
14 ህዳር 2023
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ጨምሮ 31 አውሮፕላኖች ለመግዛት ከአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ጋር ከስምምነት ደረሰ።
አየር መንገዱ ግዢ ለመፈጸም ከስምምነት የደረሰው ግዙፉን 11 ቦይንግ 787 ድሪምላይነር እንዲሁም 20 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ነው።
ቦይንግ እና አየር መንገዱ የደረሱት ስምምነት ከ31ዱ አውሮፕላኖች ውጪ በተጨማሪነት 15 ቦይንግ 787 ድሪም ላይነር እና 21 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን የመግዛት አማራጭን ያካተተ ነው።
አየር መንገዱ ለመግዛት የተስማማው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከአምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ ባጋጠመ አደጋ ምክንያት ከበረራ የታገደው አውሮፕላን መሆኑ ይታወቃል።
ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ሲበር አደጋ ያጋጠመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ አውሮፕላን የአደጋው መንስዔ ከበረራ ስርዓት ጋር የተያያዘ ነው መባሉን ተከትሎ አውሮፕላኑ በመላው ዓለም ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን ተደርጎ ነበር።
በዱባይ ኤየር ሾው ላይ ስምምነቱ ይፋ ሲደረግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው “አውሮፕላኑ የነበረበት የዲዛይን ስህተት በቦይንግ መስተካከሉን አረጋግጠናል” ስለማለታቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
“በዚህ አውሮፕላን ላይ ያለንን እምነት አድሰናል” ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው።
- “ኢትዮጵያ በኤርትራም ሆነ ጅቡቲ ላይ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የላትም ” ጠ/ሚ ዐቢይ14 ህዳር 2023
- የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ወደ መቃብር ስፍራነት እየተቀየረ ነው- የዓለም ጤና ድርጅት12 ህዳር 2023
- በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው ውይይት በምን ሁኔታ ላይ ነው?14 ህዳር 2023
የግዢ ስምምነቱ መፈረምን በተመለከተ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ 787 ድሪምላይነር እና 737 ማክስ አውሮፕላኖች የነዳጅ ፍጆታቸው እንዲሁም የሚያስከትሉት የአየር ብክለት ከሌሎች አውሮፕላኖች ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ነው ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የመንገደኞችን ምቾት እና ፍላጎት በመጠበቅ ተመራጭነቱን ለማሳደግና ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደሚረዳው አየር መንገዱ አስታውቋል።
መስፍን ጣሰው ጨምረው እንደገለጹት አየር መንገዱ ከግዙፎቹን ቦይንግ 777ኤክስ ወይም ኤየርባስ ኤ350 መካከል አንዱን በቀጣይ ወራት ግዢ እንደሚፈጽም ያስታውቃል ብለዋል።
መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤየርባስ ኤ220 አውሮፕላንን የመግዛት ፍላጎት ቢኖረውም አውሮፕላኑ ባለበት የሞተር ችግር ምክንያት የግዢ ትዕዛዝ የመስጠት ፍላጎት የለንም ብለዋል።
የዚህ አውሮፕላን ሞተር የአገልግሎት ዘመኑ ማጠሩ፣ የመለዋወጫ እና የጥገና ችግር መኖሩ አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊ እና ግዙፍ የሆኑትን 20 ኤየር ባስ ኤ350 እና 10 ቦይንግ 787-9 ጨምሮ 147 አውሮፕላኖች አሉት።