November 15, 2023 

መብታችንን በመጠየቃችን ለእስር እና እንግልት እየተዳረግን ነው ሲሉ የኮሬ ዞን ነዋሪዎች ቅሬታቸውን አቀረቡ

(አዲስ ማለዳ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን አልፋጮ ቀበሌ ነዋሪዎች መብታችንን በመጠየቃችን ለእስር እና እንግልት ተዳርገናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

የአልፋጮ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑትና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ እንደገለጹት “በአዲሱ አደረጃጀት መሰረት የተቋቋመው ወረዳ በዞኑ ያሉ ቀበሌዎችን ያላማከለ እና የልማት ተጠቃሚ የማያደርግ ነው” ብለዋል።

የተቋቋመው ወረዳ ለኮሬ ዞን 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ሲሆን ከቀበሌው ወደ ዞኑ መንገድ ያልተሰራ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪ “በእጁ እየቆፈረ ያበጃጀው መንገድ ብቻ ያለ ሲሆን በሞተር ሳይክል ወደ ከተማ ለመጓዝ ለአንድ ሰው ደርሶ መልስ 4000 ሺህ ብር ያስፈልጋል” ሲሉ ገለጸዋል።

አክለውም  “ወደ ወረዳው ሄዶ ጉዳዮችን ለማስጨረስ የፈለገ ገበሬው ምናልባት መሬቱን ሽጦ ሊሆን ይችላል የሚሄደው ያካልሆነ ግን ከሁለት ቀን በላይ በእግሩ መሄድ ይጠበቅበታል” ብለዋል።

ስለሆነም  ጥያቄያችን ለዞኑ ያቀረብን ሲሆን የዞኑ አስተዳዳሪ ከመከላከያ ሰራዊት የተቀነሱ ወይም ሸሽተው የመጡ አካላትን ከባባድ መሳሪያ አስታጥቆ ሰዉን እያሰሩ እና እያንገላቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስር ሂደቱም ይሄ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 16 ያህል ሰዎች ከተለያዩ ቀበሌዎች መታሰራቸውን ነዋሪው የገለጹ ሲሆን ለማሰር ይዘውት የመጡት ዝርዝር እርሳቸውን ጨምሮ ከ40 በላይ ሰዎችን  ዝርዝር መያዙን ጠቁመዋል።

ከታሰሩትም መካከል መምህራን የሚገኙበት ሲሆን “ይሄን ገበሬ የምታነሳሱት እናንተ ናቹ እንጂ ጥያቄውን በራሱ አይጠይቅም” እያሉ መሆኑንም አመላክተዋል።

በተመሳሳይም ሌላ ነዋሪ “ከመከላከያ ሰራዊት ሸሽተው ለተደራጁ አካላት ብር አዋጡ በማለት ከአንድ ቀበሌ 200 ሺህ ብር መሰብሰብ አለበት በማለት ነዋሪውን እያስጨነቁ መሆኑን” ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ያደራጃቸው አካል ማነው በሚል ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄም “የዞኑ አስተዳዳሪ ነው ያደራጃቸው። ወይ ዘመዶቹ ናቸው አሊያም የሀገሩ ልጆች ናቸው። ወደ አርባ የሚጠጉ ሲሆኑ በፖሊስ እና በሚሊሻ እጅ የማይገኝ መሳሪያ ነው የታጠቁት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንዲሁም “የወረዳው ርቀት የማህበረሰቡን ልማት ተጠቃሚ የማያደርግ ነው ብለን ቅሬታችንን ለዞኑ፣ ለክልሉ እንዲሁም ለአርባ ምንጭ ክልል ምክር ቤት ያቀረብን ቢሆንም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም” ብለዋል።

አክለውም “ህጋዊ አግባብነት በሌለው አካል ሰዎች እየታሰሩ እና እየተንገላቱ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሌላ ግለሰብም በበኩላቸው “ትምህርት ቤቶችንና እና ጤና ጣቢያዎች እንዳይሰሩ ሰራተኞቹን አስወጥተዋቸዋል። የሚመስለው ለምን በእኛ አምባገነን ስርዓት አትገዙም ነው” ብለዋል።

በዞኑ ስር ባሉ ቀበሌዎች ከ85 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ቅሬታችንን ይመለስልን የልማት ተጠቃሚ መሆን የሚያስችለን ዕድል ይፈጠርልን በማለታቸው አሁን ላይ ከፍተኛ ስጋት ዉስጥ መሆናችውን ነው ያስረዱት።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑትን ታረቀኝ በቀለ እንዲሁም የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ሀላፊ የሆኑት ጢሞቲዮስ በቀለ ምላሻቸውን ለማካተት ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ሳይሳካላት ቀርቷል።