ጄኔራል ጄንኪንስ [ወታደራዊ መለዮ የለበሱት]
የምስሉ መግለጫ,ጄኔራል ግዊን ጄንኪንስ [ወታደራዊ መለዮ የለበሱት]

ከ 2 ሰአት በፊት

የዩናይትድ ኪንግደም አንድ ከፍተኛ ጄኔራል በአውሮፓውያኑ 2011 የብሪታኒያ አየር ኃይል ወታደሮች አፍጋኒስታን ውስጥ እጃቸው የተጠፈረ ሰዎችን መግደላቸውን የሚያሳይ መረጃ ደብቀዋል ተባሉ።

ቢቢሲ ፓኖራማ እንዳጣራው በአሁኑ ወቅት የብሪታኒያ ጦር ኃይል ሁለተኛ ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ጄኔራል ግዊን ጄንኪንስ አየር ኃይሉ ሕጋዊ ያልሆነ ግድያ መፈፀሙን የተመለከተ መረጃ ደርሷቸዋል።

ነገር ግን መረጃውን ለወታደራዊ ፖሊስ አሳልፈው እንደመስጠት የሚስጥር ቁልፍ ያለው ሳንዱቅ ውስጥ አስቀምጠውታል።

ግለሰቡ መረጃውን ለወታደራዊው ፖሊስ አሳልፈው አለመስጠታቸው በአንድ ወቅት ፍርድ ቤት ውስጥ ቢነሳባቸውም በመከላከያ ሚኒስቴር ጥያቄ መሠረት ስማቸው ለሕዝቡ ይፋ እንዳይሆን ተደርጓል።

ጄኔራል ጄንኪንስ በወቅቱ የልዩ ኃይል ኮሎኔል ነበሩ። ሚያዚያ 2011 የደረሳቸውን መረጃ ጥብቅ ሚስጥር የሚቀመጥበት አስቀምጠዋል፤ ነገር ግን ጉዳዩን በወቅቱ የልዩ ኃይሉ ኃላፊ ለነበሩት ጄኔራል ጆናታን ፔጅ መግለጫ ሰጥተዋል።

በብሪታኒያ ሕግ መሠረት የጦር አዛዥ የሆኑ ሰዎች የጦር ወንጀል እንደተፈፀመ የሚያሳይ መረጃ ከደረሳቸው ለወታደራዊ ፖሊስ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው።

ነገር ግን ይህ የምስርክርነት ቃል ያዘለ ዶሴ ባለሚስጥር ቁልፍ ሳንዱቅ ውስጥ ለአራት ዓመታት ተቆልፎበት ቆይቷል።

ጄኔራል ጄንኪንስ በወታደራዊ እርከን አድገው እዚህ እስኪደርሱ ድረስ ስለመረጃው የሚያውቁት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው።

በመሐሉ አንድ መረጃ አሾላኪ ግለሰብ ጉዳዩን ለንጉሣዊው ወታደራዊ ፖሊስ አሳውቀዋል።

ጄኔራል ኬንኪንስ መረጃውን በዶሴ አሽገው በደበቁ በተመሳሳይ ወር በአፍጋኒስታን የዩናይትድ ኪንግደም ልዩ ኃይል ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።

ከዚያ የዩናይትድ ኪንግደም ልዩ ኃይል ዳይሬክተር፤ ቀጥሎ ደግሞ የመከላከያ ስታፍ ምክትል አለቃ ሆነዋል። ይህ በሃገሪቱ ሁለተኛው ትልቁ እርከን በአንድ ጊዜ ከባለ ሁለት ኮከብ ወደ ባለአራት ኮከብ ጄኔራል እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

የብሪታኒያ አየር ኃይል አፍጋኒስታን ውስጥ ሕጋዊ ያልሆነ ግድያ ፈፅሟል ተብሎ ጉዳዩ ለሕዝብ ይፋ ሆኖ በንጉሣዊው የፍትሕ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።

ቢቢሲ እና ሌሎችም ስለጉዳዩ ዘገባ ከሠሩ በኋላ ነው ፍርድ ቤቱ ለሁሉም ክፍት የሆነ ችሎት የከፈተው።

ባለፈው ዓመት ፓኖራማ ይፋ እንዳደረገው በ2011 የአየር ኃይል አንድ ቡድን ለስድስት ወራት ወደ አፍጋኒስታን ባቀኑበት ወቅት 54 ሰዎችን ገድለዋል ሲል ዘግቦ ነበር።

በተመሳሳይ ወቅት አንድ ጄኔራል ጄንኪንስ በሚመረቱት ዕዝ ሥር የነበሩ የአየር ኃይል አባል አንድ ቡድን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ያልታጠቁ ሰዎችን ገድለዋል ሲሉ ለጄኔራል ተናዘዋል።

ጄኔራል ጄንኪንስ እና ንጉሥ ቻርልስ
የምስሉ መግለጫ,ጄኔራል ጄንኪንስ እና ንጉሥ ቻርልስ ባለፈው ዓመት በንግሥት ኤልዛቤት ሞት ወቅት ተገናኝተው ነበር

ጄኔራሉ ወታደሩን ኑዛዜውን በፅሑፍ እንዲያመጡ አዘዋቸዋል። መኮንኑ በፅሑፋቸው የልዩ አየር ኃይል አባላት በአፍጋኒስታን ፍተሻ ሲያደርጉ ያልታጠቁ ሰዎችን ሳይመርጡ ገድለዋል መባሉን መስማታቸውን አስፍረዋል።

“በአንድ ክስተት አንድ ግለሰብ ጭንቅላት በጥይት ሲመታ ጭንቅላቱን በትራስ በመሸፈን ነው” ሲሉ ወታደሩ በፅሑፋቸው አስረድተዋል።

ጄኔራሉ ይህ መረጃ ከደረሳቸው በኋላ ጄነራል ጄንኪንስ ለወታደሩ አለቃና የልዩ ኃይሉ ዳይሬክተር ለነበሬት ጄኔራል ጆናታን ፔጅ ተናግረዋል።

ጄኔራል ጄንኪንስ ለጄኔራል ፔጅ በላኩት ደብዳቤ “ጠበቅ ያለ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል” ማለታቸው ተመልክቷል።

ቢቢሲ እንደተረዳው አንድ የልዩ አየር ኃይል አባል አንድ ሳምንት የወሰደ ምርመራ አድርጓል። የፍርድ ቤት ወረቀቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ የመርማሪው ዘገባ የተፈረመው ወንጀሉን ፈፅመዋል ተብሎ በተጠረጠረው ቡድን አዛዥ መኮንን ነው።

ጄኔራል ጄንኪንስ በአፍጋኒስታን የዩኬ ልዩ ኃይል አለቃ ሆነው ለዓመታት ከሠሩ በኋላ ወደ ዩኬ ተመልሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ወታደራዊ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።

ንጉሣዊው ወታደራዊ ፖሊስ ጉዳዩን መመርመር ጀምሮ ማንም ክስ ሳይመሰረትበት ምርመራ መጠናቀቁ የተወሰኑ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አስቆጥቷል።

የወታራዊው ፖሊስ አባላት ለቢቢሲ እንደገለጡት ጥብቅ ምርመራ እንዲያደርጉ አልተፈቀደላቸውም፤ ቁልፍ የሚባሉ ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ ማድረግና ወሳኝ ማስረጃዎችን ማግኘት አልቻሉም።

ቢቢሲ ከጄኔራል ጄንኪንስም ሆነ ከጄኔራል ፔጅ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ውጤት አልባ ሆኗል።