
ከ 6 ሰአት በፊት
ኢትዮጵያውያንን እና ኤርትራውያን ወደ ጂቡቲ የሚያደርጉት የበረሃ ጉዞን ለመመልከት አደገኛ የተባለውን የጂቡቲ-ኦቦክ የጉዞ መስመር ላይ ደርሰናል።
ኦቦክ ትንሽ የባሕር ዳርቻ ከተማ ናት።
በባሕር ዳርቻዋ ላይ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የሚታዩት ከነዋሪዎቿ ይልቅ ስደተኞች ናቸው።
ከአገሪቱ ይፋዊ የሥራ ቋንቋ ፈረንሳይኛ እና አረብኛ ይልቅ የባሕር ዳርቻው መግባቢያ ኦሮምኛ ይመስላል።
በከተማዋ የሚገኙ ቤቶች ካስጠለሏቸው ባልተናነሰ የባሕር ዳርቻዎቹ ላይ አሸዋ ተንተርሰው፣ ካርቶን ለብሰው የሚያድሩ ስደተኞች ቁጥር ቀላል አይደለም።
እነዚህ በኦቦክ የቀይ ባሕር ዳርቻ የሚውሉ ስደተኞች የሚበሉት ባለመኖሩ ከትንሿ ከተማ ነዋሪዎች ደጃፍ እየቆረቆሩ ምጽዋት ይጠይቃሉ።
በዚህችም ከተማ ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 20ዎቹ አጋማሽ የሚቆጠሩ ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ ከተሞች የመጡ ወጣቶችን አግኝተናል።
ይህ ግን የስደት መንገድ እስኪመቻች የሚቆይበት ከተማ እንጂ ዘላቂ መሸሸጊያ አይደለም።
የስደት ጉዞ ሲሟላ፣ ደላላ አሁን በረሃውን መሻገር ይቻላል ሲል፣ በአንድ መኪና ተጭኖ ወደ ጌሄሬ መሄድ ያስፈልጋል።
አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ቢፈልጉም ለመመለስ የሚያስችላቸው ነገር የላቸውም።
- በቀለጠ ተኩስ መሀል ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩት ስደተኞች11 ህዳር 2023
- የዛሬ 10 ዓመት በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የደረሰው የላምፔዱዛው እልቂት3 ጥቅምት 2023
- የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን መግደላቸውን ሪፖርት ጠቆመ21 ነሐሴ 2023
ጫማው የከበደው ስደተኛ በጅቡቲ ጌሄሬ በረሃ

ጌሄሬ ከኦቦክ አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ትርቃለች።
ይህች ስፍራ ደላሎች ወደ የመን መሻገር የወሰኑ ስደተኞችን የሚያሰባስቡባት በረሃ ናት።
በእርግጥ ደላሎቹ ስደተኞቹን የሚያሰባስቡባቸው ሦስት ስፍራዎች እንዳሉ ሰምተናል።
ከኦቦክ አንድ ሰዓት ተኩል በመኪና ተጉዘን፣ 40 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደ ምትገኘው ጌሄሬ በመኪና ስንፈጥን መንገዳችን ላይ የወደቀ ሸበጥ ተመለከትን።
መንገድ ያዛለው ስደተኛ፣ ጫማው የከበደው መንገደኛ የጣለው ሸበጥ ብዙ ይናገራል።
ጫማው ላይ ‘ትግራይ ዓደይ’ [ትግራይ አገሬ] የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል።
የዚህ በመንገድ የዛለ ስደተኛ መነሻ ትግራይ ሳይሆን አይቀርም። መድረሻውን ግን ማንም አያውቅም።
በዚህ አሸዋው በሚፋጅበት በረሃ፣ ሀሩሩ በሚያነድ የስደተኞች መንገድ ላይ ሁለት እግር ጫማውን ጥሎ ወዴት ሄዶ ይሆን?
ከጂቡቲ የድንበር ጠባቂዎች ዕይታ እየተሹለከለኩ በባዶ እግር ጉዞ ምን ያህል ርቀትስ ያስጉዛል?
ይህ አጋጣሚ ለኦቦክ አስተዳዳሪ ሙሳ አደን አዲስ አይደለም። በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የተጫሙት ጫማ አብሯቸው በረሃውን መዝለቅ አቅቶት ባዶ እግራቸውን በጋለ አሸዋ ላይ ሲጓዙ ተመልክተዋል።
በዚህም ዳፋ የተነሳ እግራቸው አብጦ በየበረሃው የቀሩ፣ የቻሉም ወደ ከተማዋ የሕክምና ተቋም መጥተው መታከማቸውን ያስታውሳሉ።
የቢቢሲ ጋዘጠኞችን የያዘው መኪና፣ ወደ ጌሄሬ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መኪናን በቅርብ ርቀት ተከትሎ ይከንፋል።
መኪናችን የተነሳው ከትንሿ የጂቡቲ ከተማ ኦቦክ ነው።
ኦቦክ ጂቡቲያውያን ከተማዋን የሚጠሩበት ስያሜ ቢሆንም ኢትዮጵያውያኑ ግን ሀዩ ማለትን ይመርጣሉ። ለምን አንደሆን እነርሱም አያውቁም።
ከኢትዮጵያ ድንበር ታጁራ፣ ከታጁራ ሀዩ ምቹ በሆነ አስፓልት ላይ ነው ስደተኞቹ የሚጓዙት።
ደላሎች ተራራውን አልያም የበረሃውን መንገድ ካልመረጡ በስተቀር የኢትዮጵያውያን ስደተኞች የየመን ጉዟቸውን የሚመርጡት በዚህ ቅቤ በሆነ አስፓልት ላይ በሚከንፍ የአይሱዚ ጀርባ ላይ ተጭነው ነው።
አይሱዚው ሠላሳም፣ አርባም ሰው በአንድ ጊዜ ያሳፍራል።
ሁሉም ለእግራቸው መጫሚያ ነጠላ ጫማ፣ አልያም ኮንጎ ከማድረጋቸው ውጪ በረሃውን የሚረዳቸው አለባበስ አይታይባቸውም።
ሁሉም ከኢትዮጵያ የገጠር መንደር እንደወጡ በአፋር በኩል አድርገው ወደ ጂቡቲ ማቋረጣቸውን ይናገራሉ።
የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የመስክ ቅኝት ቡድን ከባሕር ዳርቻው አካባቢ ወደ የመን ለመሻገር ከተሰባሰቡ ስደተኞች መካከል የተወሰኑት መታመማቸው መረጃ ስለደረሰው ነው ወደዚያው የሚያቀናው።
የድርጅቱ የሕክምና ባለሙያ ዶ/ር የሱፍ ሙሳ እንዲህ ዓይነት የቅኝት ጉዞ በተደጋጋሚ እንደሚያደርጉ በጉዟችን መነሻ ላይ ነግረውናል።
ደላሎች ስደተኞችን በዚህ የጂቡቲ በረሃ የተለያየ ስፍራዎች በማሰባሰብ ወደ የመን ያሸጋግራሉ።

በየስፍራው ተበትነው የሚታዩት ስደተኞች
የአይኦኤም የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ጌሄሬ ሲደርስ ቁጥራቸው ወደ 70 የሚጠጋ ስደተኞች በየዛፉ ጥላ ስር እዚህም እዚያም ተኝተዋል።
በአንድ የዛፍ ጥላ ስር የታመመ ወጣትን ከብበው የሚታዩ በርካታ ወንዶች ወዳሉበት ተጠጋን።
ከቡታጅራ፣ ከስልጤ፣ ከቆቦ፣ ከትግራይ፣ ከኦሮምያ የመጡ ስደተኞችን በዚህ ከተራራ ስር ተዘርግቶ በሚገኝ ሜዳ አገኘናቸው።
ከተራራው ስር አነስተኛ ቤት እና የአይኦኤም ውሃ ታንከር ይታያል።
ስደተኞች በተኙበት አቅራቢያ አገልግሎት የሰጠ ብረት ድስት ወድቋል።
