ዩክሬናውያን በዋና ከሀገራቸው ለመውጣት ከሚሞክሩባቸው ወንዞች አንዱ ቲሳ ወንዝ አንዱ ነው።
የምስሉ መግለጫ,ዩክሬናውያን በዋና ከሀገራቸው ለመውጣት ከሚሞክሩባቸው ወንዞች አንዱ ቲሳ ወንዝ አንዱ ነው።

ከ 3 ሰአት በፊት

ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ዩክሬናውያን በሩሲያ በከፈተባቸውን ወረራ የተጣለባቸውን ወታደራዊ ግዳጅ በመሸሽ አገራቸውን ጥለው መውጣታቸውን ቢቢሲ ባሰባሰበው መረጃ መረዳት ችሏል።

ከነዚህ ዩክሬናውያን አንዳንዶቹ ወንዝ እየዋኙ ሲወጡ ሌሎች የታመሙ በማስመሰል አገራቸውን ተሰናብተዋል።

ድቅድቅ ጨለማ “ምቹ አጋጣሚ” የፈጠረላቸው ደግሞ በቀላሉ ዩክሬንን ጥለው ሄደዋል።

በተለይ ወንዝ እየዋኙ ከሀገር ለመሸሽ በሚደረግ ሙከራ ህይወታቸውን ያጡ በርካቶች ናቸው።

ሌሎች ከ21 ሺህ በላይ የሚሆኑ ግዳጅ የሸሹ ደግሞ ከሀገር ለመሸሽ ሲሞክሩ በዩክሬን የጸጥታ ኃይሎች መያዛቸውን ባለስልጣናት አረጋግጠዋል።

ሩሲያ ኪዩቭ ላይ ወረራ ስትከፍት ከ18 እስከ 60 ባለው የዕድሜ ክልል ያሉ ወንድ ዩክሬናውያን ከአገር እንዳይወጡ ታግደዋል።

ቢቢሲ ይህንን ዕገዳ ጥሰው ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት፣ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወይም አዲስ ኑሮ ለመመስረት ከአገራቸው የተሰደዱ ዩክሬናውያንን አነጋግሯል።

ከዩክሬን ግዳጅን አልቀበልም ብሎ ሸሽቶ የወጣ ይቬግኒ የተባለ ግለሰብ የተሰደደበትን ምክንያት ሲገልጽ “ዩክሬን ውስጥ ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል ታዲያ?” ሲል ጠይቆ “ሁሉም ሰው ጦረኛ አይደለም። ሀገሩ በሙሉ መቆለፍ አይገባውም። በሲቪየት ህብረት ጊዜ እንደነበረው ሁሉንም አንድ ላይ መጠፍነግ አይቻልም” ብሏል።

ቢቢሲ የዩክሬን አጎራባች ከሆኑት ሮማኒያ፣ ሞዶልቫ፣ ፖላንድ፣ ሀንጋሪና ስሎቫኪያ መንግሥታት የድንበር አስተዳዳሪዎች ባገኘው መረጃ ጦርነቱ ከተጀመረበት የአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 እስከ ባለፈው ነሀሴ 19 ሺህ 740 ዩክሬናውያን እነዚህን ድንበሮች አቋርጠው በህገወጥ መንገድ ከአገር መውጣታቸውን አረጋግጠዋል።

በዩክሬን ባለስልጣናት ከተያዙት 21 ሺህ 113 ዩክሬናውያን መካከል 14 ሺህ 313 በላይ የሚሆኑት ድንበሮቹን በእግር ጉዞ አልያም ወንዞችን እየዋኙ ለማቋረጥ የሞከሩ ናቸው። የተቀሩት 6 ሺህ 800 አጭበርብረው ከአገራቸው ለመውጣት የሞከሩ ናቸው። ይህምም መታመማቸውን የሚገልጽ የተጭበረበረ ሰንድ ማቅረብን ይጨምራል።

አንዳንዶቹ የህክምና ማስረጃዎች ከወታደራዊ ሆስፒታሎች የወጡ ናቸው።

ይህንን በተመለከተ ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ባለፈው ነሀሴ ባደረጉት ንግግር የአገሪቱ የወታደራዊ ህክምና ኮሚሽን በተደረገ “የተበላሸ ውሳኔ” ወረራው ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ከአገራቸው የወጡ ሰዎች ቁጥር በ10 እጥፍ መጨመሩን ገልጸዋል።

በዚህም ሳቢያ በሁሉም ክልሎች ያሉ የወታደራዊ ህክምና ክፍል ኃላፊዎች ከስልጣን መባረራቸውን እና ከ30 በላይ ሰዎች ደግሞ ለህግ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

የፕሬዝዳንቱ የምክር ቤት ተወካይ ፌድሪ ቬንሳልቭስኪ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጉዳዩ ችል የማይባል እና የተስፋፋ ነው የሚሉት ተወካዩ ሙስናን ለመከላከል ግን አገራቸው ከፍተኛ ጥረት እያደረገች እንደሆነ አመላክተዋል።

አክለውም ከአገር የሸሹት ወይም ለመሸሽ የሞከሩት ሰዎች ቁጥር የዩክሬን የመዋጋት አቅም ላይ ምንም ተጽዕኖ የለውም ብለዋል።

“አገራቸውን መጠበቅ የሚፈልጉ ዩክሬናውያን ከ95 እስከ 99 በመቶ ይሆናሉ. . .ግዳጅን ለመሸሽ የሚሞክሩት ደግሞ ከ1 እስከ 5 በመቶ የሚሆኑት ናቸው። ይህ የዩክሬን የመከላከል አቅም ላይ ዋሳኝ ቁጥር አይደለም” ሲሉም አክለዋል።

ባለፈው ነሀሴ የአሜሪካ ባለስልጣናት በጦርነቱ የተገደሉ ዩክሬናውያን እስከ 70 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ገልጸዋል። ሆኖም ኪዬቭ ይህንን መሰል መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች።

በተጨማሪም ዩክሬን ያላትን የተዋጊ ብዛት ይፋ አላደረገችም። ሆኖም አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር ሩስተም ኡሜሮቭ ዩክሬን ከ800 ሺህ በላይ ወታደር እንዳላት ገልጸዋል።

በዚህም መሃል ሀገራቸውን ለመሽሽ የሚሞክሩ ወይም የሸሹ ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች አሉ።

ከሩስያ ጋር የምታደርገው ጦርነት መቼ እንደሚጠናቀቅ በማይታወቅበት ሁኔታ ሀገርን ጥሎ የመሸሽ ጉዳይ መቼ እልባት እንደሚያገኝ ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም።