ተመሳስለው የሚሠሩ ምርቶች

ከ 5 ሰአት በፊት

የኒው ዮርክ ባለሥልጣናት 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተመሳስለው የተሠሩ የዲዛይነር ምርቶችን መያዛቸውን አስታወቁ።

ይህን ያህል መጠን ያለው ተመሳስሎ የተሠራ ቁሳቁስ በቁጥጥር ሥር ሲውል በአሜሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።

ባለሥልጣናቱ እንደገለጡት 219 ሺህ ‘ፌክ’ የእጅ ቦርሳዎች፣ ጫማዎች እና ሌሎችም ውድ ዕቃዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ሁለት ግለሰቦች እኒህን ተመሳስለው የተሠሩ ቁሳቁሶች ማንሃታን ከሚገኝ መጋዘን ውስጥ እያከማቹ ሲሸጡ ነበር ተብለው ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ሁለቱ ሰዎች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 10 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል።

የኒው ዮርክ ፖሊስ ኮሚሽነር ኤድዋርድ ኤ ካባን በለቀቁት መግለጫ ተመሳስለው የሚሠሩ ምርቶች “ሕጋዊ ሱቆችን፣ መንግሥትን እና ሸማቹን ማሕበረሰብ ይጎዳሉ” ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ሕግ የደቡብ ኒው ዮርክ ቀጣና ቢሮ አዳማ ሶው እና አብዱላይ ጃሎህ የተባሉ ሰዎች ረቡ ዕለት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይፋ አድርጓል።

የዩኤስ አቃቤ ሕግ እንደገለጠው ሁለት ግለሰቦች ካለፈው ዓመት ጥር እስከ ኅዳር ባለው ጊዜ “ትልቅ መጠን ያለው ተመሳስሎ የተሠራ ምርት ሲያጋግዙ ነበር።”

ባለሥልጣናት የለቀቁት ፎቶ ውድ የእጅር ቦርሳዎች፣ የኪስ ቦርሳዎች [ዋሌት]፣ የፀሐይ መነፅሮችና ሌሎችም ‘ፌክ’ ምርቶች በገፍ ተደርድረው ያሳያል።

የዕቃዎች አጠቃላይ ዋጋ ሲሰላ ወደ 1.03 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ባለሥልጣናቱ ገልጠዋል።

አክለው እኒህ ተመሳስለው የተሠሩት ምርቶች ገበያ ላይ የሚሸጡበት ዋጋ አምራቾች በችርቻሮ እንዲሸጥ ከሚያወጡት ዋጋ እጅግ ያነሰ ነው ብለዋል።

ፖሊስ፤ አዳማ ሶው የተባለው ግለሰብ ከሚቆጣጠረው ግቢ ብቻ 502 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ የሚያወጡ 83 ሺህ ሐሰተኛ ምርቶች በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ከአብዱላይ ጃሎህ ግቢ ደግሞ 237 ሚሊዮን ዶላረ የሚያወጡ 50 ሺህ ገደማ ተመሳሳይ ምርቶች ተይዘዋል።

ባለፈው መስከረም የኒው ዮርክ ፖሊስ 35 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ተመስስለው የተሠሩ ምርቶችን ይዞ 18 ሰዎች ማሰሩ ይታወሳል።

ታችኛው ማንሃታን በተለይ ደግሞ ካናል መንገድ ተብሎ የሚጠራው ሥፍራ ተመሳስለው የተሠሩ ምርቶች በሰፊው የሚቸበቸቡበት ሥፍራ ነው።