ከዚያ ውጪ ዓይን እስከ ቻለው ቢያማትሩ ጭው ያለ በረሃ ነው።
በየዛፉ ጥላ ስር የተሰባሰቡት ስደተኞች ከየአካባቢያቸው ልጆች ጋር መሆኑን ይመርጣሉ።
ከወጣት ሴቶች እና ወንዶቹ መካከል ታዳጊ ልጆችም አሉ።
ዕድሜያቸው 15 እና 16 የሆናቸው ከስልጤ እና አድዋ-ትግራይ የመጡ ታዳጊዎችን የቢቢሲ የጋዜጠኞች ቡድን ተመልክቷል።
ጌሄሬ ስንደርስ ታምመው ያገኘናቸው ስደተኞች ቁጥር አራት ነበሩ።
ስደተኞቹ ምግብ የቀመሱት ከኦቦክ ከመነሳታቸው በፊት መሆኑን ይናገራሉ።
ከተኙበት አጠገብ ፌስታል ቢታይም የሚቀመስ ምግብም ሆነ ጉሮሯቸውን የሚያርስ ውሃ አልያዙም።
ከራያ ቆቦ የመጣው እና እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ እንደተማረ የሚናገረው ወጣት ከባጃጅ ሹፌርነት ይልቅ ሳዑዲ ሄጄ ሠርቼ ያልፍልኛል ብሎ ለእናት አባቱ ደጃፍ ጀርባውን ሰጥቶ ነው እዚያ የደረሰው።
ስለዚህ የስደት መስመር ማን ነገረህ ሲባል “ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ብዙ ስደተኛ ሞልቶ የለም እንዴ? በስደት የቀናቸው በደህና አሉ፤ በዚያው የቀሩም አሉ። እነርሱን እነርሱን ስናይ እኛም እንሞክረው ብለን ወጥተናል” ይላል።
እንደ እርሱ ከዋጃ አካባቢ የመጣው ሌላው ቢቢሲ ያነጋገረው ወጣትም፣ ከቤተሰቦቻቸው ጎጆ ከወጡ ሁለት ሳምንት እንዳለፋቸው ይናገራል።
ለሁለት ሳምንት ያህል ጎናቸው የረባ መኝታ፣ በቂ ምግብ እና ውሃ ሳያገኙ ጌሄሬ ደርሰዋል።
“እዚህ በየዛፉ ጥላ ስር ተረፍርፎ የምታየው ሁሉ ያደከመው ረሃብ እና ውሃ ጥም ነው” ሲል ያክላል።
በአንድ መኪና እስከ 50 የሚደርሱ ሰዎች ተጭነው መምጣታቸውን እና ከአንድ በላይ መኪና ሌሊቱን ስደተኞችን አምጥቶ እዚህ ማድረሱን ይገልጻሉ።
ምንም እንኳ ሌሊቱን ተጉዘው እዚህ መድረሳቸውን ቢናገሩም፣ እኛ በስፍራው ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ እስክንደርስ ድረስ ምግብም ሆነ ውሃ አልቀመሱም።
ይህ እስከ መቼ አንደሚቀጥል እነርሱም አያውቁም።
“ትናንት የበላን ነን። ለሊቱን ስንጓዝ አደርን። እስካሁን ምንም እህል በአፋችን አልዞረም፤ እንደምታየው አብዛኛውን በየዛፉ ስር አስተኝቶት የሚታየው ረሃብ ነው” ይላል ከዋጃ እንደመጣ የተናገረው ወጣት።
ከራያ ቆቦ የመጡት እና ከሁለት ሳምንት በፊት መነሳታቸውን የሚናገረው ወጣት ከኢትዮጵያ ሳይወጡ ሃራ እና ሎጊያ ላይ ተይዘው የቀሩ ጓደኞች አሏቸው።
ከቆቦ አካባቢ የመጡ እና ቁጥራቸው ከ13 በላይ የሆኑት ወጣቶች፣ አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው።
ከቀያቸው ከመነሳታቸው በፊት ድንበር ለመሻገር፣ ባሕር ለማቋረጥ መመካከራቸውን ይናገራሉ።
ከትግራይ አድዋ እንደመጡ የሚናገሩት እና አነስተኛ ዛፍ ጥላ ስር ተሰባበስበው ያገኘናቸው ሌሎች ወጣቶች ከአድዋ ከመውጣታቸው በፊት እንዲሁ መመካከራቸውን ነግረውናል።
ከእነዚህ ወጣቶች መካከል የተወሰኑት ሴቶቹ ፀጉራቸውን እርስ በእርስ ሲጎናጎኑ፣ ወንዶቹ ደግሞ የወደቀ ግንድ ተደግፈው ያንጎላጅጃሉ።
የእኛን መምጣት የተረዳች አንዲት ታዳጊ የራስ ምታት ኪኒን ይዘን እንደሆን ስትጠይቅ፣ ሌላኛዋ ደግሞ የሚበላ በእጃችን መኖሩን እና አለመኖሩን አረጋገጠች።
ከእነዚህ ሦስት ወንድ እና ስድስት ሴቶች መካከል፣ ሁለቱ ሴቶች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች መሆኑን ቢቢሲ ጠይቆ መረዳት ችሏል።
በአካባቢው ላይ ተበትነው የሚታዩት ሁሉም ስደተኞች በረሃብ እና በውሃ ጥም እንዲሁም ያለ በቂ መኝታ ሁለት ሳምንት ማሳለፋቸውን ይናገራሉ።
እነዚህ ወጣቶች ቤተሰቦቻቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ካወሩ 10 ቀን አልፏቸዋል።
የኢትዮጵያን ድንበር ካለፉ በኋላ ስልክ ስለሌላቸው መደወል አልቻሉም።
በየዛፉ ጥላ ስር የተኙት ፍልሰተኞች ሁሉ የተገናኙት ኦቦክ ነው።

ከኢትዮጵያ ሲነሱ በስልክ ያነጋገሩት ደላላ ድንበር አይሻገርም። ድንበር ተሻግረው ለሚገኙ ሌሎች በስልክ አሳልፎ ይሰጣቸዋል።
ኦቦክን አልፈው ጭው ባለው ጌሄሬ በረሃ ላይ ሲደርሱም ደላላው በአቅራቢያቸው የለም።
በራባችሁ ሰዓት ምግብ ካላቀረበ፣ ውሃ ካላቀበላችሁ፣ ለታሙት መድኃኒት ካልሰጠ ታድያ የደላላው እርዳታ ምንድን ነው? የእኛ ጥያቄ ነበር።
አንዱ ከቆቦ የመጣ ወጣት ቀልጠፍ ብሎ “ማረፊያ ቦታ ምግብ ያመጡልናል። ባሕር ላይ በማሻገር ይተባበሩናል። ርቀት ያለውን መንገድ ደግሞ በመኪና ይጭኑናል” ሲል ደላሎቹ የሚያደርጉትን ያስረዳል።
ሁሉም መዳረሻቸው ሳዑዲ አረቢያ እንደሆነ ይናገራሉ። ከደላሎች ጋር የሚገናኙት በስልክ አማካይነት ነው።
ኦቦክ ላይ ሁለት ቀን ያህል አድረዋል። እንደእነርሱ አባባል በየመንገዱ አንድም ሁለትም ቀን ማደር የተለመደ ነው።
የጂቡቲን ድንበር መቼ ነው የምታሻገሩት ሲባሉ “አላወቅንም እርሱን፤ ከእዚህ ሊያሳድሩንም ሊያውሉንም ይችላሉ” የሁሉም ምላሽ ነው።
“መቼ እንደምንሻገር አልነገሩንም፤ እግዚአብሔርን አምነን ቁጭ ብለናል” ያለችው ደግሞ ከአድዋ የመጣችው ወጣት ናት።
ቢቢሲ በስፍራው ያገኛቸውን ስደተኞች ጠይቆ መረዳት አንደቻለው የጂቡቲን ድንበር ተሻግሮ የመን ለመግባት እስከ 50 ሺህ ብር ለመክፈል የተስማሙ አሉ።
40 እና 50ሺህ ብር ብዙ አይደለም? ማን ይከፍለዋል?
ገንዘቡ የወላጆቻቸው በሬዎች ተሽጠው፣ አልያም ባሕር ማዶ እህት ወይም ወንድም ያለው እነርሱ እንዲከፍሉ በማድረግ እንደሚከፍል ያስረዳሉ።
ከትግራይ የመጡት ወጣቶች እስካሁን ድረስ ለትራንስፖርት እስከ 10 ሺህ ብር መክፈላቸውን፣ ድንበር ከተሻገሩ በኋላ ደግሞ ቀሪውን እንደሚከፍሉ ተናግረዋል።
ሴቶች የሚጠየቁት ብዙ ብር መሆኑን እና ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አብዛኛውን ጊዜ በእግራቸው ለመጓዝ ስለሚከብዳቸው በመኪና ስለሚሻገሩ መሆኑን እና ወንዶች ግን የተወሰነውን መንገድ በእግር በመሄድ ወጪያቸውን ለመቀነስ እንደሚሞክሩ ያስረዳሉ።

በረሃ እና ባሕር ላይ እንደወጡ የሚቀሩት ስደተኞች
በየዓመቱ ወደ የመን እና ሳዑዲ አረቢያ መሻገር የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የጅቡቲ ኦቦክ መንገድን ይመርጡታል።
ይህች የባሕር ዳርቻ ከተማ የሆነችው ኦቦክ ስደተኞች አደገኛ የሆነውን የባሕር ላይ ጉዞ ለመጀመር ለአጭር ጊዜ የሚቆዩባት ከተማ ነች።
በ2022 (እአአ) ብቻ ወደ ጅቡቲ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት በእጥፍ የጨመረ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚሁ ዓመት ብቻ በሚጓጓዙበት ትራስፖርት ላይ በሕመም እንዲሁም በአስከፊ የአየር ጠባይ፣ ባሕር ላይ በመስመጥ እና በግጭት የተነሳ 89 ስደተኞች መሞታቸው አልያም መጥፋታቸው ተመዝግቧል።
ከዚህ የሚልቀው ሞት እና መሰወር ደግሞ ሳይመዘገብ እንደቀረ ይታመናል።
በጌሄሬ የአይኦኤም የሕክምና ቡድንን የመሩት ዶ/ር የሱፍ እኤአ ከሐምሌ እስከ መስከረም 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 54 ስደተኞች ጅቡቲ ውስጥ መሞታቸውን መመዝገባቸውን ነግረውናል።
23 የሚሆኑት ደግሞ የገቡበት ሊታወቅ አልቻለም።
በዚሁ ጊዜ ብቻ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ለ2930 ፍልሰተኞች የምግብ እና የመጠጥ ውሃ ድጋፍ ሲያደርግ፣ ለ267 ደግሞ በመንገዳቸው ላይ ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት የሕክምና ድጋፍ አድርጓል።
ከታኅሣሥ እስከ ሐምሌ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ የጂቡቲ ጤና ሚኒስቴር በአገሪቱ 241 ስደተኞች መሞታቸውን፣ 258 ደግሞ በአሊ ሳቤህ፣ በአርታ፣ በዲኪል፣ ኦቦክ እና ታጁራ የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረጉንም መረጃዎች ያሳያሉ።
የቢቢሲ የጋዜጠኞች ቡድን ጌሄሬ በደረሰበት ወቅት የዓለም አቀፉ የስደተኞች ቡድን አራት በጠና የታመሙ ስደተኞችን ሕክምና እርዳታ ሲሰጥ ተመልክቷል።
ሦስቱ የተሻለ ሕክምና ስለሚያስፈልጋቸው ወደ ኦቦክ ለመሄድ ተስማምተዋል “ዕድለኞች ነን ወደ ኦቦክ ለመሄድ መስማማታቸው” ይላሉ ዶ/ር የሱፍ ሙሳ።
አብዛኛውን ጊዜ ድንበር ላይ የደረሱ ስደተኞች ወደ ኋላ ለመመለስ ፈቃደኛ አይሆኑም።
ደላሎቹ ከጂቡቲ ወደ የመን የሚያሻግሯቸውን ብቻ ሳይሆን ከየመን ወደ ጂቡቲ የሚመለሱትንም በእዚሁ ጌሄሬ ላይ ነው የሚያስቀምጧቸው።
በቅርብ የምትገኘው ደግሞ ኦቦክ ናት – በአገር ልጅ አጠራር ሀዩ።
ችግሩ ኦቦክ ቅርብ መሆኗን ብቻ ደላሎቹ ይናገራሉ እንጂ ተመላሾቹን ከተማዋ ድረስ ይዘው አይመጡም።
ስለዚህ በበረሃ ጉዞ የደከሙ ስደተኞች በእግራቸው የጂቡቲን ደረቅ በረሃ ማቋረጥ ይጠበቅባቸዋል።
በዚያ በረሃ ያለ አንዳች መንገድ አመላካች ለሚባዝኑ ስደተኞች አቅጣጫ ለመጠቆም የሚያግዝ መፍትሄ ድርጅቱ አዘጋጅቷል።
አይኦኤም ይህንን የስደተኞች ጉዞ ለማገዝ የውሃ ታንከሮች በየመንገዱ ላይ ሰቅሏል።
እነዚህ የውሃ ታንከሮችም ለተጠማ ጉሮሮ የሚያርስ ውሃ ብቻ ሳይሆን፣ ኦቦክ በየት አቅጣጫ እንደሆነች እና ምን ያህል ኪሎሜትር እንደሚቀራቸው የሚጠቁም መረጃን ያሳያል።
‘ከከተማዋ ነዋሪዎች ስደተኞቹ ሊበልጡ ነው’

የኦቦክ ከተማ አስተዳደሪ የሆኑት ሙሳ አደን ሚጌኔ፣ ወደዚህች ከተማ ከመምጣታቸው በፊት በአሊሳቤህ በአስተዳዳሪነት ቆይተዋል።
በእነዚህ የጅቡቲ ከተሞች በአስተዳዳሪነትም ሆነ በነዋሪነት በቆዩባቸው ዓመታት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየበረሃው በውሃ ጥም እና በረሃብ ሲሞቱ መመልከታቸውን ይናገራሉ።
ኦቦክ ከ23ሺህ ብዙም የማይዘል ነዋሪ እንዳላት አስተዳዳሪው ጠቅሰዋል።
በየወሩ ወደ ከተማዋ ድንበር አቋርጦ ለመሻገር በማሰብ የሚመጣው ስደተኛ ቁጥር ግን ከ10ሺህ በላይ እንደሚደርስ ያላቸውን ግምት ይናገራሉ።
“ከአገሪቱ ነዋሪ ጋር እኩል ሊሆኑ ምንም አልቀራቸውም. . . በኦቦክ ከነዋሪው በላይ የሚሆኑት ስደተኞች ናቸው” የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ በየቤቱ በልመና ከመሰማራታቸው ባሻገር አንዳንድ ጊዜ ግጭት ስለሚከሰት የከተማዋ ፀጥታ እና ደኅንነት አስከመታወክ ደርሷል ይላሉ።
ይህ ግን የአስተዳዳሪው ብቻ ሳይሆን የነዋሪዎቹም ስሞታ ሆኖ አግኝተነዋል።
ስደተኞች ለመንገድ ምቹ የሆነ ጫማ ስለማያደርጉ በየበረሃው ጫማቸውን ጥለው ባዶ እግራቸውን ሲጓዙ እግራቸው አብጦ፣ በውሃ ጥም ደክመው፣ በተለያዩ በሽታዎች ተጠቅተው በየቦታው ይገኛሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ በሽታዎች የሚታመሙ ፍልሰተኞችን ወደ ከተማዋ ሕክምና ተቋም በማስገባት እንደሚያክሙም ያስረዳሉ።
ቢቢሲ በኦቦክ እንዲሁም በጌሄሬ በተዘዋወረበት ወቅት ፍልሰተኞች በኮሌራ ታመው የሕክምና ድጋፍ ሲያገኙ ተመልክቷል።
በከተማዋ ወደ የመን ለመሻገር የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት አስተዳዳሪው፣ ከየመን የሚመለሱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም መኖራቸውን ያነሳሉ።
በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዲያስፖራ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ግዛቸው ቡሹ በ2015 ዓ.ም. ብቻ 1700 የሚሆኑ ስደተኞችን ከአይኦኤም ጋር በመተባበር ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ነግረውናል።

ሂያጅ እና ተመላሽ የሚተላለፉበት መንገድ
ቢቢሲ የኦቦክ ቆይታውን አጠናቅቆ ስደተኞቹን ባሉበት ትቶ ወደ ታጁራ መንቀሳቀስ ጀምሯል።
በመንገዳችን ላይ በመኪና ተጭነው ወደ ኦቦክ የሚጓዙ ስደተኞችን በአንድ በኩል በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ወደ ታጁራ በእግራቸው የሚጓዙ ስደተኞችን ተመልክተናል።
ወደ ታጁራ የሚሄዱ እና የተጎሳቆሉ ውሃ የሚለምኑ ስድስት ወጣቶችን ስናይ መኪናችን አቆምን።
አደም መሐመድ እና ጓደኞቹ የጂቡቲን ድንበር አቋርጠው ወደ የመን ተሻግረው ነበር።
ሳዑዲ ለመሻገር መሞከራቸውን እና ተይዘው እስር ቤት ስለሞላ በሚል ወደ የመን እንደተላኩ ይናገራሉ።
“ድንበር ላይ በርካታ ሬሳ ተራምደን ተሻግረናል” ይላል አወል ሰዒድ አህመድ፣ እርሱም እጁን በፍንጣሪ እንደተመታ በማሳየት።
የመን ላይ በልመና ስድስት ወር የቆዩት እነዚህ ወጣቶች፣ ቤተሰቦቻቸው ከብቶቻቸውን እና መሬታቸውን ሸጠው በባሕር ለመሻገር የሚያስችል ገንዘብ ስለላኩላቸው ጂቡቲ ድንበር ላይ መድረሳቸውን ይናገራሉ።
አደም እና አወል የመን ላይ በርካታ ሰዎች መመለሻ አጥተው መቀመጣቸውን ይናገራሉ።
የየመን ታጣቂዎችን አልፎ ሳዑዲ መግባት አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹት ስደተኞች፣ ከየመን ለመውጣት በርካቶች ቢፈልጉም በተለያየ ምክንያት አልቻሉም ይላሉ።
የጂቡቲ መንገድ ስደተኛ መቀበል እና መሸኘት ልማዱ ነው። የቀይ ባሕር ዳርቻም ስደተኛ ማሻገር አልያም በሰፊ ሆዱ ውጦ ማስቀረት አይታክተውም።
የኦቦክ ባሕር ዳርቻዎችም ከለላ ያጣን ስደተኛ ለማሳደር ፊታቸውን አያጠቁሩም።
በርካቶች ወደ አገራቸው የሚመልሳቸው እንዳጡ በሚናገሩባት ኦቦክ፣ ሌሎች በርካቶች ደግሞ እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል በሚል ጂቡቲ ድንበር ሆነው የመንን ይናፍቃሉ።
ከየመን ለመውጣት ቀዳዳ የጠፋባቸውን በርካታ ስደተኛ የተመለከቱት እነ አደም ደግሞ፣ ወደ ኦቦክ ለአዲስ ስደት የሚተመውን ወጣት እየተመለከቱ ለእኛ ግን ከዚህ ሁሉ አገር ቤት ገብቶ የሚሆነውን መጠበቅ ይሻለናል ሲሉ የእግር ጉዟቸውን ወደ ኢትዮጵያ ቀጥለዋል።
ማን ያውቃል ከስደት የተመለሱባት ምድር በአዲስ ሲሳይ ትቀበላቸው፣ አልያም ደላላ ለዳግም ስደት ልባቸውን አሸፍቶት ወደ በረሃ ይወጡ ይሆናል።