
ከ 3 ሰአት በፊት
ቻይናና አሜሪካ በመካከላቸው የነበረውን ውጥረት ለማቀዝቀዝ አቋርጠውት የቆዩትን ወታደራዊ መረጃ ልውውጥ ዳግም ለመቀጠል መስማማታቸውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ገልጸዋል።
ትናንት ረቡዕ ፕሬዝዳንቱና የቻይናው አቻቸው ዢ ጂፒንግ በካሊፎርኒያ ተገናኝተው ተወያይተዋል። ከዚህ ውይይት በኋላ ባይደን “ግልጽና ቀጥተኛ ወደ ሆነው ግንኙነት ተመልሰናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ሁለቱ መሪዎች በአካል ተገናኝተው ከተነጋገሩ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥረዋል።
ባይደን ጨምረውም ሁለቱ መሪዎች አንዳቻው ከአንዳቸው በቀጥታ የሚገናኙበት የግንኙነት መስመር ለማበጀት መስማማታቸውንም ገልጸዋል።
ሁለቱ መሪዎች ካደረጉት ንግግር በኋላ ፕሬዝዳንት ባይደን በሰጡት መግለጫ በመሪዎቹ መካከል ያለው የመረጃ ልውውጥ መሳሳት ችግር ሊያስከትል ይችል ነበር ብለዋል።
“አሁን ግን ሁለቱም ፕሬዝዳንቶች ስልክ ተደዋውለው በቀጥታና በፍጥነት ሊያወሩ ይችላሉ” ሲሉ አክለዋል።
ያኔ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት ናንሲ ፔሎሲ ራስ ገዟን ታይዋንን ሲጎበኙ ነበር ቻይና ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ወታደራዊ መረጃ ልውውጥ ያቋረጠችው።
ባይደን በመካከላችን የማያስማሙ በርካታ ጉዳዮች አሁንም ቢኖርም “ፕሬዝዳንት ዢ ግን ቀጥተኛ ነበሩ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በውይይታችን “አብዛኞቹ ጉዳዮች ገንቢና ፍሬያማ” ነበሩ ካሉ በኋላ ዢን እንደ “አምባገነን” እንደሚቆጥሯቸው ገልጸዋል።
ጆ ባይደን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ከእኛ ፈጽሞ የተለየ ሀገር ከመምራቱ አኳያ አምባገነንን ነው” ሲሉ መልሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን አይነት አስተያየት ሲሰጡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ባለፈው ሰኔ ወር ተመሳሳይ አስተያየት ስለ ዢ ሰጥተው የቻይና ባለስልጣናትን አስቆጥተዋል። ንግግራቸው “ረብየለሽና ኃላፊነት የጎደለው” ነው ሲሉም ተችተዋቸዋል።
- ወደ ሞት ጉዞ: የኢትዮጵያውያን የስደት ጉዞ በጂቡቲ በረሃከ 6 ሰአት በፊት
- ተመድ የጋዛ ጦርነት ‘ሰብዓዊ ፋታ’ እንዲሰጠው ውሳኔ አሳለፈ12 ህዳር 2023
- ከበረቱ ያመለጠ ፈረስ በፈጠረው ግርግር ምክንያት የጭነት አውሮፕላኑ በረራውን አቋረጠከ 5 ሰአት በፊት
አገራቱ ወታደራዊ የመረጃ ልውውጣቸውን ዳግም ለመቀጠል ከመስማማታቸው በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራቱ መካከል የውጥረት ምንጭ የሆኑ ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።
ክነዚህም መካከል አንዱ የእስራኤል ጋዛ ግጭት ይገኝበታል። አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ባይደን የቻይናው ፕሬዝዳንት ያላቸውን ተጽዕኖ ተጠቅመው ኢራን ግጭትን ሊጭር ከሚችል እርምጃ እንድትቆጠብ እንዲያሳስቧት ጠይቀዋል።
የሁለቱ ኃያላን አገራት መሪዎች ‘የአርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ’ ዕድገትን በጋራ ለመገምገም ተስማምተዋል። በሌላ በኩል አንድ የአሜሪካ ባለስልጣን እንደገለጹት መሪዎቹ ዘለግ ያለ ጊዜ ወስደው ስለታይዋን መክረዋል። በዚህ ምክክር ዢ ከታይዋን ጋር በተገናኘ ባነሱት ሃሳብ “በአሜሪካና ቻይና ግንኙነት ትልቁና አደገኛው ጉዳይ” ሲሉ ገልጸውታል።
ከባይደንና ዢ ንግግር በኃላ ቻይና በሀለቱ አገራት መካከል ሲደረግ የነበረው የወታደራዊ መረጃ ልውውጥ “እኩልነትና መከባበርን” መሰረት አድርጎ መመለሱን ገልጻለች።
በሁለቱ መሪዎች ምክክር መግቢያ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዢ “ምድር ለሁለቱም አገራት በቂ ነች፣ የአንዱ ስኬት ለሌላኛው ዕድል ነው. . . የተካረረ ግንኙነት መዘዙ ለሁለቱም አገራት ነው” ብለዋል።
በዚህ የኃያላኑ አገራት መሪዎች ምክክር የተጠበቀውን ያህል መሰረታዊ ውጤት አለመምጣቱ ይገለጻል።
አንድ የአሜሪካ ባለስልጣን ይህንን አስመልክቶ ሲናገሩ የዚህ ምክክር “ትክክለኛ ግብ ፉክክራቸውን ማስጠበቅ፣ ወደ ግጭት የሚያስገቡ ስጋቶችን መከላከል እና የግንኙነት መስመራቸውን ክፍት ማድረግ ነው” ሲል ተናግረዋል።
ባለፈው የካቲት ወር በአሜሪካ ሰማይ ስር ሲንሳፈፍ የተገኘው የቻይና የስለላ ፊኛ በአሜሪካ ተመትቶ ከተጣለ በኋላ የአገራቱ ግንኙነት እጅግ ሻክሮ ነበር።
ይህን ከሆነ ከወራት በኋላ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ ብሊንከን ወደ ቻይን አምርተው ፕሬዝዳንት ዢን አግኝተው አነጋግረዋል።
ከዚህ ጉብኝት በኋላ ብሊንከን በሰጡት አስተያየት በአገራቱ መካከል የማያስማሙ ጉዳዮች ቢኖሩም የተሻለ የመረጃ ልውውጥ እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ ብለው ነበር።