የእስራኤል ጦር አል-ሺፋ ሆስፒታል ገብቷል

ከ 3 ሰአት በፊት

በእስራኤል ወታደሮች ቁጥጥር ስር በዋለው በጋዛው ትልቁ ሆስፒታል ውሃ እና ኦክስጅን ባመለመኖሩ ታካሚዎች “በውሃ ጥም እየተሰቃዩ” መሆኑን ዳይሬክተሩ ገለጹ።

የሆስፒታሉን ሁኔታ “አስከፊ” ሲሉ ሙሐመድ አቡ ሳልሚያ ገልጸዋል። በሆስፒታሉ 650 ታካሚዎች፣ 500 ሐኪሞች እና 5 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ።

የእስራኤል ጦር ሆስፒታሉን መክበቡን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ከላይ እንደሚያንዣብቡ ጠቁመዋል። ውስጥ የሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች የሚያደርጉትን ፍተሻ መቀጠላቸው ተሰምቷል።

ሐማስ ላይ የጀመረውን ዘመቻ “ጥበባዊ፣ ልዩ እና ጥልቅ በሆነ መንገድ” እየተካሄደ ነው ሲል ጦሩ ገልጿል። ከሆስፒታሉ መውጣት ያልቻለ ከድር የተባለ ጋዜጠኛ ለቢቢሲው ራሽዲ አቡ አሎፍ በስልክ እንደተናገረው የእስራኤል ወታደሮች በሁሉም ቦታ በየአቅጣጫው እየተኮሱ ነው።

ቢቢሲ ዘገባዎቹን በገለልተኛነት ማረጋገጥ አልቻለም።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ባለፈው ረቡዕ በአል-ሺፋ ወረራ ከጀመረ ወዲህ፣ የሐማስን መሳሪያዎች እና ቁሳቁሶች ያሳያሉ በሚል በርካታ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ለቋል።

ሐሙስ ዕለት “ዋሻ እና ብዙ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን የያዘ ተሽከርካሪ” ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የእስራኤል ወታደሮች የአል-ሺፋን ዋና የውሃ መስመር አፈንድተዋል ሲሉ አቡ ሳልሚያ ከሰዋል።

“የጥቃቅን ሥራዎች ቢቀጥሉም ማንም ሰው ከአንዱ ህንጻ ወደ ሌላኛው መንቀሳቀስ አይችልም። ከባልደረቦቻችን ጋር ያለው ግንኙነትም ተቋርጧል” ብለዋል።

ከድር ቀደም ሲል ለቢቢሲ እንደተናገረው የእስራኤል ወታደሮች “ሁሉንም ክፍሎች ወረዋል”፤ የሕንፃውን ግንብ ደቡባዊ ክፍል እና በደርዘን የሚቆጠሩ መኪኖች አውድመዋል።

የከድር የስልክ ልውውጥ ከመቋረጡ በፊት የታጠቁ ቡልዶዘሮች መግባታቸውን ተናግሯል።

በሐማስ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የእስራኤል ቡልዶዘሮች የሆስፒታሉን ደቡባዊ መግቢያ አወድመዋል ብሏል።

መስከረም 26 በመቶ የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ያደረሱትን ድንበር ዘለል ጥቃት ለመበቀልና ሐማስን ለማጥፋት እስራኤል ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምራለች። እስራኤልን ጨምሮ እንደ እንግሊዝ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ሐማስን በአሸባሪነት ፈርጀውታል።

ይሁዲት ዌይስ

ሐማስ በእስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት ከ 1200 በላይ ሰዎች ሲገደሉ 240 የሚደርሱት ደግሞ ታግተዋል።

እስራኤል የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዋን ከጀመረች ወዲህ በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በግዛቱ ቢያንስ 11,400 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በጋዛ የከፋ ቀውስ እንዳለ እና የጋዛ ሰርጥ ወደ ህጻናት መቃብር ስፍራ መቀየሯንም ገልጿል።

የእስራኤል ጦር ሐሙስ አመሻሽ ላይ ከታጋቾች መካከል የአንደኛው አስከሬን በአል-ሺፋ አካባቢ መገኘቱን አስታውቋል።

ጦሩ ተጎጂዋ ይሁዲት ዌይስ እንደምትባል ገልጾ፣ ከደቡባዊ እስራኤል ከሚገኘው ቤቷ ታግታ እንደነበር ገልጿል።

በሌላ በኩል ደግሞ በጋዛ የሞባይል ስልክ፣ የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት፣ ዋይፋይ እንዲሁም መደበኛ የስልክ መስመሮች መቋረጣቸው ተገለጸወል።

የፍልስጤም ኮሚኒኬሽን ኩባንያ የሆነው ጃዋል በጋዛ ሁሉም የቴሌኮም አማራጮች መቋረጣቸውን አስታውቋል።

“በጋዛ የቴሌኮም አግልግሎቶችን የሚያንቀሳቀሱ የኃይል ምንጮች ተሟጠው በማለቃቸው ሁሉም የቴሌኮም አማራጮች ተቋረጠዋል” ብሏል ኩባንያው።

በመላው ዓለም የኔትዎርክ ግንኙነትን የሚከታተለው ኔትብሎክስ የተሰኘው ድርጅትም ይህንኑ ያረጋገጠ ሲሆን ጋዛ የጠቅላላ የኢንተርኔት መቋረጥ ውስጥ ትገኛለች ብሏል።