እና እስላማዊ ጂሃድ በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሆስፒታሎችን እንዲሁም መሬት ለመሬት የተቆፈሩ ዋሻዎችን የወታደራዊ አንቅስቃሴዎቻቸውን ለመሸፈን እና ያገቷቸውን ሰዎች ለማቆየት ይጠቀሙባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም አሜሪካ አስተዳደር ሐማስ ሆስፒታሎችን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎቹን ለመሰወር ይጠቀምበታል የሚለውን መረጃ ከሌሎች አካላት ስትጠቅስ እንጂ መረጃው እንዳላት ስትናገር ተሰምታ አትታወቅም።

“ሐማስ እና ፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ አባላት የማዘዣ ዕዛቸውን የሚያንቀሳቅሱት እና የሚቆጣጠሩት ጋዛ ከተማ ከሚገኘው የአል ሺፋ ሆስፒታል ነው” ብለዋል።

“በዚያ የጦር መሳርያ አከማችተዋል እናም እስራኤል ለምትወስደው እርምጃ ከሆስፒታሉ በመሆን የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል” ሲሉ ያክላሉ።

ኪርቢ የእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ ምን ያህለ ፈታኝ እንደሚሆን ያሳያል ካሉ በኋላ “ሐማስ ራሱን በንጹኀን ዜጎች መካከል ምን ያህል አስርጎ እንዳስገባ ያሳያል” ሲሉ አክለዋል።

“ግልጽ ለመሆን፣ ሆስፒታሉ ላይ የሚፈጸምን የአየር ጥቃት አንደግፍም። እንዲሁም ሰላማዊ፣ ከለላ የሌላቸው ረዳት አልባ ሰዎች፣ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት በሆስፒታሉ የሚገኙ ሕሙማን በሚገኙበት የተኩስ ልውውጥ እንዲካሄድ እና በዚያ መካከል እንዲጎዱ አንፈልግም። ሆስፒታሎች እና ሕሙማን ጥበቃ ማግኘት አለባቸው” ብለዋል።

“በተደጋጋሚ ግልጽ ለማድረግ እንደሞከርነው የሐማስ ድርጊት እስራኤል በጋዛ ንፁኀንን መከላከል ያለባትን ኃላፊነት የሚቀንስ አይደለም፣ ይህ ደግሞ ከአጋሮቻችን ጋር የምንነጋገርበት ጉዳይ ይሆናል።”

ሐማስ ከዋይት ሐውስ ስለተሰማው መረጃ ማክሰኞ እለት ምላሹን ለኤኤፍፒ የሰጠ ሲሆን እስራኤል የዋሺንግተንን ትንታኔ በሕክምና ተቋሙ ላይ “ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ለማካሄድ” “ይሁንታን” እንዳገኘች አድርጋ በመጠቀም “ የጋዛን ጤና ክብካቤ ስርዓትለማፍረስ እና ፍልስጤማውያንን ለማፈናቀል” ትጠቀምበታለች ብሏል።

በአልሺፋ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ዶክተሮች እንዳሉት ከሆነ በርካታ ሰዎች፣ ሦስት ከጊዜያቸው ቀድመው የተወለዱ ህጻናትን ጨምሮ ነዳጅ፣ መድሃኒት እና የኤሌትሪካ ኃይል ባለመኖሩ ምክንያት መሞታቸውን ተናግረዋል።

አክለውም ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከ100 በላይ የሞቱ ሰዎች አስከሬን ሳይቀበር በግቢ ውስጥ ተከማችቶ ይገኛል።

በተጨማሪም ማንም በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ አልያም ቅጥር ግቢ ውጪ ወጥቶ ለመንቀሳቀስ የደፈረ ግለሰብ በአካባቢው ባለው ግጭት የተነሳ ሕይወቱን ለአደጋ አጋልጦ መሆኑን አስረድተዋል።

እስራኤል ምንም እንኳ በሆስፒታሉ ሐማስ ይገኛል ብላ ብታምንም እስካሁን ወደ ሕክምና ተቋሙ አለመተኮሷን ትናገራለች።

የእስራኤል መከላከያ በአሜሪካ፣ ዩኬ እና የአውሮጳ ሕብረት በአሸባሪነት የተፈረጀውን እና በጋዛ ሰርጥ የሚንቀሳቀሰውን ሐማስን ለማጥፋት ቃል ገብታ ዘመቻ ከጀመረች አንድ ወር አልፏታል።