
15 ህዳር 2023
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በሞባይል መሸጫ ሱቅ ውስጥ ተቀጣሪ የነበረችው የ21 ዓመት ወጣት በሞባይል ባንኪንግ አማካይነት በሁለት ግለሶች ከተጭበረበረች በኋላ እራሷን አጠፋች።
መቅደስ መኮንን የተባለችው ወጣት አራት ሞባይሎችን በ69 ሺህ ብር ለመሸጥ ከተስማማች በኋላ ገዢ መስለው የቀረቡት ሁለት ግለሰቦች ክፍያውን በሞባይል ባንኪንግ መፈጸማቸውን የሚያሳይ ሐሰተኛ አጭር የጽሑፍ መልዕክት በማሳየት እንዳጭበረበሯት ፖሊስ ለቢቢሲ ገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ የወንጀል ድርጊቱ ሕጋዊውን የሞባይል የገንዘብ ዝውውር መንገድ በማስመሰለል መፈጸሙን አስረድተዋል።
“ሁለቱ ግለሰቦች ገንዘቡን የሚያስተላልፉበትን የሂሳብ ቁጥር ጠይቀው ከተነገራቸው በኋላ በኋላ ገንዘቡን ወደሌላ የሂሳብ ቁጥር በማዘዋወር የተላከላቸውን ከባንክ ዝውውሩ ተሳክቷል የሚለውን ጽሑፍ በማሳየት ነው ማጭበርበሩን የፈጸሙት።”
ወጣቷም የባንክ አጭር መልዕክት የሚደርስበት ስልኳ እርሷ እጅ እንዳልነበረ እና ግለሰቦቹ ገንዘቡን እንዳስተላለፉ በማመን አራቱን የሞባይል ስልኮች ለገዢዎቹ ሰጥታ ግብይቱን በመፈጸሟ ነው ወንጀሉ ዝርፊያው ያጋጠመው።
ከዚያም በኋላ ገንዘቡ ገቢ መደረጉን ለማረጋገጥ ወደ ባንክ ከሄደች በኋላ ነው ገንዘቡ ወደተጠቀሰው ቁጥር ገቢ እንዳልሆነ ሲነገራት ነው ወጣቷ መጭበርበሯን የተረዳችው ሲሉ ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ተናግረዋል።
በዚህም “የተቀጠረችበትን ሥራ እምነት እንዳጎደለች ስለተሰማት። ከጭንቀቷ የተነሳ እራሷን ለማጥፋት መድኃኒት” መጠጣቷን ፖሊስ ገልጿል።
የ21 ዓመቷ ወጣት ድርጊት እጅግ ያስደነገጣቸው የቤተሰብ አባላት እና ጎረቤቶች ለሕክምና በአካባቢው ወደሚገኝ አጣጥ ሆስፒታል ቢወስዷትም የደረሰባት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ለሕልፈት ተዳርጋለች።
- ‘ሆስፒታሎች የጦር ሜዳዎች አይደሉም’ የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን12 ህዳር 2023
- የሱዳኑ ጄኔራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን ጉብኝት በአዲስ አበባ15 ህዳር 2023
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ተስፋ15 ህዳር 2023
ፖሊስ እስካሁን ድረስ ሁለቱን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ባያውልም ግለሰቦቹን ለመያዝ ብርቱ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ምክትል ኮማንደሩ ጨምረው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሞባይል ባንኪንግ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ተገልጋዮችን የማጭበረበር የወንጀል ድርጊቶች ቁጥርም አብሮ መጨሩን የፖሊስ አባሉ ይገልጻሉ።
የፖሊስ አባሉ እንደሚሉት በሞባይል ባንኪንግ ሰዎች እየተጭበረበሩ ያሉት የቴክኖሎጂውን አጠቃቀም አለማወቃቸው አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል።
“ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች እስከ 10 ሺህ ብር በኤቲኤም ማሽን እንዲያወጡ፤ ገንዘብ ለማዘዋወር ደግሞ ሞባይል ባንኪንግ እንዲጠቀሙ ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ለሕብረተሰቡ አጠቃቀሙን በተመለከተ በቂ ትምህርት አልተሰጠም” በማለት የተጠቃሚዎች ግንዛቤ መጭበርበርን ለማስቀረት እንደሚጠቅም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ተጠቃሚዎች ገንዘብ ሲተላለፍላቸው በራሳቸው መንገድ የተባለው የገንዘብ መጠን ገቢ መደረጉን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ሲሉ የፖሊስ አባሉ መክረዋል።
የንግድ ተቋማት ባለቤቶችም ገንዘብ ሲተላልፍ መልዕክት የሚገባበት ሞባይል ቁጥር ሠራተኞች ጋር ማኖር፣ አልያም ደግሞ እያንዳንዱ ግብይ ከተፈጸመ በኋላ ገንዘብ መግባቱን ስልክ በመደወል ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ።