የአፍሪካ ልማት ባንክ ሕንጻ

16 ህዳር 2023, 18:16 EAT

አህጉራዊው የገንዘብ ተቋም የአፍሪካ ልማት ባንክ አዲስ አበባ ውስጥ ሠራተኞቹ በአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ታስረው አካላዊ ጥቃት ደረሰባቸው አስታወቀ።

በአህጉሪቱ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎችን በተለያየ መልኩ በገንዘብ የሚደግፈው ባንኩ ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 06/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት ሁለት ሠራተኞች በአዲስ አበባ “ከሕግ ውጪ” ታስረው አካላዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ብሏል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም. ሠራተኞቹ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካሳወቀ በኋላ በፍጥነት እንደተፈቱም ገልጿል።

“መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት ሁለት የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ባልደረቦች ያለ ይፋዊ ማብራሪያ በፀጥታ ኃይሎች በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዘው አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸው ለሰዓታት ታስረዋል” ብሏል።

ባንኩ ክስተቱን ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሳወቀ በኋላ ሠራተኞቹ በፍጥነት መለቀቃቸውን እና ክስተቱም በዝርዝር እንደሚመረመር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል መግባታቸውን ባንኩ በመግለጫው ላይ አስታውቋል።

“የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳዩን እንዳወቁት በፍጥነት እርምጃ ወስደው ሠራተኞቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ትዕዛዝ መስጠጣቸው እና ጉዳዩ በአስቸኳይ እንደሚጣራ ቃል መግባታቸው አስደስቶናል” ብሏል ባንኩ።

ባንኩ በመግለጫው ላይ ታስረው እንግልት ደረሰባቸው ያላቸውን የባንኩን ሠራተኞች ማንነት፣ የሥራ ድርሻ እና ክስተቱ ያጋጠመበትን ሁኔታ በተመለከተ ያለው ነበር የለም።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ክስተቱትን የዲፕሎማሲያዊ መብት ጥሰት ብሎ የገለጸው ሲሆን፣ እስሩን በተመለከተ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ይፋቂ ቅሬታውን ማቅረቡንም ጨምሮ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቅሬታውን በይፋ ተቀብሎ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ ለክስተቱ ክብደት በመስጠት “ሕግን የተላለፉት ላይ ጥልቅ ምርመራ ተደርጎ ለፍትሕ እንደሚቀርቡ ማረጋገጫ ሰጥቶኛል” ብሏል።

መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉም ሆነ ለሥራ ወደ አገሪቱ የሚመጡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ሠራተኞች በቪዬና ኮንቬንሽን እና ባንኩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በደረሰው ስምምነት መሠረት ሙሉ መብቶቻቸው እና ዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብታቸው መከበሩ እንደሚቀጥል ከመንግሥት ማረጋገጫ እንደተሰጠው ባንኩ አመልክቷል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጠው ገልጾ፣ ክስተቱን በተመለት በዲፕሎማሲያዊ መስመሮች ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እየተመለከተው መሆኑንም ገልጿል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ ቁልፍ የፋይናንስ አጋሮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የባንኩ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ በመጡ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር።

ባለፈው መስከረም 2016 ዓ.ም. ባንኩ በኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ የ100 ሚሊዮን ዶላር በጀት ማጽደቁ ይታወሳል።